በታይላንድ የ17 ዓመት ሴት አስከሬን በሻንጣ መገኘቱን ተከትሎ አውስትራሊያዊ ተጠርጣሪ ተከሰሰ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በሻንጣ የተከተተ የ17 ዓመት ሴት አስከሬን ታይላንድ ውስጥ መገኘቱን ተከትሎ አውስትራሊያዊው ግለሰብ በግድያ እንደሚከሰስ ተገለጸ።
የፓታያ ፖሊስ እንዳለው ቱንቻኖክ ዶናሆማላ የተባለችው ሴት አስከሬን ሻንጣ ውስጥ "ታጭቆ" በባቡር ሐዲድ አካባቢ ተጥሎ ተገኝቷል።
የታይላንድ ፖሊስ እንዳስታወቀው ሳይመን ፒተር ካርመን የተባለው ተጠርጣሪ "ለመሸሽ በዝግጅት ላይ ሳለ" በባንኮክ ሱቫርናቡሚ አውሮፕላን ማረፊያ በቁጥጥር ሥር ውሏል።
ተጠርጣሪው ድረጊቱን እንዳልፈጸመ ተናግሯል። በፖሊስ ከተያዘ በኋላ ለሟቿ ቤተሰቦች ባስተላለፈው መልዕክት "ልጃቸው በገጠማት ነገር አዝኛለሁ። ከቁጥጥሬ ውጪ ነው" ብሏል።
የፓታያ ከተማ ፖሊስ እንዳለው የ17 ዓመቷ ሴት መጥፋቷ ሪፖርት የተደረገው ባለፈው አርብ ነበር።
ተጠርጣሪው ሐሙስ ዕለት ከሟቿ ጋር ወደ መኖሪያ ሕንጻ ሲገባ የሚያሳይ የደኅንነት ካሜራ ቪድዮ መገኘቱን ፖሊስ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ምሽት ላይ ከሕንጻው "ግዙፍ ሻንጣ" ይዞ ብቻውን ሲወጣም በቪድዮው ታይቷል።
ሻንጣውን በሞተር ሳይክል ጭኖ ወደ ባቡር ሐዲድ መስመር እንደተጓዘም ተገልጿል።

የፎቶው ባለመብት, Pattaya Police
ፖሊስ ከከተማው 150 ኪሎሜትር ከሚርቀው አውሮፕላን ማረፊያ ተጠርጣሪውን ይዞ ያሰረው ቅዳሜ ዕለት ነው።
የታዳጊዋ አስከሬን በሻንጣ ውስጥ የተያዘው ተጠርጣሪው ከተያዘ ከ15 ደቂቃ በኋላ ነበር።
ተጠርጣሪው የቀረበበትን የግድያ፣ አስከሬን ሰውሮ የማጓጓዝ እና ታዳጊን ለወሲብ ድርጊት የመውሰድ ክሶች አስተባብሏል። ድርጊቱ ራስን የመከላከል እንደሆነም ተናግሯል።
ግለሰቡ ከታዳጊዋ ጋር ወሲብ ለመፈጸም 30 ዶላር ለመክፈል ተስማምቶ ወደ መኖሪያ ሕንጻው ከሄዱ በኋላ ግማሹን ገንዘብ ብቻ እከፍላለሁ በማለቱ አለመግባባት እንደተፈጠረ የመገናኛ ብዙኃን ዘገባ ይጠቁማል።
የታይላንድ ፖሊስ ለአውስትራሊያ ብሔራዊ ጣቢያ እንደገለጸው፤ ተጠርጣሪው ተኝቶ ሳለ ታዳጊዋ "ከክፍሉ መጥፋቷን" ተናግሯል።
ለቤተሰቦቿ ባስተላለፈው የቪድዮ መልዕክት "እንዳዘናችሁ እና እንደተበሳጫችሁ አውቃለሁ። እኔም ተመሳሳይ ስሜት ተሰምቶኛል። እባካችሁ ሌሎች ሴቶች እንዲጠነቀቁ ንገሯቸው" ብሏል።
የፓታያ ከተማ ፖሊስ ኃላፊ ኮለኔል አንክ ስራታሆንጋዮ "በትግል ወቅት የሚፈጠር የጥፍር ቡጭራት በሰውነቱ ላይ ቢገኝም እንደገደላት አላመነም" ሲሉ ለኤቢሲ ተናግረዋል።
በጥፍሮቹ ሥር ስለተገኘው ምልክት ሲጠየቅ "ሸረሪት ይሆናል፤ ሁሌ እዚያ ጋር ይይዙኛል" ሲል ምላሽ ሰጥቷል።
የታዳጊዋ ወላጆች ለኤቢሲ እንደተናገሩት ትኖር የነበረው ከአባቷ እና እንጀራ እናቷ ጋር ነበር።
'ኬክ' በሚል ቅጽል ስም የምትታወቀው ታዳጊዋ ወደ ፓታያ ከተማ ከጓደኞቿ ጋር ለመዝዝናት መሄዷ ተገልጿል።
አባቷ በልጃቸው ሞት "ጥልቅ ሐዘን" እንደተሰማቸው ገልጸዋል።
"ልጄ እናት የላትም። የምትፈልገውን ለማግኘት በራሷ መጣር ነበረባት። እኔንም ታግዘኝ ነበር" ብለዋል።
የእንጀራ እናቷ "በጣም ፈርተን ነበር። የፈራነው ደረሰ። ብዙ በማልቀሳችን ዓይናችን አብጧል። እንዲገደል እፈልጋለሁ። ልመታው እችል እንደሆነ ፖሊስን ጠይቄያለሁ" ሲሉ ተናግረዋል።
ተጠርጣሪው በግድያ ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ በሞት ሊቀጣ ይችላል።















