በአርሲ ዞን በአራት ዓመት ውስጥ "458 ሰዎች ተገድለዋል" - ኢሰመጉ

የፎቶው ባለመብት, Mahibere Kidusan Broadcast Service
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ውስጥ ባለፉት አራት ዓመታት በተፈጸሙ ጥቃቶች "458 ሰዎች" ሲገደሉ፤ "38 ነዋሪዎች ያሉበት ሁኔታ አይታወቅም" አለ።
መንግሥታዊ ያልሆነው የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት ኢሰመጉ፣ ይህንን ያለው "በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ አርሲ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች በተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን" በተመለከተ እሁድ ሐምሌ 19/2018 ዓ.ም. ባወጣው ሪፖርት ነው።
ባለ 37 ገጹ ሪፖርት፣ ከ2014 እስከ እስካለፈው ግንቦት 24/2018 ዓ.ም. በዞኑ "የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን" የዳሰሰ እንደሆነ ተገልጿል።
ሪፖርቱ እንደሚያስረዳው፤ የኢሰመጉ ባለሙያዎች ከመጋቢት 3 እስከ 9 ቀን በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች ተገኝተው ምርመራ አድርገዋል። ባለሙያዎች ምርመራ አካሄደውባቸዋል ከተባሉ ዘጠኝ ወረዳዎች መካከል ሽርካ፣ መርቲ፣ ሆንቆሎ ዋቤ እና አሰኮ ይገኙበታል።
የምርመራ ባለሙያዎች በእነዚህ አካባቢዎች "ከሟች ቤተሰቦች፣ በጥቃቱ ጉዳት ከደረሰባቸው ሰዎች እና ከዐይን ምስክሮች ጋር" ቃለ መጠይቅ እንዳደረጉ ሪፖርቱ ላይ ሰፍሯል።
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን "አርሲ ሀገረ ስብከት ቤተ ክህናት እና ከወረዳዎች ቤተክህነቶች" የተገኙ መረጃዎች እንዲሁም "አስረጂ ሰነዶች" የምርመራው አካል እንደሆኑም ተጠቅሷል።
በአርሲ ዞን የተመዘገቡት የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መፈጸም የጀመሩት ከአራት ዓመት በፊት መሆኑን የሚገልጸው ሪፖርቱ፤ "በአካባቢው የሚገኙ የታጠቁ ቡድኖች የአካባቢው ማኅበረሰብ ላይ ሃይማኖትን መሠረት ባደረገ መልኩ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ላይ" ጉዳት ማድረሳቸውን ያትታል።
በሪፖርቱ መሠረት በእነዚህ ዓመታት ውስጥ "ከፍተኛ የሆነ ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመት፣ አስገድዶ መሰወር፣ እገታ" ተፈጽሟል። "አብያተ ክርስቲያናት ላይ ዝርፊያ" መድረሱን እንዲሁም ታጣቂዎቹ "በርካታ ቤቶችን ማቃጠላቸውን" አክሏል።
የኢሰመጉ ሪፖርት ከ2014 ዓ.ም. አንስቶ በአርሲ ዞን ዘጠኝ ወረዳዎች ውስጥ "458" ሰዎች መገደላቸው ይገልጻል። ከዚህ ውስጥ አራቱ "የአካባቢው ነዋሪዎች የሆኑ የመንግሥት ታጣቂዎች (ሚሊሻ)" እንደሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን ቀሪዎቹ ሟቾች "ንጹኃን" እንደሆኑ ሰፍሯል።
የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ከሟቾቹ ውስጥ የ349 ያህሉን ስም፣ የተገደሉበት ስፍራ እንዲሁም ጥቃቱ የደረሰበትን ዕለት በሪፖርቱ አካትቷል። በጥቃት የተገደለች የሰባት ወር ሕጻንን ጨምሮ የ67 ሰዎች ፎቶግራፍም ይፋ አድርጓል።
ሪፖርቱ ከግድያ በተጨማሪ "የታጠቁ አካላት ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ እገታ" እንደፈጸሙ በመግለጽ ይከስሳል። የማስለቀቂያ ገንዘብ ከተከፈለ በኋላ ነጻ የወጡ ሰዎች ቢኖሩም "አንዳንዶቹ" ክፍያው ተፈጽሞም መገደላቸውን ያነሳል።
ሌሎች ደግሞ ከታገቱ በኋላ "የት እንዳሉ እንደማይታወቅ" ጠቅሷል። "ታግተው ያሉበት ሁኔታ የማይታወቅ" በሚል የተገለጹ 38 ሰዎች ስም ዝርዝር ሪፖርቱ ውስጥ ተካትቷል።
በተጨማሪም፤ እነዚህ ጥቃቶች "ስጋት ያሳደሩባቸው" ነዋሪዎች "ወደ አጎራባች አካባቢዎች ተሰደው በከፍተኛ ችግር ውስጥ" እንደሚገኙ ሰፍሯል።
በአርሲ ዞን ውስጥ የተፈጸሙት ጥቃቶች "ማንነትንና ሃይማኖትን መሠረት ያደረጉ" ሲል የገለጻቸው ኢሰመኮ፤ መንግሥት ፈጻሚዎቹን በሕግ ተጠያቂ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል።
የፌዴራል እና የኦሮሚያ ክልል መንግሥታት ከእነዚህ ጥቃቶች ጋር በተያያዘ "ሆነ ብለውም ሆነ በቸልተኝነት የሕግ ግዴታቸውን ያልተወጡ የመንግሥት የፀጥታ እና የአስተዳደር አካላትን በአስቸኳይ ለሕግ አቅርበው ተጠያቂ እንዲያደርጉ" ጠይቋል።
የክልሉ መንግሥት የተፈናቀኑ ነዋሪዎች "በፈቃደኝነት፣ በክብር እና በደኅንነት ወደ ቀያቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ እንዲያመቻች" ጥሪ አቅርቧል።
እንዲሁም የክልሉ መንግሥት በታጣቂዎች "የሚደርሱትን የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መቆጣጠር ካልቻለ" የፌደራል መንግሥት "ጣልቃ በመግባት የንጹኃን ዜጎችን በሕይወት የመኖር መብት እንዲያስጠብቅ" አሳስቧል።

የፎቶው ባለመብት, Mahibere Kidusan Broadcast Service
በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን የሚገኙ ወረዳዎች በተለያዩ ጊዜያት ተደጋጋሚ ጥቃቶችን አስተናግደዋል። በዚህ ዓመት ቢያንስ በጥቅምት እና ግንቦት ወራት ብቻ በተፈጸሙ ጥቃቶች ነዋሪዎች ተገድለዋል።
የፌደራል መንግሥት እና ኦሮሚያ ክልል በጥቃቶቹ ተጠያቂ የሚያደርጉት "ሸኔ" በማለት የሚጠሩትን ታጣቂውን ቡድን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ነው። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንም ግንቦት ላይ ለተፈጸመው ጥቃት "በተለምዶ ኦነግ ሸኔ" የሚጠራውን ሲል የገለጸውን ይህንኑ ታጣቂ ቡድን ተጠያቂ አድርጓል።
ቡድኑ በአንጻሩ ጥቃቶቹን የሚፈጽሙት መንግሥት በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት "ስም ያሰማራቸው ታጣቂዎች ናቸው" በማለት ይወነጅላል
በተጨማሪም የዞኑ የሚደርሱት ጥቃቶች "ማንነት ተኮር" የመሆን አለመሆናቸው ጉዳይ ሌላ የክርክር ምንጭ ነው። ከጥቃቱ የተረፉ ነዋሪዎች ቤተ ክርስቲያናት ላይ ጭምር ጉዳት መድረሱን በማንሳት "ማንነት ተኮር" መሆኑን ይግጻሉ።
ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤት ክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስም በጥቅምት እና ሰኔ ወራት የተፈጸሙ ጥቃቶችን ተከትሎ ባወጧቸው መግለጫዎች የእምነቱ ተከታዮች መገደላቸውን አመልክተዋል።
ጥቅምት ላይ የተፈጸመውን ጥቃት የሚያጣራ ኮሚቴ ያሰማራው የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በበኩሉ ኅዳር ላይ ይፋ ባደረገው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ድርጊቱ የተፈጸመው "የአንድ የሃይማኖት ተከታይ እና አገልጋዮች ላይ እንዳልሆነ" ገልጿል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በበኩሉ ግንቦት ላይ "በኦነግ ሸኔ አማጽያን በንጹኃን ዜጎች ላይ በተለይም በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ" የተፈጸሙት ጥቃቶች ዓላማቸው "በኢትዮጵያ አለመረጋጋትን እና የምርጫ መስተጓጎልን መፍጠር" እንደሆነ ገልጿል።















