እስከ ግማሽ ሚሊዮን ብር የሚወጣባቸው ግዙፍ የሽምግልና አበባዎች፡ የአበባ አብዮት ወይስ የባህል ለውጥ?

ለሽምግልና የተዘጋጁ ግዙፍ የአበባ እቅፎች

የፎቶው ባለመብት, Hirut Flower

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 7 ደቂቃ

የሽምግልና ሥርዓት መልክ እየተቀየረ መጥቷል። በተለይ አዲስ አበባን ጨምሮ በትላልቅ ከተሞች ሰርግ የሚያስንቁ የሽምግልና ድግሶች እየተከወኑ ነው። ሰርግ እና ሽምግልና ገላጋይ በሌለበት ትንቅንቅ ውስጥ የገቡም ይመስላሉ።

በተለይ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ የሚፈስባቸው አበባዎች የመነጋገሪያ ማዕከል ሆነዋል።

አበባዎቹ ከሰው እቅፍም፣ ከአንድ ሰው ሸክምም የከበዱ ናቸው። አንድ መጠሪያ ስም ያላገኙት እነዚህ ቅንጡ የአበባ 'ክምሮች' የዚሁ ባህላዊ ሥርዓት ምልክት እየሆኑ ነው።

ሽምግልናን ጨምሮ ለሌሎች ፕሮግራሞች ግዙፍ አበባዎችን ማዘዝ የተጀመረው ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ እንደሆነ በአበባ ንግድ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች ይናገራሉ።

ሒሩት አናጋው ላለፉት 15 ዓመታት በዘርፉ ተሰማርታ ትገኛለች።

በቅርቡ በሥራ ታሪኳ ግዙፉን ሁለት ሜትር በሁለት ሜትር የሚለካ የአበባ 'እቅፍ' አዘጋጅታለች። በእርሷ አገላለጽ "አንድ አነስተኛ መኝታ ቤት" ያክላል።

ሒሩት ይህን አበባ የታዘዘችው ለልደት ቢሆንም ለሽምግልናም ቁመቱ አጠር ያለ እና ሁለት ሜትር ስፋት ያለው አበባ አዘጋጅታ ለደንበኞቿ አስረክባለች።

ሽምግልና ወደ ትዳር ለመግባት የወላጆች ፈቃድ የሚጠየቅበት፣ ወሳኝ ጥያቄዎች የሚመለሱበት፣ ወንዶች ለሴት ቤተሰቦች ያላቸውን ክብር የሚያሳዩበት እንዲሁም ከእነርሱ ጋር ቤተሰብ ለመሆን ማቀዳቸውን የሚገልጹበት ሒደት እንደሆነ የባህል አጥኚ የሆኑት አንዱዓለም አባተ (ዶ/ር) ያስረዳሉ።

ለዚህ ሥርዓት የሚላኩት ሽማግሌዎችም በዕድሜ በሰል ያሉ፣ ተናግረው የሚያሳምኑ፣ የሚጠየቁትን ጥየቄዎች በአግባቡ መመለስ የሚችሉ፣ ጋብቻ ጠያቂውን እና ቤተሰቡን በደንብ የሚያውቁ፣ በአካባቢው የሚወደዱ እና የሚከበሩ መሆን አለባቸው።

ብዙውን ጊዜ ቁጥራቸውም አራት፣ አምስት፣ ሰባት ነው የሚሆነው። እንደየእምነቱ የሃይማኖት አባቶች ሊካተቱበትም ይችላሉ ።

ቀደም ባለው ጊዜ እነዚህ ሽማግሌዎች ውስኪ፣ ቡና፣ በግ እና ቀለል ያሉ ስጦታዎችን ይዘው እንደሚሄዱ የሚናገሩት አንዱዓለም (ዶ/ር )፣ ሥርዓቱ እንደየአካባቢው ባህል እንደሚከወንም ያስረዳሉ።

የሴቷ ወላጆች የማሰቢያ ጊዜ ለማግኘት ለሽማግሌዎቹ ድጋሚ ቀጠሮ ሊሰጡ የሚችሉበትም ዕድል አለ።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በተለይ በአዲስ አበባ እና በሌሎች ከተሞች ሽምግልና ከቤተሰብ ወደ ሕዝብ፤ ከቤት ወደ አደባባይ ወጥቷል።

ሥርዓቱም የሰርግ ያህል የደመቀ፣ በአበቦች እና በጌጣጌጦች ያሸበረቀ፣ በርካታ ሽማግሌዎች የሚላኩበት እንዲሁም በትልቁ የሚደገስበት ሆኗል።

ጉዳዩም በሁለት ጎራ እያከራከረ ነው።

በአንድ በኩል "ባህልን እየበረዘ እና ሥርዓትን እያናጋ ነው፤ ያልተገባ ፉክክር በመፍጠር ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እያስከተለ ነው" በሚል በጥብቅ ይተቻል።

በሌላ በኩል ደግሞ "ባህል በጊዜ እና በሁኔታ ይለወጣል" ሲሉ ከለውጡ ጋር አብሮ መራመድ እንደሚያስፈልግ የሚሟገቱ አሉ።

ጥንዶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"ባህል ተለዋዋጭ ነው" የሚሉት አንዱዓለም (ዶ/ር ) ፣ "በአገሪቷ ያለው የሰላም እጦት፣ የተጋቢዎች ተራርቆ መኖር፣ የጊዜ እጦት፣ የኢኮኖሚ ሁኔታዎች የኖረውን የሽምግልና ልማድ እየለወጡት መጥተዋል" ይላሉ።

በአበባ ንግድ ላይ የተሰማራችው ሒሩት በበኩሏ ለለውጡ ማኅበራዊ ሚዲያ አስተዋፅኦ እንዳለው ትናገራለች።

እርሷ እንደምትለው በቀደመው የሽምግልና ሥርዓት አበባ ሳይሆን ውስኪ እና በግ ነበር የሚወሰደው። እነዚህን ስጦታዎች ይዘው የሚሄዱትም "ጥያቄያቸው ተቀባይነት ሲያገኝ" ነበር።

የዛሬ ሰባት ዓመት ገደማ አነስ ያሉ የአበባ እቅፎችን ይዞ መሄድ ተጀመረ የምትለው ሒሩት፣ "አሁን ግን ግዙፍ አበባዎች፣ እንደ ዳይመንድ፣ መኪና ያሉ በጣም ውድ እና ትላልቅ ስጦታዎች እንደሚወሰዱ ትናገራለች።

እነዚህን የሚያሳዩ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚጋሩ ቪዲዮዎች እና ፎቶዎችም "የሚላከው የአበባ መጠን፤ የዲኮሩ ውበት እና ድግሱ ይበልጥ ከፍ እንዲል" እንዳደረገው ትገልጻለች።

ጋዜጠኛ፣ ደራሲ እንዲሁም በፋሽን እና በአኗኗር ዘይቤ ላይ ያተኮረ የራዲዮ እና የቴሌቪዥን ፕሮግራም የምታዘጋጀው ኤልሳ አሰፋም በእነርሱ ሃሳብ ትስማማለች።

"ባህል በጊዜ እና በሁኔታ ይለወጣል፤ ለምን ተለወጠም አይባልም" የምትለው ኤልሳ፣ "የኢኮኖሚ ሁኔታ፣ ቴክኖሎጂ፣ ማኅበራዊ ሚዲያ፣ የአኗኗር ዘይቤ፣ ለነገሮች የሚሰጠው ዋጋ፣ ወጪ ቁጠባ፣ ሉላዊነት (ዓለም አቀፋዊነት)" ለለውጡ ምክንያት እንደሆኑ ታስረዳለች።

በእነዚህ ምክንያቶች ቀደም ባለው ጊዜ የጋብቻ አንዱ አካል የነበረው የሽምግልና ሥርዓት መልኩን ቀይሮ "መጨረሻውም መጀመሪያውም ሽምግልና የሆነባቸውን የጋብቻ ሥርዓቶች እያየን ነው" ትላለች።

ሽማግሌዎች በቀጠሮ መመላለሳቸው ቀርቶ በሽምግልናው ቀን ሙሽራዋን ይዞ የሚኬድበት ሁኔታ እየታየ እንደሆነም ትዝብቷን አጋርታለች።

ወደፊት ሥርዓቱ ከነጭራሹ ይቀራል የሚል ግምትም አላት።

ጠዋት ሽምግልና ከሰዓት ሰርግ?

አንዱዓለም (ዶ/ር) እንደሚሉት በኢትዮጵያ ባህል ጋብቻ የራሱ ሰንሰለቶች አሉት። እነዚህም መተጫጨት፣ ሽምግልና፣ ጥሎሽ፣ ሰርግ፣ ቅልቅል እና መልስ ናቸው።

"አሁን ግን በተለይ በከተሞች አካባቢ እነዚህን ጠቅልሎ የማምጣት ነገር እየታየ" ነው ይላሉ።

በቅርቡ የሄዱባቸውን ሁለት ሽምግልናዎችንም በምሳሌነት ይጠቅሳሉ።

የባህል አጥኚው ለመጀመሪያው ሽምግልና አምስት ሆነው መሄዳቸውን እና ቀጠሮ ተሰጥቷቸው ድጋሚ ከሄዱ በኋላ ተቀባይነት ማግኘታቸውን ያስታውሳሉ።

በሁለተኛው ሽምግልና የገጠማቸው ግን ከዚህ የተለየ ነበር። "የዚያኑ ዕለት የቤተሰብ ቅልቅል ተደረገ" ይላሉ። ይህም የቦታ ርቀት እና የሁኔታዎች አለመመቻቸት የፈጠረው እንደሆነ አስረድተዋል።

በቅርቡ አንድ ሰርግ ላይ ተገኝታ እንደነበር ያስታወሰችው ኤልሳም ተመሳሳይ አጋጣሚ አላት።

"ሽምግልናው ጠዋት ላይ ተካሂዶ ነው ምሳ ላይ ለሰርግ የተጠራነው " ብላለች።

በሰርግ ዝግጅት ዘርፍ ገበያው እየተቀዛቀዘ እንደመጣ እንደሚነገርም ኤልሳ ትጠቅሳለች።

እዚህ ላይ ሰርግ ወደ ኋላ አፈግፍጎ ሽምግልና ላይ ለምን ቆመ የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም።

በቅርቡ 25ኛ ዓመት የጋብቻ በዓሏን ያከበረችው ኤልሳ፤ ከእጮኛዋ ጋር ለመጋባት ከወሰኑ በኋላ ሽምግልና እንደተላከ በማስታወስ "ሽምግልና የቤተሰብ ክብር የሚገለጽበት እና ወላጆችም የሚፈልጉት" እንደሆነ ትናገራለች።

አንዱዓለም (ዶ/ር) ሁለት ጊዜ የተመላለሱለት ሽምግልና ጥንዶቹ ቀድሞውኑ አብረው መኖር እንደጀመሩ በመግለጽ "ሽምግልና ወደ ጋብቻ ለመሄድ ትልቁ እና ወሳኙ እርምጃ እንደሆነ" አስረድተዋል።

ለወጉ ያህል ካልሆነ ወላጆች በውሳኔው ላይ ቀድሞ የነበራቸው ሚና በተጋቢዎቹ እየተወሰደ በመምጣቱ ባለቀ ጉዳይ ላይ በቀጠሮ መመላለሱ እና በተከታታይ መደገሱ እየቀረ መጥቷል።

ለዚህም የሴቶች በኢኮኖሚ፣ በትምህርት እና በማኅበራዊ ተሳትፎ ያላቸው ሚና መጎልበት አስተዋፅኦ እንዳለው ይነገራል።

የባህል አጥኝው አንዱዓለም አባተ ( ዶ/ር)

የፎቶው ባለመብት, Andualem Abate

የምስሉ መግለጫ, የባህል አጥኝው ሽምግልናን ጨምሮ በአጠቃላይ የሚሰናዱ ድግሶች የፉክክር መንፈስ ፈጥረዋል ይላሉ

ከድሮው በተሻለ ሴቶች በሚፈልጉት ጉዳይ ላይ ራሳቸውን ችለው ውሳኔ ማሳለፍ ችለዋል፤ የሚወዱትን መርጠው፣ ፈቅደው እና ተጠናንተው ጋብቻ ይመሠርታሉ።

ይህም የሽምግልና ሥርዓት ለወጉ ያህል ብቻ የሚከወን እንዲሆን አድርጎታል።

በሌላ በኩል ደግሞ በተጋቢዎች ውሳኔ ውስጥ የሽማግሌዎች እና የወላጆች ሚና አናሳ መሆን ሴቶች ለጥቃት እንዲጋለጡ፣ ፍቺዎች እንዲበራከቱ ምክንያት እንደሆነ የሚጠቅሱም አሉ።

በአዲስ አበባ ባለፈው ዓመት በስድስት ወራት ውስጥ የተመዘገበው የፍቺ መጠን ከቀደመው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ34 በመቶ መጨመሩን የከተማዋ የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ መግለጹ አይዘነጋም።

ለፍቺዎቹ ተጋቢዎች ስለትዳር በቂ ግንዛቤ ሳይኖራቸው ወደ ትዳር መግባት ከምክንያቶቹ አንዱ ሆኖ ተጠቅሷል።

በዚህ ዓመትም የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በኋላ ላይ ቢያስተባብልም ተጋቢዎች ትዳር ውስጥ ከመግባታቸው በፊት "ሥልጠና መውሰድ አስገዳጅ ነው" ማለቱ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።

አሁንም በተለያዩ ምክንያቶች በወላጆች ውድቅ የሚደረጉ የጋብቻ ጥያቄዎች እንዳሉ የሚጠቅሱት የባህል አጥኚው፣ የሴቶች ውሳኔ ሰጭነት እንዲህ ዓይነት ባህሎችን የሚጫንበት ዕድል የለም ይላሉ።

ኤልሳም በቤተሰብ ውሳኔ ብቻ የሚደረግ ጋብቻን ባትደግፍም፣ አሁንም ወላጆች የቀረበላቸውን ሁሉ መቀበል አለባቸው ብላ አታምንም።

"ሽምግልና ለታይታ ብቻ መደረግ የለበትም" የምትለው ኤልሳ፣ የሚላኩ ሽማግሌዎች ሙሽራውን የሚያውቁ፣ የሚከበሩ፣ ተሰሚነት ያላቸው መሆናቸው ወደፊት የሚፈጠሩ ቤተሰባዊ ችግሮችን ለመፍታት እና ትዳርን ለማፅናት የራሱ ድርሻ እንዳለው ትናገራለች።

ኤልሳ የሽምግልና ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ከጥቃት ይጠብቃል ወይም ዋስትና ነው ብላ ባታምንም፤ "ወላጆች ልጃቸው ሕይወቷን የምታጋራው ወንድ ምን ዓይነት ባህሪይ ፣ ምን ዓይነት አስተዳደግ እንዳለው ለማጣራት እና ለመተዋወቅ የሚካሄድ ሥነ ሥርዓት ስለሆነ ጥቃቶችን አስቀድሞ ለመከላከል የራሱ የሆነ አስተዋፅኦ ሊኖረው ይችላል" ብላለች።

"አሁን ግን በአንዳንድ ሁኔታዎች ቤተሰቡ የማያውቃቸው፣ በቲቪ ወይም በቲክቶክ የሚታወቁ ሰዎች፣ አንዳንዴም ተጋቢዎቹን የማያውቋቸው ሰዎች እየተላኩ ነው" የምትለው ኤልሳ፣ ጉዳዩ ጥንቃቄ የሚያሻው እንደሆነ አሳስባለች።

"ኢንቨስትመንቱ በአበባ እና በዲኮሩ፣ በሚላከው መጠጥ እና በሚጎተተው በግ ላይ ሆኗል" ስትልም ዋናው ቁም ነገር መዘንጋቱን አክላለች።

ሽምግልናን የሚያስውቡት ግዙፍ አበባዎች

አበባዎችን መለዋወጥ በተቀረው ዓለምም የተለመደ ነው። በኢትዮጵያ እየተለመዱ የመጡ የአበባ ስጦታዎች ግን ለየት የሚያደርጋቸው ግዝፈታቸው ነው።

ሒሩት ግዙፍ የአበባ 'እቅፎችን' ለሽምግልና መላክ የኑሮ ደረጃ (ስታተስ) መለያ እየሆነ ነው ትላለች።

በአበባ ንግድ ላይ የተሰማራው ወጣቱ ደረጀ ድሪባ፣ "አበባ ብዛት ሲኖረው ደስ ይላል። አበባ ውበት ነው። ቤት ውስጥ ሲቀመጥ የሚሰጠው ደስታ አለ" ይላል።

ደረጀ እንደሚለው ለሽምግልና የሠሩት ግዙፉ አበባ አንድ ሙሉ ሌሊት የወሰደባቸው ሲሆን፣ አራት ባለሙያዎች ተሳትፈውበታል።

እነዚህ ግዙፍ አበባዎች ከሁለት መቶ እስከ 400 ሺህ ብር ዋጋ እንዳወጡም ጠቅሷል።

ሌሎች ቢቢሲ ያነጋገራቸው በአበባ ንግድ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችም ቅንጡ የአበባ 'እቅፎች' እንደ መጠናቸው እስከ ግማሽ ሚሊዮን ብር ድረስ እንደሚሸጡ ገልጸዋል።

ተሽከርካሪ ላይ የተጫነ ግዙፍ የአበባ እቅፍ ፊት ለፊት የሚታዩ ሠራተኞች

የፎቶው ባለመብት, Lilyflower19

የምስሉ መግለጫ, ለሽምግልና የሚላኩ ግዙፍ አበባዎች ከ200 ሺህ እስከ 400 ሺህ ብር ይሸጣሉ

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሁለተኛዋ አበባ ላኪ አገር ስትሆን ባለፉት ስድስት ዓመታት ውስጥ በአገር ውስጥ ያለው ገበያዋም መነቃቃቱን የአበባ አምራቾች እና ላኪዎች ማኅበር ለቢቢሲ ገልጿል። የአበባ ዋጋም ከነበረበት በእጥፍ ጨምሯል ብሏል።

የማኅበሩ የሥልጠና ክፍል ኃላፊ ሽመልስ ጥላሁን (ዶ/ር )፣ "በቁጥር ማስቀመጥ ባይቻልም በአገር ውስጥ ገበያው ለውጦች መኖራቸው የሚታይ ነው" ብለዋል።

"ለልደት፣ ለሽምግልና፣ ለሰርግ፣ ለምርቃት፣ ለሐዘን ጭምር አበባዎችን ይዞ መሄድ እየተለመደ ነው" የሚሉት ሽመልስ (ዶ/ር )፣ የአንድ ዘለላ የአበባ ዋጋ እስከ 40 ብር እንደሚሸጥ ተናግረዋል።

የአበባ ፍላጎት ጨምሯል የምትለው ሒሩትም ለሠራችው 2 ሜትር በ2 ሜትር ለሆነ አበባ በሺዎች የሚቆጠሩ የአበባ ዘለላዎችን እንደተጠቀመች ትናገራለች። ምን አልባት ከአምስት ሺህ በላይ ሊሆኑ ይችላሉ።

ሰባት ባለሙያዎች የተሳተፉበት ይህ የአበባ 'እቅፍ' 15 ሰዓታትን ወስዷል።

እንዲህ ዓይነት ግዙፍ አበባዎች ዋጋቸው እንደ መጠናቸው እና ዓይነታቸው የሚለያይ ሲሆን፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ብር ያወጣሉ።

በተለይ ለሽምግልና የሚላኩ አበቦች በማኅበራዊ ሚዲያ መጋራታቸው በአገር ውስጥ ያለውን ፍላጎት ጨምሮታል የምትለው ሒሩት፣ ልማዱ ከመዲናዋ ውጪ ቅርብ ወደሆኑ ከተሞችም እየተስፋፋ እንደሆነ ታስረዳለች።

አበባ የሚያዘጋጁ ባለሙያዎች
የምስሉ መግለጫ, ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሁለተኛዋ አበባ ላኪ አገር ስትሆን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአገር ውስጥ ያለው ገበያዋም ተነቃቅቷል

የማኅበራዊ ሚዲያ ፉክክር እና 'የኪራይ ስጦታዎች'

ማኅበራዊ ሚዲያ በሽምግልና ብቻ ሳይሆን በሌሎች ጉዳዮችም ሰዎችን አላስፈላጊ ውድድር ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ ሥነ ልቦናዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ቀውስ በማስከተል ይወቀሳል።

አንዱዓለም (ዶ/ር ) ሽምግልናን ጨምሮ በአጠቃላይ የሚሰናዱ ድግሶች የፉክክር መንፈስ ፈጥረዋል ይላሉ። ኤልሳም የምትስማማበት ጉዳይ ነው። "የሽምግልና ድግስ እና የሚላከው አበባ አቅምን ማሳያ እና መወዳደሪያ እየሆነ ነው" ትላለች።

ሒሩት ግን በማኅራዊ ሚዲያ የሚጋሩ የሽምግልና ሥርዓቶችን ከፉክክር ጋር ሳይሆን ልምድ ከመውሰድ እና የተሻለ ነገር ከመፍጠር ጋር ነው የምታያይዘው።

"ገንዘብ ኖሯቸውም አበባ የማያሠሩ እና የማይደግሱ አሉ" የምትለው ሒሩት፣ የአበባዎቹ ግዝፈት እና የድግሱ ማማር የሽምግልናቸው መለያ እንጂ የሃብት ማሳያ እንዳልሆነ ታስረዳለች።

"በእኔ ሽምግልና ይህን ብጨምርበት የበለጠ ያምራል፤ ከለሩ እንዴት ይሁን ለሚለው ሃሳብ መውሰድ ይችላሉ" ስትል መንፈሱ ያልተገባ ውድድር እንዳልሆነ ትሞግታለች።

ይህ ለአንዱዓለም (ዶ/ር ) አይዋጥላቸውም።

"የሚመረጠው ቦታ፣ ዲኮሩ፣ አበባው፣ ልብሱ፣ የሙዚቃው ባንድ፣ የፎቶ እና ቪዲዮ ፕሮግራም ላይ የኢኮኖሚ አቅምን እና የተሻለ አኗኗርን ማሳየት ሆኗል" ይላሉ።

በአንዳንድ ሁኔታዎች ስጦታዎች ጭምር በኪራይ የሚቀርቡበት አጋጣሚ እንዳለም አንስተዋል።

በኢትዮጵያ የአበባ ዘመን ራሱ 20 ዓመት አልሞላውም የሚሉት አንዱዓለም (ዶ/ር )፣ በብዙ ሺዎች የሚቆጠር የአበባ 'ክምር' ይዞ መሄድ ሽምግልና ላይ ብቻ ሳይሆን የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ እና የሃይማኖት ሥፍራዎችም ጭምር እንደሚስተዋል ተናግረዋል።

"ይህ የፉክክር መንፈሱ የወለደው ነው። የበላይነት ለማሳየት የሚመጣ ነገር ነው። ይህ ማጋነን የሚሸፍነው አንዳች ነገር ያለ ነው የሚመስለኝ" ብለዋል።

ኤልሳም የእርሳቸውን ሃሳብ ትጋራለች።

ይሁን እንጂ የፉክክር መንፈሱ ለውበት እና ለባህል አልባሳት ዘርፍ ትልቅ ዕድል ይዞ መምጣቱን የፋሽን ባለሙያዋ ትናገራለች።

"ቬሎ ጫና ውስጥ ገብቷል። በባህል ልብስ ለተሰማሩ ሰዎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል። ለሜካፕ፣ ለፀጉር፣ ለአበባ እና ለዲኮር ዘርፍ ትልቅ ዕድል እየፈጠረ ነው" ብላለች።

የባህል ጥናት ባለሙያው ግን "በኢኮኖሚ ድቀት ላይ ባለ፣ በርካታ ሕዝብ በችግር ውስጥ በሚኖርበት አገር ላይ ይህን ያህል ውድ ነገር አውጥቶ እዩልኝ ማለት መንፈሱ ራሱ ትክክል እንዳልሆነ" ነው የሚናገሩት።

"አገርን፣ ወገንን፣ ሕዝብን፣ ባህልን እና ማንነትን ያለመረዳት ችግር ውስጥ የመሆን ስሜት ነው ብዬ ነው የማምነው" ሲሉም አክለዋል።

እነዚህ መቶ ሺዎች የሚፈስባቸው የተፈጥሮ አበባዎች ዕጣ ፈንታ የሚያሳየውም ይህንኑ አለመረዳት ይመስላል። የሳምንት ዕድሜ የሌላቸው የተፈጥሮ አበባዎች መጨረሻቸው የቆሻሻ ቅርጫት ነው።

ሒሩት እንደምትለው አንዳንድ ሰዎች አድርቀው የተወሰነውን ለማስታወሻነት ያስቀምጡታል።

ብዙዎች ግን ትዝታቸውን የሚያስቀሩት በቪዲዮዎች እና በፎቶዎች እንዲሁም በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ነው።