ከፍተኛ ነዳጅ አምርታ ትንሹን ለምትጠቀመው ኖርዌይ የኢራን ጦርነት የከፈተላት ገበያ

በኖርዌይ በውሃ ላይ የሚገኝ የነዳጅ ማውጫ

የፎቶው ባለመብት, Kristian Helgesen/ Getty

የምስሉ መግለጫ, በኖርዌይ ምጣኔ ሃብት ውስት ጋዝ እና የነዳጅ ዘይት ቁልፍ ሚና አለው
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

ኖርዌይ በዓለም ላይ ካሉ ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት ከሚሰጡ እና አረንጓዴ ከሆኑ አገራት መካከል ቀዳሚዋ ናት። አገሪቱ የምትጠቀመው ኤሌትሪክ በአብዛኛው የሚመረተው ከታዳሽ ኃይሎች ነው።

በከተሞቿ ውስጥ በየቦታው የሚንቀሳቀሱ ብስክሌቶች መንገዶቹን ከእግረኞች ጋር በፀጥታ ይጋራሉ። በኖርዌይ መንገዶች ላይ ከሚታዩ አስር አዳዲስ መኪኖች ዘጠኙ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠሩ ናቸው።

ከ35 ዓመታት በፊት ኩባንያዎች ለሚለቁት ለእያንዳንዱ ቶን በካይ ጋዝ የሚያስከፍለውን የካርቦን ታክስ ከጀመሩ የመጀመሪያዎቹ አገሮችመካከልም አንዷ ነች።

ሆኖም ኖርዌይ በአገር ውስጥ ባትጠቀመውም ወደ ውጭ ለመላክ የነዳጅ ዘይት እና ጋዝ ምርትዋን በማሳደጓ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ አስገኝቶላታል።

እንደ እውነቱ ከሆነ የአገሪቱ የወደፊት ዕጣ ፈንታ የተሳሰረው ሕዝቦቿ የማይጠቀሙትን ነዳጅ በመሸጥ ከሚገኝ ገቢ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው።

ኖርዌይ አገሯን ከአየር ብክለት ለማጽዳት ጉልህ እርምጃዎች እየወሰደች ለዓለም ገበያ ከፍተኛ የሆነ ነዳጅ ማቅረቧ የፈጠረውን ባለሙያዎች የኖርዌይ ተቃርኖ ብለው የሚጠሩት ሲሆን፣ ለዓመታት ከፍተኛ የፖለቲካ እና የማኅበራዊ ክርክር አስነስቷል።

ታዲያ በመካከለኛው ምሥራቅ የተቀሰቀሰው ጦርነት የሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ እንዲዘጋ በማድረጉ በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ማስከተሉ ለኖርዌይ ካዝና ምን ትርጉም አለው? ይህስ በአገሪቱ ውስጥ የሚደረጉ ክርክሮች እንደገና ቀስቅሶታል?

ነዳጅ ለኖርዌይ ምን ማለት ነው?

በተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ልማት መረጃ ጠቋሚ መሠረት ኖርዌይ በዓለም ላይ ካሉት እጅግ የበለፀጉ አገራት አንዷ ስትሆን የኢነርጂ ዘርፉም ለዕድገቱ ዋነኛ ምንጭ ነው።

ከዚህ ዘርፍ የሚገኙ ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ የሚገኘው ገቢ 60 በመቶ የሚሆነውን የሚሸፍን ሲሆን፣ ከአገሪቱ አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) 2 በመቶ በላይ ይይዛል።

የኖርዌይ መንግሥት በአገሪቱ የሚንቀሳቀሰው የነዳጅ አውጪ የሆነው ኢኩኖር ኩባንያ ውስጥ አብላጫውን ድርሻ የሚይዝ ሲሆን፣ አብዛኛውን የሚያገኘውን ትርፍ ወደ አገሪቱ የሀብት ካዝና ፈሰስ ያደርጋል።።

በ2025 መጨረሻ ላይ 1.9 ትሪሊዮን ዶላር የሚገመት ሀብት ገቢ ሆኖ ነበረ፤ ይህም ለእያንዳንዱ የኖርዌይ ዜጋ ቢከፋፈል በግምት 350 ሺህ ዶላር ማለት ነው።

ይህ እያደገ የመጣ የገንዘብ ቋት የኖርዌይን የጡረታ ሥርዓት እና የደኅንነት ሁኔታዋንም እንዲደረጅ እና ለጋስ እንዲሆን አድርጎታል።

የኤሌትሪክ መኪናዎች ቻርጅ እየተደረጉ

የፎቶው ባለመብት, Jonathan Nackstrand/AFP via Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አሁን አሜሪካ እና እስራኤል ኢራን ላይ ጦርነት ካወጁ በኋላ በመካከለኛው ምሥራቅ አለመረጋጋት በመስፈኑ ባለሙያዎች የገንዘብ ክምችቱ ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ይናገራሉ።

እንደ እውነቱ ከሆነ ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የኖርዌይ መንግሥት ገቢ ጨምሯል ተብሎ ይጠበቃል። የኦስሎ የአክሲዮን ገበያ ዋጋ በከፍተኛ መጠን ሲጨምር ይህም በአብዛኛው በአገር ውስጥ የኢነርጂ ኩባንያዎች የበላይነት የተያዘ ነው።

በተመሳሳይ የኖርዌይ የሌበር መንግሥት የኖቤል የሰላም ሽልማት የምትሰጠው አገር ከጦርነቱ በገንዘብ ተጠቃሚ ናት የሚለውን አመለካከት ለመቃወም ሞክሯል።

የአገሪቱ የገንዘብ ሚኒስትር እና የቀድሞ የኔቶ ዋና ፀሐፊ የንስ ስቶልተንበርግ ሁኔታውን "ተቃርኖ" ሲሉ ገልጸውታል። ኖርዌይ ከሰላም የበለጠ እንደምታገኝም ጨምረው ገልጸዋል።

"የነዳጅ ዋጋ መጨመር እንደሚጠቅመን ግልጽ አይደለም" ሲሉ ለኤል ፓይስ ጋዜጣ ተናግረዋል።

"ኖርዌይ አሁን በሀብት ክምችቷ በኩል ለዓለም አቀፍ የፋይናንስ ገበያዎች ከፍተኛ ተጋላጭነት አላት። የአክሲዮን ገበያው ማሽቆልቆል የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ መጨመር ከሚረዳን በላይ እየጎዳን ነው።"

የኖርዌይ የሀብት ክምችት ኃላፊ ኒኮላይ ታንገን ለሮይተርስ እንደተናገሩት በኢራን ጦርነት ምክንያት ከፍተኛ የነዳጅ ገቢ ቢፈጠርም የአክሲዮን ዋጋ መቀነስ እና በገንዘብ ምንዛሬ መጨመር የተነሳ ይህ ነው የሚባል ጥቅም አገሪቱ አላገኘችም።

ሆኖም ተንታኙ ሴሲሊ ላንጉም ቤከር እንደገለጹት "አሳዛኙ እውነታ ዓለም ሲቃጠል ገንዘብ ወደ አገራችን በጀት በከፍተኛ መጠን ይገባል የሚለው ነው።"

ይህ መዋዠቅ በ2022 ሩሲያ ዩክሬን ስትወር ሞስኮ ወደ አውሮፓ የምትልከውን ኢነርጂ በከፍተኛ ሁኔታ በማገዱ የተነሳ ተስተውሏል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኖርዌይ በአውሮፓ ውስጥ ቁልፍ የነዳጅ እና የጋዝ አቅራቢ ሆና ብቅ ብላለች።

አገሪቱ በአውሮፓ ትልቁ የጋዝ አቅራቢ እና የምዕራብ አውሮፓ ትልቁ የድፍድፍ ዘይት አምራች ነች።

"ዛሬ አውሮፓ የሚጠቀመውን ጋዝ 30 በመቶ እና 15 በመቶ የሚሆነውን የነዳጅ ዘይት እናቀርባለን፤ እዚያም 90 በመቶ የሚሆነውን የወጪ ምርታችንን እንልካለን" ሲሉ የኖርዲያ የፋይናንስ ተንታኝ ቲና ሳልትቬት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የኋሊት ጉዞ

በኖርዌይ ተቃውሟቸውን ለማሰማት አደባባይ የወጡ ኖርዌያውያን

የፎቶው ባለመብት, Paul S. Amundsen / Getty

የምስሉ መግለጫ, በኖርዌይ ለዓመታት የፎሲል ነዳጅ ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ ዙሪያ ክርክር ሲደረግ ቆይቷል

ይሁን እንጂ የኢራን ጦርነት እና በመካከለኛው ምሥራቅ የተከሰተው አለመረጋጋት ኖርዌይን በሌሎች በርካታ መንገዶች ጎድቷታል።

ቀዳሚው የኖርዌይ የሞራል ኃላፊነቶች ላይ የቀሰቀሰው ሰፊ ክርክር ነው። ተደማጭነት ያለው የኖርዌይ ሪፊውጂ ካውንስል ከአገሪቱ የሀብት ክምችት የሚገኘው ትርፍ በጦርነቱ የተጎዱ ኢራናውያንን ለመርዳት እንዲውል ጥሪ አቅርቧል። ኖርዌይ፤ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ጦርነት በከፈተችበት ወቅት ይህንን ማድረጓን ጠቁመዋል።

ስቶልተንበርግ ለሮይተርስ እንደተናገሩት ለእነዚህ ጥሪዎች የተሰጠው ይፋዊ ምላሽ ኖርዌይ በዓለም ላይ ከፍተኛ የዓለም አቀፍ እርዳታ ከሚያቀርቡ አገራት መካከል አንዷ እና "ለተቸገሩ አገራት ብርቱ ደጋፊ" መሆኗን ለማመልከት ነው።

በሁለተኛ ደረጃ በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱ ኖርዌይ በአረንጓዴ የኃይል አቅርቦት ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ ግንባር ቀደም መሆኗን ጥያቄ ውስጥ ጥሎታል።

አንዳንድ ታዛቢዎች እንደሚሉት በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው አለመረጋጋት በአረንጓዴ ቴክኖሎጂ እና ኦስሎ ለረጅም ጊዜ ለዘርፉ ያላት ቁርጠኝነትን ያዘገየው ይመስላል።

የኖርዌይ የአካባቢ ጥበቃ ማኅበር ፕሬዝዳንት ትሩልስ ጉሎውሰን ለቢቢሲ "እንደኔ ላሉ የኖርዌይ የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋች ሰዎች ሁኔታው ​​አሳፋሪ እንደሆነ ግልጽ ነው" ብለዋል።

በኖርዌይ ውስጥ ያለው ዋነኛ መከራከሪያ አሁን ዓለም አቀፍ አለመረጋጋት በነዳጅ እና በጋዝ ላይ የበለጠ ጥገኛ መሆንን የሚያረጋግጥ መሆኑን ወደ መቀበል እየተሸጋገረ ነው ሲሉ ጉሎውሰን ተናግረዋል።

"በጥልቅ የአርክቲክ ውሃዎች ውስጥ ስለሚከፈቱ ቦታዎች እየተወራ ነው፤ በማንኛውም ሁኔታ ሊነኩ የማይገቡ ተጋላጭ አካባቢዎች" ሲሉ አክለዋል።

ቀጥሎ ምን ይሆናል?

በባሕር ላይ ሆኖ የሚመለከት ሰው

የፎቶው ባለመብት, Chris Ratcliffe / Getty

የምስሉ መግለጫ, የኖርዌይ መንግሥት የነዳጅ ኢንዱስትሪውን ማስፋፋት ለመቀጠል የሚፈልግ ሲሆን አዳዲስ የሃሰሳ ፈቃድ እየሰጠ ነው

የአካባቢ ጥበቃ ቡድኖችና አክቲቪስቶች መንግሥት በነዳጅ ኢንዱስትሪው ላይ ያለውን ጥገኝነት ለመቀነስ ተጨባጭ እርምጃዎችን እንዲወስድ እና የጊዜ ሰሌዳ እንዲያዘጋጅ ጥሪ አቅርበዋል።

በምላሹም የነዳጅ እና የጋዝ ዘርፉ ለኢኮኖሚው ያለውን ጠቀሜታ እና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የሥራ ዕድሎችን ይፈጥራል ሲሉ ይከራከራሉ።

የኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዮናስ ጋህር ስቶር መንግሥት በቅርቡ 57 አዳዲስ የነዳጅ አሰሳ ፈቃዶችን ሰጥቷል። "ለአውሮፓ ለማቅረብ ተጨማሪ ነዳጅ መፈለጋችንን እንቀጥላለን" ሲሉ ዓላማቸውን አስታውቀዋል።

ኢንዱስትሪው እንዲቋረጥ የጊዜ ሰሌዳ ከማውጣት ይልቅ እንዲያድግ ማድረግ እንደሚያስፈልግ በመሟገት ተከራክሯል።

ብስክሌቶች በቆሙበት አካባቢ የሚያልፍ ሰው

የፎቶው ባለመብት, LightRocket via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኖርዌይ በዓለም ላይ ካሉ አረንጓዴ አገራት መካከል አንዷ እንደሆነች ይታመናል

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርቲያቸው የወጣቶች ክንፎች ጫና ቢያሳድርም፣ የመውጫ ዕቅድ ለማዘጋጀት ብዙም ፍላጎት አላሳዩም።

በምትኩ አስተዳደራቸው ጥቅም ላይ በዋሉ ጉድጓዶች ያለውን የምርት መቀነስ ለማካካስ ከዚህ በፊት ብዙም ፍለጋ ባልተካሄደባቸው የባረንትስ ባሕር ላይ የነዳጅ ፍለጋ እንዲደረግ የሚፈልጉ ይመስላል።

የኢንደስትሪ ኢነርጂ የሠራተኛ ማኅበር አባል የሆኑት ፍሮድ አልፍሃይም "ስለ 200 ሺህ በላይ ቀጥተኛ ሥራዎች እየተነጋገርን ነው። ይህ ወቅት አውሮፓን ያለ ኢነርጂ አቅርቦት የምንተውበት ጊዜ አይደለም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሳልትቬድት በበኩሏ "ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ የሚሄድ ሰዎች የፀሐይዋ መጥለቂያ እየተቀረበ መሆኑን ይገነዘባሉ። ግን ያማል" ብላለች።

ለጊዜው ግን፣ ስለ ለረዥም ጊዜ ከማሰብ ይልቅ ለወቅታዊ ክስተቶች እና በዚህም ምክንያት ለሚፈጠሩት እጥረቶች ምላሽ መስጠት ላይ የበለጠ ትኩረት የተሰጠው ይመስላል።