አቢጋይል ብርሃነ፡ በኬምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ታሪክ የሠራችው ትውልደ ኤርትራዊት የኤሮስፔስ ኢንጂነሪንግ ተመራማሪ

አቢጋይል ብርሃነ

የፎቶው ባለመብት, Abigail Berhane

የምስሉ መግለጫ, አቢጋይል ብርሃነ በምረቃዋ ዕለት
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

ከሕጻንነቷ ጀምሮ ሰማይ መጨረሻ እንደሌለው የተገነዘበች ትመስላለች፤ በከፍተኛ የራስ መተማመን ትልቅ ህልም እያለመች ነው ያደገችው።

ባለፉት ዓመታትም የተለያዩ ሽልማቶች ለመቀበል እና የዩናይትድ ኪንግደም ንጉሥን ጨምሮ ከበርካታ የዓለማችን ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ጋር ለመገናኘት ችላለች።

አቢጋይል ብርሃነ በቅርቡ ከእውቁ ኬምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ በዶክትሬት ዲግሪ ተመርቃለች። በዚህም ከዊትል ላቦራቶሪ በከፍተኛ አካዳሚያዊ መዓርግ የተመረቀች የመጀመሪያዋ ጥቁር ሴት ናት።

ከልጅነቶ አንስቶ ለኢንጅነሪግ ዘርፍ ልዩ ፍላጎት ያደረባት አቢጋይል "ከልጅነቴ ጀምሮ ፊዚክስ፣ ሳይንስ እና ሒሳብ እወድ ነበር" በማለት የ11 ክፍል ተማሪ እያለች ያጋጠማት አንድ ዕድል ቀጣዩ ጉዞዋን ያቀና እንደነበረ ትናገራለች።

ከትምህርት ቤት ጓደኞቿ ጋር ስዊትዘርላንድ በሚገኘውን ትልቁ የፊዚክስ ቤተ ሙከራ (ላቦራቶሪ) ጎበኘች። ይህም በትምህርቷ ላይ ተጨማሪ መነቃቃት አሳደረባት።

ላቦራቶሪው በፈረንሳይ እና ስዊትዘርላንድ ድንበር አቅራቢያ ከምድር በታች የተገነባ ከ50 እስከ 175 ሜትር ጥልቀት ያለው ሲሆን፣ በዓለም ላይ ትልቁ ሃይድሮ ኮላይደር የተባለው ታላቅ ሳይንሳዊ ሙከራ የሚካሄድበት ቦታ ነው።

"ወደዚያ ስሄድ እና የተዘረጉትን የኤሌክትሪክ ገመዶች ስመለከት፣ መሐንዲስ መሆን ምን ያህል እንደሚያስደስት ማሰቤን ትዝ ይለኛል።"

በስዊትዘርላንድ የተፀነሰውን ህልሟን እውን ለማድረግ በክረምት ወቅት ተጨማሪ የፊዚክስ፣ የሒሳብ እና የኮዲንግ ኮርሶችን ለመውሰድ ወሰነች።

በለንደን የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ ከፍተኛ ውጤት አስመዝግባ ወደ ዩኒቨርሲቲ ገባች።

በእንግሊዝ የባሕር ዳርቻ ወደምትገኘው ውቧ ብራይተን ከተማ በመሄድም በሳሴክስ ዩኒቨርሲቲ ሜካኒካል ኢንጂነሪንግ አጠናች፣ የመጀመሪያ ዲግሪዋንም አገኘች።

ሆኖም "ስለ ፍሉድ ሜካኒክስ ያልተመለሱ ጥያቄዎችን" ይዛ ከሳሴክስ መውጣቷ ትናገራለች።

'ፍሉድ ሜካኒክስ' በማንኛውም ወለል ላይ የፈሳሽ እንቅስቃሴ ባህሪን የሚያጠና መስክ ሲሆን፣ የኤሮስፔስ ኢንጂነሪንግ ትልቅ ክፍል ነው።

ይህንን ችግር ለመፍታት ተጨማሪ የማስተርስ እና የዶክትሬት ጥናቶችን ለመከታተል በመወሰን ዕድሎችን መፈለግ ጀመረች።

ለከፍተኛ ትምህርት ሙሉ ነፃ የትምህርት ዕድል ወደሰሚጥ 'ሲዲቲ' (Centres for Doctoral Training) ያቀረበችው ጥያቄ ተቀባይነት በማግኘትም ምኞቷ ተሳክቶ ወደ ዩኒቨርሲቲ ተመለሰች።

ታዋቂው የትላልቅ አውሮፕላን ሞተሮች አምራች የሆነው ሮይስ-ሮልስ (የማስተርስ እና የዶክትሬት) ትምህርቶቿን እንደሚደግፍ ማወቋ በጣም አስደስቷታል። ምክንያቱም በአቪዬሽን ኢንዱስትሪው የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች ለመረዳት እና መፍትሄዎችን ለማግኘት ዕድል ስለሰጣት።

አቢጋይል ብርሃነ

የፎቶው ባለመብት, Abigail Berhane

የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ሕይወት

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አቢጋይልን ያገኘናት ከለንደን ደቡብ ምሥራቅ 80 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው ተማሪዎች፣ መምህራን እና የዩኒቨርሲቲ ሠራተኞች በብዛት በሚገኙባት ኬምብሪጅ ከተማ ነው።

የከተማዋ ማኅበራዊ፣ ባህላዊ እና ኢኮኖሚያዊ መሠረት የተገነባው በዓለም ላይ ግንባር ቀደም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አንዱ በሆነው በኬምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ላይ ነው።

ብቁ ተማሪዎች በማስመረቅ ከሚታወቀው ዩኒቨርሲቲ መመረቋ በራሱ ትልቅ ስኬት ነው።

በ1209 የተመሠረተው ዩኒቨርሲቲው ከኦክስፎርድ እና ሃርቫርድ ጋር እኩል ሲሆን፣ አይዛክ ኒውተን፣ ቻርለስ ዳርዊን እና ስቴፋን ሃውኪንግን ጨምሮ ብዙ ሊቃውንትን እና መሪዎችን አፍርቷል።

አቢጋይል ግን "ፍራንክ ዊትልን እና አላን ቱሪንን ያፈራው ዩኒቨርሲቲ" ማለት ይቀናታል።

ፍራንክ ዊትል በ1996 የሞተው የቀድሞ አብራሪ እና በጄት ሞተር ፈጠራ ውስጥ ግንባር ቀደም ሚና ከተጫወቱ ዕውቅ የአውሮፕላን መሐንዲሶች አንዱ ነበር። አቢጋይል በስሙ በሚጠራው የምህንድስና ክፍል አካል የሆነውን የዊትል ላቦራቶሪ ነው ነው የተመደበችው።

"ትንሽ የኢምፖስተር ሲንድሮም [የራስን ችሎታ መጠራጠር] ስሜት ተሰምቶኝ ነበረ፣ ነገር ግን ቀደም ሲል ያሳካኋቸውን ታላላቅ ነገሮች በማስታወስ ተቀባይነት ለማግኘት አስቸጋሪ ሂደት ውስጥ ማለፍ ግድ ስለሆነ ይህም በራሱ ማለፍ ቀላል አልነበረም" ትላለች።

ስኬት የሚለካው የስኬት ጫፍ ላይ ከመድረሱ በፊት ትናንሽ ድሎችን በማስመዝገብ መሆኑን ታምናለች።

"የዶክትሬት ዲግሪ ከባድ ሥራ የሚጠይቅ ሊሆን ይችላል፣ ግን ይህ በጣም ጥሩ ምርምር እንዳደርግ የሚረዳ ነው" የምትለው ዶ/ር አቢጋይል "ውጤታማ ሥራ ለመሥራት በቂ እረፍት መውሰድ አስፈላጊ መሆኑን" ገልጻለች።

በእረፍት ጊዜዋም የተለያዩ አገራትን መጎብኘት ታዘወትራለች፤ ቡና ስለምትወድ ወደ ካፌዎች መሄድም ከተጨናነቀ እና ከከባድ ሕይወት ለመደበቅ እና እንደገና ለመመለስ ከሚያስችሏት ዘዴዎች አንዱ ነው።

አቢጋይል ብርሃነ

የፎቶው ባለመብት, Abigail Berhane

ዊትል-ላቦራቶሪ፡ 'ብቸኛ ጥቁር የፒኤችዲ ተመራቂ'

በአውሮፓውያኑ 1973 በፍራንክ ዊትል በይፋ የተመረቀው ይህ ላቦራቶሪ በቅርብ ዓመታት ውስጥ አስፈላጊ የሆኑ የአቪዬሽን ተቋማትን እና መሪዎችን ትኩረት ስቧል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት የዩናይትድ ኪንግደም ንጉሥ ተቋሙን ጎብኝተዋል። ቻርለስ ሳልሳዊ የአየር ንብረት ለውጥን በመቀነስ እና አካባቢን በመጠበቅ ረገድ የላቀ ቴክኖሎጂ ስለሚጫወተው ሚና ባባላቸው ራዕይ ምክንያት ላቦራቶሪውን አራት ጊዜ ጎብኝተዋል።

በዘመናዊው ላቦራቶሪ ውስጥ የተካሄደው ምርምር ዓላማ አየርን እየበከሉ ያሉት የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ሞተሮች ንፁህ ኃይልን በመጠቀም ከብክለት የጸዳ የአየር ንብረት መፍጠር የሚቻልበትን ሁኔታ መፍጠር ነው።

ይህንን ለማድረግ ትላልቅ የአውሮፕላን ሞተሮች መሻሻል እና እንደ አዲስ መሠራት አለባቸው፣ የዶ/ር አቢጋይል ምርምር የኢንዱስትሪውን እና የንጉሡን ታላቅ ራዕይ ለማሳካት ያለመ ነው።

ከዚህ ዩኒቨርሲቲ በሁለተኛ እና በሦስተኛ ዲግሪ መመረቅ የቻለችው ብቸኛ ጥቁር ሴት መሆኗ "ትልቅ ክብር ነው፣ ነገር ግን ኃላፊነትም ጭምር ነው። ተመሳሳይ አስተዳደግ ካላቸው ትውልዶች ድንቅ ምርምር ለማድረግ ምሳሌ ይሆናል።"

በዓለም አቀፍ ደረጃ፣ በአቪዬሽን ምህንድስና ወይም 'በአየር እና በኤሮስፔስ' የሴቶች ተሳትፎ ከወንዶች ጋር ሲነጻጸር ከ9 እስከ 15 በመቶ አይበልጥም።

በቅርቡ ከተመረቀች በኋላ፣ የ'ፖስት-ዶክቶራል' ሥራ በማግኘት ሮልስ-ሮይስ ለአውሮፕላን ሞተሮች ከፍተኛ ቅድሚያ የሚሰጠውን የኤሮ-ኢንጂን ተርባይን ኤሮዳይናሚክስ ተግዳሮትን ለመፍታት ምርምር ስታደርግ ቆይታለች።

ሴቶች በቴክኖሎጂ፣ በፈጠራ እና በሳይንስ

በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በኢንጂነሪንግ እና በሂሳብ ዘርፎች የሴቶች ውክልና ውስን ስለመሆኑ ሲነገር ቆይቷል።

ለምሳሌ በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ በዘርፉ የሚሳተፉ ሴቶች ቁጥር ከ27 በመቶ አይበልጥም። በአየር ምህንድስና ዘርፍ ያለው የሴቶች የተሳትፎ ደረጃ እጅግ በጣም አዲስ ነው።

"በርካታ ተግዳሮቶች አሉ፣ ነገር ግን አንዱ በሳይንስ እና በሂሳብ ዘርፎች ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ በዋናነት በሶፍትዌር ብቻ የተወሰነ መሆኑ ነው፤ ስለዚህ በሃርድዌር ውስጥ የሚሠሩ አርአያ የሆኑ ብዙ ሴቶች የሉም። በተግባራም የራሱ የሆኑ ተግዳሮቶች አሉት። ትላልቅ ማሽኖዎችን ስንመለከት የሚይደፈሩ ነው የሚመስለን። ነገር ግን ይህም ሴቶች ማድረግ እንደሚችሉ ማወቅ አለባቸው።

"እኔ አይደለም ትላልቅ ማሽነሪዎች፣ ትናንሽ መሳሪያዎችም እየተጠቀምኩ አላደግኩም። የዶክትሬት ዲግሪዬን ስጀምር ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ያየኋቸው" በማለት የኤሮኖቲክስ ምህንድስና ቴክኖሎጂዎች ዕውቀቷ በጊዜ ሂደት እየዳበረ መሄዱን ትናገራለች።

ሁኔታውን በቅርበት እና በተግባራዊ መንገድ የመረዳት ዕድል ስላገኘች፣ አቢጋይል በዘርፉ ውስጥ ዝቅተኛ ውክልና ያላቸውን ሴቶችን ጨምሮ ማኅበረሰቦችን እንዲሁም ተማሪዎችን ለማበረታታት በሚደረጉ ተነሳሽነቶች ላይ በመሳተፍ ተማሪዎችን ወደ ላቦራቶሪዋ በመጋበዝ በምትመራቸው ጥናቶች ፈጠራን ለማበረታታት በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ግንባር ቀደም ሆና ስትሠራ ቆይታለች።

የኬምብሪጅ ተመራቂዎች

የፎቶው ባለመብት, Abigail Berhane

"በምህንድስና ዘርፍ ብዝሃነትን ማበረታታት አስፈላጊ ነው። ይህም በፍጥነት መሳካት አለበት" ትላለች።

ለሌሎች እንደ እሷ ያሉ የማስተርስ ወይም የዶክትሬት እድሎችን በሳይንስ እና በሒሳብ መስኮች ከዚያም በላይ ለማግኘት ማመልከቻ ከማስገባታቸው በፊት የትምህርት ተቋማትን ድረ-ገጾች እንዲመለከቱ እና ከማኅበራዊ ሚዲያ መረጃ ለማግኘት ጥረት እንዲያደርጉ ትመክራለች።

"ለዶክትሬት ጥናቴ ማመልከቻ ከማቅረቤ በፊት የረዳኝ ነገር በዘርፉ ውስጥ ካሉ ፕሮፌሰሮች እና አስተማሪዎች ጋር መገናኘት እና ሱፐርቫይዘር መሆን የሚችሉ ሰዎችን ማግኘቴ ነበር።"

"ይህንን በጣም ጠቃሚ ሆኖ አግኝቼዋለሁ ምክንያቱም ወደፊት ልሳተፍበት የምችል ጥናት እንዳላቸው ለማወቅ ዕድል ፈጥሮልኛል" በማለት ያለፈችበትን ሂደት አጋርታለች።

ኤርትራ ውስጥ ተወልደው ያደጉት እና ለኤርትራ ነፃነት በተደረገው ጦርነት ወቅት የተሰደዱት ወላጆቿ ለስኬቷ ቀዳሚ አርአያዎቿ ናቸው።

"አባቴ የዶክትሬት ዲግሪ ስላለው ዕድለኛ ነበርኩ። የአምስት ዓመት ልጅ ሳለሁ የዶክትሬት ዲግሪ ምን ማለት እንደሆነ አውቅ ነበር። እናቴም የሒሳብ ሊቅ ነበረች። ሁልጊዜ የቤት ሥራዬን ትረዳኝ ነበር። ነገሮችን የማስረዳት ትልቅ ችሎታ አላት" በማለት የእናቷን ትላለች።

ሴቶች በኤርትራ ነፃነት ትግል ውስጥ ስለ ነበራቸው ሚና እየሰማች ማደጓም፡ ሴቶች በፆታቸው ምክንያት ሊገለሉ እንደማይችሉም ለመገንዘብ አስችሏታል።

ሽልማቶች እና እውቅና

አቢጋይል በአንጻራዊ ሁኔታ አጭር እና ስኬታማ በሆነ ጉዞዋ በርካታ ሽልማቶችን አሸንፋለች።

አንደኛው የኤሚሊያ ኤርሃርት ፌሎውሺፕ ሲሆን፣ የዶክትሬት ዲግሪ ለመከታተል ለሚፈልጉ ሴቶች ብቻ የሚሰጥ የገንዘብ ሽልማት ነው።

አሜሪካዊቷ ኤርሃርት በ1932 የአትላንቲክ ውቂያኖስን ላይ በአውሮፕላን ካቋረጡ የመጀመሪያ ሴት አብራሪዎች መካከል አንዷ ነበረች። ፍረድ ኑናን ከተባለ ረዳቷ ጋር በምድር ዙሪያ ስትዞር በሰላማዊ ውቅያኖስ ከጠፉ በኋላ አልተገኙም።

"አሚሊያ ኤርሃርት ከማደንቃቸው የስኬት ምልክቶች አንዷ ናት፣ እና ለእኔ ጠንካራ አርአያ ሆናለች" ትላለች አቢጋይል።

አቢጋይል በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ለጥቂት ጎበዝ ተማሪዎች ብቻ የሚሰጠውን 'ሲኤስኤአር' ሽልማት አሸንፋለች።

ጥናቷ የሮልስ-ሮይስ ሞተሮችን እንደሚያሻሽል እና እንደሚያዳብር ይጠበቃል።

ዶ/ር አቢጋይል ሌሎች ሽልማቶችን እና ማበረታቻዎችን እንዳገኘች ትናገራለች።

"ዕድለኛ ነኝ፣ ትልቅ ማበረታቻ ሆኖኛል።"