ኢዜማ 1 ወንበር ባሸነፈበት የኦሮሚያ ምክር ቤት መቀመጫ ያላገኘው ኦነግ በአዲስ አበባ 2 ወንበር አሸነፈ

በሰባተኛው የኢትዮጵያ አጠቃላይ ምርጫ በኦሮሚያ ምክር ቤት አንድም ወንበር ያላሸነፈው ኦነግ፤ በአዲስ አበባ ምክር ቤት ሁለት ወንበር ሲያገኝ ኢዜማ ደግሞ በኦሮሚያ ምክር ቤት አንድ መቀመጫ አገኘ።
ብልጽግና አብዛኛውን መቀመጫ ባሸነፈበት አጠቃላይ ምርጫ 40 የተቃዋሚ ፓርቲ ዕጩዎች እና ስምንት የግል ተወዳዳሪዎች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ አሸንፈዋል።
ውድድር ከተደረገባቸው 501 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች ገዢው ብልጽግና ፓርቲ ለተጨማሪ አምስት ዓመታት በሥልጣን ላይ ለመቆየት የሚያስችለውን 438 አሸንፏል።
በምርጫው ከተሳተፉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ከፍተኛውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ያገኘው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ሲሆን 13 መቀመጫዎችን አሸንፏል።
ስምንት የግል ዕጩዎች፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) 6፣ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) 3፣ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ 3፣ ነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ 3፣ ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ፓርቲ 2 መቀመጫዎችን ሲያሸንፉ አምስት ፓርቲዎች ደግሞ አንድ አንድ መቀመጫ አግኝተዋል።
በተጨማሪም ብልጽግና ምርጫ በተካሄደባቸው 11 የአገሪቱ ክልሎች ውስጥ እንዲሁም በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ እና በድሬ ዳዋ ምክር ቤቶች ውስጥ ካሉት መቀመጫዎች አብዛኛውን አግኝቷል።
ብልጽግና በፌደራል፣ በክልል እና በከተሞች መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችለውን የምክር ቤት መቀመጫዎችን አሸንፏል።
በዚህም የኦሮሚያን 523፣ የአማራ 257፣ የሶማሌ 214፣ የሲዳማ 175፣ የጋምቤላ 176፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ 143፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ 144፣ የደቡብ ኢትዮጵያ 182፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ 145፣ የአፋር 124፣ የሐረሪ 32፣ የአዲስ አበባ 134 እና የድሬዳዋ 161 የምክር ቤት መቀመጫዎችን ዕጩዎቹ አሸንፈዋል።
158 መቀመጫዎች ላሉት የዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ምክር ቤት መቀመጫዎች ከተወዳደሩት ፓርቲዎች እና የግል ዕጪዎች መካከል ብልጽግና 134ቱን ሲያሸንፍ፣ ኢዜማ 8፣ አንድ ኢትዮጵያ ፓርቲ 4፣ ሕዳሴ፣ ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ሰላም ለኢትዮጵያ እና ኦነግ ሁለት ሁለት መቀመጫ አሸንፈዋል። ሦስት ፓርቲዎች እና አንድ የግል ተወዳዳሪም አንድ አንድ ወንበር ተጋርተዋል።
528 መቀመጫዎች ካሉት የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት ውስጥ ብልጽግና 523ቱን ሲያሸንፍ፣ የግል ተወዳዳሪዎች 4ቱን እንዲሁም የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) 1 መቀመጫ አሸንፈዋል።
በበርካታ የኦሮሚያ ክልል ቦታዎች ላይ ዕጩዎችን ያቀረበው በኦሮሚያ ከሚንቀሳቀሱ ዋነኛ ፓርቲዎች መካከል የሆነው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በፌደራልም ሆነ በክልሉ ምክር ቤት አንድም መቀመጫ ባያሸንፍም በአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ሁለት መቀመጫዎችን አግኝቷል።
ግንቦት 24/2018 ዓ. ም. ከትግራይ ክልል እና ከአንዳንድ አካባቢዎች ውጪ በመላው አገሪቱ ለተካሄደው ምርጫ 54 ሚሊዮን በላይ በመራጭነት የተመዘገቡ ሲሆን ከመካከላቸውም 96 በመቶው በላይ የሚሆኑት ድምጽ መስጠታቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቋል።













