ሰባት ወንበሮችን ያሸነፈው ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ምክር ቤት እንደማይገባ ገለጸ

የትብብርት ለኢትዮጵያ አንድነት ቅስቀሳ

የፎቶው ባለመብት, Enat Party

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የአምስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅንጅት የሆነው 'ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት' በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ያገኛቸውን ወንበሮች እንደማይረከብ ለቢቢሲ አስታወቀ።

ቅንጅቱ ከዚህ ቀደም ያቀረባቸው ቅድመ ሁኔታዎች የሚሟሉ ከሆነ ምክር ቤት የመግባት ጉዳይን ሊያጤነው እንደሚችል ገልጿል።

ጥምረቱ በተደጋጋሚ ያወጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች እንዳልተሟሉ በመግለጽ ከምርጫው ራሱን እንደሚያገልል ሲያሳውቅ የቆየ ሲሆን፤ ከምርጫው ከሁለት ቀን በኋላ ደግሞ ቢያሸንፍም ምክር ቤት እንደማይገባ ገልጾ ነበር።

ሰኔ 14/ 2018 ዓ.ም. ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው አጠቃላይ የምርጫ ውጤት እንደሚያሳየው ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ሁለት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና አምስት የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎችን አሸንፏል።

ጥምረቱ 1,032 ዕጩዎችን በማቅረብ ከብልጽግና እና ከኢዜማ ቀጥሎ ከፍተኛ ተመራጮችን ለተለያዩ ምክር ቤቶች ያስመዘገበ ሦስተኛው ፓርቲ ነው።

በአዲስ አበባ፣ በአማራ እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች በአጠቃላይ ሰባት ወንበሮችን በምርጫ 2018 ያሸነፈው ቅንጅቱ፤ ምርጫውን አውግዞ በአቋሙ እንደጸና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ጌትነት ወርቁ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ምርጫውን "የጨረባ" ሲል የገለጸው ትብብሩ፤ "እጅግ የተወሳሰበውን የአገራችንን ችግር ከድጡ ወደ ማጡ ከመውሰድ በዘለለ ዲሞክራሲን አያዋልድም" በማለት አጣጥሎታል።

ጥምረቱ የአገሪቱን የሰላም እና የደኅንነት እጦት እንዲሁም "ጠባብ" የፖለቲካ ምኅዳር በዋና ምክንያትነት ያነሳል።

". . .መንግሥት ሸብረክ ብሎ ወደ መነጋገሩ፤ ወደ መደራደሩ እስኪሄድ ድረስ እኛም ዕውቅና አንሰጠውም። የብልጣ ብልጥ ጨዋታ ነው" በማለት አገራትም ምርጫውን "እውቅና እንዲነፍጉት ውትወታ" እያደረጉ መሆናቸውን አቶ ጌትነት ገልጸዋል።

ቢቢሲ አቋማችሁ ከምርጫው በፊትም ይህ ከሆነ ለምን በምርጫው ተሳተፋችሁ? ሲል ላነሳላቸው ጥያቄ፤ አቶ ጌትነት ለመሳተፋቸው ምክንያት የሆኑ "ንግግሮች" ስለነበሩ እንደሆነ አመልክተው፤ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ግን ተቆጥበዋል።

"በቅድመ ሁኔታዎቻችን ላይ ምናልባት ጆሮ የመስጠት፤ ዘምበል የማለት ምልክቶች ሊኖሩ ይችላሉ የሚል እምነቶች ነበሩ" በማለት በግልጽ መናገር ባልፈለጉት እና "ወደፊት ይፋ እናደርገዋለን" ባሉት ምክንያት ወደ ምርጫው ለመግባት መወሰናቸውን ተናግረዋል።

አቶ ጌትነት ምክር ቤት አንገባም የሚለው አቋማቸው በሰባት ምርጫ ክልሎች ለመረጣቸው ሕዝብ ድምፅ መንፈግ አይደለም ብለዋል።

ተመሳሳይ ትችት በተለይም በ1997 ዓ.ም. ምርጫ ከነበረው የቅንጅት አቋም ጋር ተገናኝቶ እንደገጠማቸው የጠቆሙት ኃላፊው፤ የሁኔታውን ልዩነት ሲያብራሩ "የሰማይ እና የምድር ያህል ነው" ብለዋል።

"በሰባት ኪስ ቦታዎች ላይ ተሰጥቶን 'ይህን ተቀበል እና ሌላውን አቆይ' ከምንባል ለታላላቅ ጥያቄዎች መልስ እንፈልግ የሚል ነው" ሲሉ አቋማቸው "የማመዛዘን"፣ "የማበላለጥ" እንደሆነ ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ መንግሥት ላስቀመጧቸው ቅድመ ሁኔታዎች ለመነጋገር ቀና ምላሽ ከሰጠ ውሳኔያቸውን እንደሚቀለብሱ ተናግረዋል።

ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት እጩዎች የምረጡኝ ዘመቻ እያካሄዱ

የፎቶው ባለመብት, Coalition for Eth. Unity

"አንገባም ማለት ለዘላለም አንገባም ማለት አይደለም" በማለት ኳሱ መንግሥት ሜዳ ላይ መወርወሩን ጠቁመዋል።

ምክር ቤት መግባቱን 'እንደ መደራደሪያ መሣሪያ' የተመለከተው ጥምረቱ፤ "በባዶ ሜዳ ብቻ የምንጮህ አይደለንም" ብሏል።

"ጦርነትን ማቆም፣ እስረኞችን መፍታት፣ የፖለቲካ ምኅዳርን ማስተካከል፣ በአገር ዕጣ ፈንታ ላይ መነጋገር ጠዋት ተጀምሮ 11 ሰዓት ማታ ላይ የሚያልቅ አይደለም። ቢያንስ ግን እኛ የምንፈልገው ወደ እዚያ [ወደ ድርድር] የሚገፋ ነገር አለ ወይ? ነው" በማለት መከራከሪያ ያቀርባሉ።

ኢሕአፓ፣ መኢአድ እና እናት ፓርቲን ጨምሮ አምስት ፓርቲዎችን ያጣመረው 'ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት' ተመራጮቹ የጥምረቱን ውሳኔ አሻፈረኝ ብለው የሚገቡ ከሆነ እርምጃ እንደሚወስዱ አስታውቀዋል።

"የተቋም [የፓርቲ] እንጂ የግለሰብ ጉዳይ አይደለም" ሲሉ አቶ ጌትነት ተመራጮቹ 'የሞራል እና የሕግ ኃላፊነት አለባቸው' ብለዋል።

ማንኛውም ዕጩ "ትብብርን ወክሎ ሊገባ አይችልም። የሥነ ምግባር እርምጃዎችንም እንወስዳለን" በማለት ውግዘት እና ከፓርቲው እስከማባረር የደረሱ እርምጃዎችን እንደሚወስዱ ጠቁመዋል።