ወደ አውሮፓ የሚሻገሩ ስደተኞች የሚጠየቁትን ካልከፈሉ ኩላሊታቸውን ዒላማ ያደረጉት የሊቢያ ታጣቂዎች

የፎቶው ባለመብት, Kurdish Regional Government
ባለፈው ዓመት ወደ ዩናይትድ ኪንግደም እያመሩ የነበሩ ከ300 በላይ ስደተኞች ታግተው ማሰቃየት ከተፈጸመባቸው በኋላ ኩላሊታቸው እንደሚወሰድ ማስፈራሪያ እንደደረሳቸው ለቢቢሲ ተናገሩ።
ከኢራቅ ኩርዲስታን የተሰደዱ ወጣቶች በሊቢያ አማፂያን ቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ ቤተሰቦቻቸው እነርሱን ለማስለቀቅ ለእያንዳንዳቸው 5000 ዶላር እንዲከፍሉ መጠየቃቸውን ተናግረዋል።
ገንዘቡን መክፈል የማይችሉ ከሆነ ግን ኩላሊታቸውን እንደሚወስዱ ማስፈራራታቸውን ጨምረው ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ቢቢሲ ታግተው የነበሩ የተወሰኑ ስደተኞችን ያነጋገረ ሲሆን፣ በአጋቾቹ ቁጥጥር ሥር ሳሉ የሚያሳዩ ምሥሎችንም ተመልክቷል።
ከዚህ በፊት በአጋቾች ቁጥጥር ሥር የነበረ አንድ ሰው የተያዙበት በካምፕ ውስጥ እንደነበር አስረድቶ 180 ያህል ሰዎች በአንድ መጋዘን ውስጥ እንዲቆዩ መደረጋቸውን ገልጿል።
ቢያንስ አንድ የሚያውቀው ታጋች መሞቱን እና ቀሪዎቹ ምን አንዳጋጠማቸው ማወቅ እንዳልቻለ ጨምሮ ገልጿል።
ስደተኞችን በሊቢያ በኩል ወደ ሜዲትራኒያን የባሕር ዳርቻ ያሻግራሉ የተባሉት ታጣቂዎች ከኢራቅ ኩርድ ካመጣቸው ደላላ፣ ኖህ አሮን ጋር በክፍያ አለመስማማታቸውን ተናግረዋል።
አሮን በፈረንሳይ በቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ ሕገወጥ ገንዘብን ወደ ሕጋዊ ሥርዓት ለማስገባት በመሞከር እና በሕገወጥ የሰው ዝውውር የ10 ዓመት እስር ተፈርዶበታል።
ቢቢሲ ስደተኞቹ ስለገጠማቸው ማወቅ የቻለው ባለፈው ወር በቁጥጥር ሥር የዋለው ሕገወጥ የሰው ዝውውር ላይ የተሰማራው ካርዶ ጃፍ ላይ የምርመራ ዘገባ በሚሠራበት ወቅት ነው።
ሁለቱ ሕገወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች በጥምረት ይሠሩ እንደነበር ይታመናል።
በቻተም ሐውስ መረጃ መሠረት ሁለቱም "በርካታ ሕገወጥ የሰው ዝውውር መረብ ከሚንቀሳቀስበት" በኢራቅ ኩርዲስታን ክልል ራንያ ከተማ የመጡ ናቸው።
በየካቲት ወር የቢቢሲ የምርመራ ዘገባ ቡድን በራንያ ለሚኖሩ ሰዎች ስለ ጃፍ ጥያቄዎችን ሲያቀርብ አንድ ግለሰብ ልጃቸው ከታገቱት ሰዎች መካከል እንደሚገኝ ተናገሩ።

ግለሰቡ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የአሮን ሕገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ቡድን ልጃቸውን ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ለመውሰድ በሺዎች የሚቆጠር ዶላር ማስከፈላቸውን እና በሰሜን አፍሪካ አድርገው በሜዲትራኒያን በኩል ወደ አውሮፓ እንደሚጓዙ እንደተነገራቸው ገልጸዋል።
በተባበሩት መንግሥታት አማካሪ የሆነው እና የሕወገጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ጥናት ያደረገው አንቶኒ ደንከርሊ ጉዞው "በአገሪቱ ውስጥ ሙሉ ቁጥጥር የሌለው መንግሥት ባለባት" ሊቢያ በኩል የሚደረግ መሆኑን ይናገራል።
የሊቢያ ሰፊ ግዛት በተቀናቃኝ ኃይሎች የተያዘ ሲሆን፣ ሕገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች መረብ ከቡድኑ ጋር በትብብር ይሠራል።
ቢቢሲ በ2025 ክረምት ላይ በርካታ ስደተኞች ከኢራቅ ኩርዲስታን ወደ ሊቢያ ተወስደው ጥብቅ ጥበቃ በሚደረግለት ቅጥር ግቢ ውስጥ መቀመጣቸውን ማወቅ ችሏል።
ታጣቂዎች አሮን ቀደም ሲል በነበረው ስምምነት መሠረት ሳይከፍል ስለቀረ በሚል በእያንዳንዱ ታጋች 5000 ዶላር ጠይቀዋል። የታጋቾቹ ቤተሰቦች ገንዘቡ በፍጥነት የማይከፈሉ ከሆነ የልጆቻቸውን "ኩላሊት" እንደሚያወጡ አስፈራርተዋል።
ሊቢያውያኑ የተጎሳቆሉ ታጋቾች ፎቶ እና ቪዲዮ ለቤተሰቦቻቸው ልከዋል። አንድ ወጣት ወደ ዶክተር ተወስዶ ኩላሊቱ እንደሚወጣ ሲነገረው በቪዲዮው ላይ ይታያል።
በራንያ የሚኖር አንድ ሰው ቤተሰቡን ከታጋቾች መዳፍ ለማስለቀቅ ገንዘብ መክፈሉን ይናገራል።
ልጁ በጥር ወር የኢራቅ መንግሥት ወደ አገሩ ከወሰዳቸው 110 ሰዎች መካከል አንዱ ነው።
ነገር ግን ልጁ በታጋቾች እጅ ሳለ የላከለት ፎቶ የሚያሳየው አባት፣ በሰውነቱ ላይ ጠባሳ መኖሩን የሚያሳይ ሲሆን፣ ምናልባት የአካል ክፍሉን ሲያወጡት የተፈጠረ ሊሆን ይችላል ሲል ጥርጣሬውን ይናገራል።
ቢቢሲ ግለሰቡን ካነጋገረ በኋላ በርካቶች ተመሳሳይ ፎቶ ይዘው ቀርበዋል።
ቢቢሲ አንዱን ፎቶ በዩናይትድ ኪንግደም ለሚገኝ ባለሙያ ያሳየ ሲሆን፣ ጠባሳው በኩላሊት ቀዶ ሕክምና ወቅት ከሚፈጠር ጋር ተመሳሳይ መሆኑን አረጋግጧል።
ነገር ግን የግለሰቦቹ ኩላሊት ወጥቷል የሚለውን ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አልተቻለም።
በሊቢያ በኩል የሚያቋርጡ ስደተኞች እገታ እንደሚፈጸምባቸው በተለያየ ጊዜ ተዘግቧል።
በሊቢያ የሚንቀሳቀሱ የወንጀል ቡድኖች ውስን የመንግሥት ቁጥጥር ያለባቸው እንደ ደንከርሌይ አካባቢዎችን ይጠቀማሉ።
ይህም ምርመራ ለማድረግ እና የወንጀል ክስ ለመመሥረት አስቸጋሪ አድርጎታል።
በርካታ ታጋቾች አሁን ተለቅቀዋል። አንዳንድ ቤተሰቦች ወዲያውኑ የተጠየቁትን የማስለቀቂያ ገንዘብ የከፈሉ ቢሆንም የኩርድ ባለሥልጣናት ግን ሌሎች ታጋቾች የአካል ክፍላቸውን በመስጠት ክፍያውን መፈጸማቸውን ይጠረጥራሉ።
ቢቢሲ ወደ ራንያ የተመለሱ የተወሰኑ ሰዎችን አነጋግሯል።

የፎቶው ባለመብት, Instagram
አንድ ተመላሽ የደረሰበትን ስቅይት ቁስሉን እያሳየ እግሩን እያቃጠሉ እንደደበደቡት ተናግሯል።
ሌላ የ16 ዓመት ታዳጊ ደግሞ ከ178 ሰዎች ጋር በጠባብ ማጎሪያ ውስጥ መቆየቱን ተናግሮ "ለስድስት ወር ፀሐይ አላየንም" ብሏል።
በጣም ከመጨናነቁ የተነሳ ሁሉም መተኛት የሚችለው ተቀምጦ ብቻ ነው የሚለው ይህ ታዳጊ፣ አንድ መፀዳጃ ቤት እንደሚጠቀሙ እና ረዥም ሰዓት በንጽህና ቤቱ ገብቶ መቆየት ግርፋት እንደሚያስከትል አስረድቷል።
በዕለት አንድ ዳቦ ብቻ የሚሰጣቸው መሆኑን የሚናገሩት የታጋቾች ቤተሰቦች ይህም የሚሆነው ለአጋቾቹ ተጨማሪ ገንዘብ ከከፈሉ ብቻ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
እንደ የኩርድ ክልላዊ መንግሥት አገር ውስጥ ሚኒስቴር ሄምን ሜራኒ ከሆነ ምንም እንኳ አደጋ ያለው ቢሆንም ከኢራቅ ኩርዲስታን ወደ አውሮፓ የሚደረገው ሕገወጥ ጉዞ አሁንም አልቆመም።
የተመለሱ ስደተኞች በጉዟቸው ስላጋጠማቸው አሰቃቂ ነገር ለቤተሰቦቻቸው እና ለወዳጆቻቸው በመናገር ተመሳሳይ ስደትን እንዳይሞክሩ እንዲመክሯቸው ይጠይቃሉ።
አንድ አባት ልጃቸው ኩላሊቱን ለማውጣት በሚሞክሩበት ወቅት እንደሞተ እንደሚጠረጠሩ አክለው ይናገራሉ።
በራንያ በተካሄደ የልጁ ቀብር ላይ ሁለት የወንድሞቻቸው ልጆች ወደ አውሮፓ ለመሄድ ጉዞ መጀመራቸውን መረዳቱን ሚኒስትሩ ጨምረው ተናግረዋል።
ሜራኒ "የዚህ ጉዳይ አስከፊው ገጽታ አለመማራችን ነው" ይላሉ።















