በአሜሪካ ጊዜያዊ ከለላ ያላቸው ስደተኞች ለቋሚ መኖሪያ ፈቃድ እንዲያመለክቱ ወይም ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ታዘዙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአሜሪካ ጊዜያዊ የጥገኝነት ከለላ አግኝተው የሚገኙ የተለያዩ አገራት ዜጎች ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት ጥያቄ ማቅረብ ወይም አገሪቱን ለቅቀው መውጣት እንዳለባቸው የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደኅንነት ኃላፊ ማርክዌይን ሙሊን አሳሰቡ።
ባለሥልጣኑ ይህንን ማሳሰቢያ የሰጡት የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባለፈው ሳምንት ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ነው።
አገራቸው ውስጥ ባለው ሁኔታ የተነሳ ጊዜያዊ ከላለ አግኝተው አሜሪካ ውስጥ የሚገኙ የሄይቲ እና የሶሪያ ስደተኞችን ሕጋዊ ጥበቃ በማቋረጥ የተወሰደው እርምጃ እንዲጸና ፍርድ ቤቱ ወስኗል።
ጦርነት፣ ሰብአዊ ቀውስ እና ሰብአዊ መብት ጥሰቶች ከሚካሄዱባቸው አገራት ተሰድደው በአሜሪካ ጊዜያዊ ከለላ ወይም ፒቲኤስ በመባል የሚታወቀውን ፈቃድ አግኝተው የሚኖሩ ከ350 ሺህ በላይ የተለያዩ አገራት ዜጎች ይገኛሉ።
በዚህ አሰራር ምክንያት የአሜሪካ ጊዜያዊ የጥበቃ ከለላ ያገኙ እስከ አምስት ሺህ የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን አሉ። ይሁን እንጂ የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደኅንነት መስሪያ ቤት ለሦስት የቆየው የኢትዮጵያውያን ከለላ እንዲቋረጥ ባለፈው ታኅሳስ ላይ ውሳኔ አስተላልፏል።
በ60 ቀናት ውስጥ አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡም አዝዞ ነበር። ይሁን እንጂ ውሳኔው የሚቃወም አቤቱታ የቀረበለት ቦተስን ውስጥ የሚገኝ የፌደራል ፍርድ ቤት እርምጃውን አግዶት ቆይቷል።
ከሄይቲ እና ሶሪያ ስደተኞችን ጋር የተያያዘውን ተመሳሳይ እግድ ሲመለከት የነበረው የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባለፈው ሳምንት ባሳለፈው ውሳኔ ግን፤ ፍርድ ቤቶች ይህንን የትራምፕ አስተዳደር ውሳኔ ማገድ እንደማይችሉ አረጋግጧል።
ይህ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ የኢትዮጵያውያኑ እግድን ጨምሮ በተመሳሳይ ጉዳዮች ላይም ተፈጻሚ እንደሚሆን የሕግ ባለሙያ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የአገር ውስጥ ደኅንነት መስሪያ ቤቱ ውሳኔውን ተከትሎ የሰጠው ማሳሰቢያም በዚህ አሰራር አማካኝነት አሜሪካ ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ጭምር የሚመለከት እንደሚሆን ይገመታል።
የመስሪያ ቤቱ ኃላፊ ሙሊን "አስፈላጊውን የመጠየቂያ ማመልከቻ በማስገባት በዘላቂነት ለመቆየት ፈቃድ አግኝታችሁ መቀጠል አለባችሁ። ካልሆነ ግን ወደ አገራችሁ እንድትመለሱ እንረዳችኋላን" ሲሉ ለስደተኞቹ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።
"የጊዜያዊ ከላላ ፈቃዱ ዘላቂ የመቆያ ፈቃድ ስለማይሆን፤ የአውሮፕላን ትኬታችሁን እና ለመቋቋሚያ የሚሆን 2,100 ዶላር የምንሰጣችሁ ይሆናል" ሲሉም የአሜሪካ መንግሥት የሚሰጠውን ድጋፍ አሳውቀዋል።
የአሜሪካ ፌደራል ሕግ መንግሥት ጦርነትን፣ በሽታን ወይም ሌሎች ሁኔታዎችን ሸሽተው በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚገኙ ግሰለቦች ጊዜያዊ ሕጋዊ ከለላ እንዲሰጣቸው ይፈቅዳል።
ኢትዮጵያውያን ከለላውን ያገኙት በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የሥልጣን ዘመን በ2015 ዓ.ም. ነበር። የባይደን አስተዳደር፤ የጥገኝነት መብት የሌላቸው ኢትዮጵያውያን የሥራ ፈቃድ እንዲያገኙ የሚያደርገውን ይህንን ከለላ የዘረጋው በዋነኛነት ከትግራይ ጦርነት ጋር በተያያዘ ነበር።
በመጀመሪያ ይህ ሕጋዊ ከለላ ለአንድ ዓመት ከመንፈቅ እንዲቆይ ተወስኖ የነበረ ሲሆን፤ ጊዜው ሲጠናቀቅ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የደኅንነት ስጋት አለመቀረፉ ተገልጾ ለተጨማሪ 18 ወራት ተራዝሟል።
ሁለተኛው የቆይታ ጊዜ ባለፈው ታኅሣሥ መጀመሪያ መጠናቀቁን ተከትሎ ግን በስደተኞች ላይ ጠንካራ እርምጃዎችን እየወሰደ ያለው የትራምፕ አስተዳደር ከለላው እንዳይቀጥል ወስኗል።















