በአርሲ የተፈጸመው ጥቃት ምርጫውን የማደናቀፍ አካል ነው - የጠ/ሚኒስትር ጽህፈት ቤት

የፎቶው ባለመብት, PM Office/FB
ንጹሐንን እና የሃይማኖት ተቋማትን ዒላማ በማድረግ የተፈጸሙ ጥቃቶች ዓላማቸው አገሪቱ እንዳትረጋጋ እና ምርጫውን ለማደናቀፍ የተደረገ ዕቅድ ተከታይ ነው ሲል የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጽህፈት ቤት አመለከተ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአርሲ ዞን ኦነግ ሸኔ በሰላማዊ ሰዎች እና በሃይማኖት ቦታዎች ላይ ፈጸማቸው ባሏቸው ጥቃቶች የቤተሰብ አባላታቸውን ሕይወት ላጡ፣ ጉዳት ለደረሰባቸው እና ንብረታቸው ለወደመባቸው ዜጎች የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸዋል።
ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘለግ ያለ መግለጫ በዋናነት በአገሪቱ በተካሄደው ምርጫ እና መንግሥታቸው አስመዘገበው ባላቸው አዎንታዊ ውጤቶች ላይ ሲሆን በአርሲ ውስጥ የተፈጸመውን ጥቃት እና የአማጺያን ሙከራዎች እና የመንግሥት እርምጃን አብራርተዋል።
አርብ አመሻሽ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስረሩ ጽህፈት ቤት የወጣው እና በመንግሥታዊ መገናኛ ብዙኃን የቀረበው መግለጫ የወጣው በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት በርካታ ሰዎች ከተገደሉ እና ሰባተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ከተካሄደ ከቀናት በኋላ ነው።
ምርጫውን ተከትሎ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የተዘገበው በምሥራቅ አርሲ አንዳንድ ወረዳዎች የተፈጸመ ጥቃት የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች እና አብያተ ክርስቲያናት ላይ ያነጣጠረ መሆኑን የቤተከርስቲያኗ ፓትሪያርክ አቡነ ፓትሪያርክ በሐዘን ባወጡት መግለጫ ገልጸዋል።
እሁድ ግንቦት 23 እና ሰኞ ግንቦት 24 የምርጫው ዕለት በተፈጸመው ጥቃት በሦስት ወረዳዎች ውስጥ የሚኖሩ ቢያንስ 13 ሰዎች መገደላቸውን፣ በርካቶች መጎዳታቸውን፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ መፈናቀላቸውን እንዲሁም አንድ ጥንታዊ ቤተ ክርስቲያን በእሳት ሲወድም ሌላ ቤተክርስቲያን ደግሞ ዘረፋ እንደተፈጸመበት ቤተ ክርስትያኗ አስታውቃለች።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ ጥቃቶቹ "የአገሪቱን ዕድገት ለማደናቀፍ ከሚሹ አካላት፣ በአማራ ክልል ከሚንቀሳቀሱ አማጺያን እና ለአገሪቱ ዕድገት ጥላቻ ካላቸው የውጭ ኃይሎች ጋር በጥምረት የተከናወኑ ነው" ብሏል።
ጨምሮም ኦነግ ሸኔ በፀጥታ ኃይሎች "በተወሰደበት እርምጃ ፍላጎቱን ማሳካት ባለመቻሉ ስስ ዒላማዎች ላይ በማተኮር የሃይማኖት እና የብሔር ግጭት ለመቀስቀስ" በአርሲ ዞን ውስጥ ጥቃት ፈጽሟል ሲል አመልክቷል።
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ጥቃቱን የፈጸመው መንግሥት በሽብርተኛ ቡድንነት የፈረጀው እና ኦነግ ሸኔ የሚለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ባለፉት ቀናት ጥቃቱን በተመለከተ በሰጠው ምላሽ እና ባወጣው መግለጫ በድርጊቱ ውስጥ እጁ እንደሌለበት አስተባብሏል።
በአርሲ ዞን ውስጥ በሰላማዊ ዜጎች ላይ በታጣቂዎች የተፈጸመው ጥቃት የመጀመሪያው ሳይሆን ባለፉት ዓመታት በተለያዩ ጊዜያት ሲፈጸሙ የቆዩ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን እና ምእመኗ በተለየ ዒላማ እንደተደረጉባት የምትገልጸው የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መንግሥት የነዋሪዎችን ደኅንነት እንዲጠብቁ በተደጋጋሚ ጥሪ ሲያቀርቡ ነበር።
ጥቃቱን ተከትሎ ቢቢሲ የአርሲ ዞን የሚገኙ ወረዳዎች ባለሥልጣናት ስለጥቃቱ ቢጠይቃቸውም መረጃ እንደሌላቸው ገልጸው ነበር። የክልሉ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ለመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በሰጡት ቃል ጥቃቱ በኦነግ-ሸኔ መፈጸሙን እና የሃይማኖትም ሆነ የማንነት ገጽታ እንደሌለው ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታት በአርሲ ውስጥ ሲፈጸም በቆየው ጥቃት በርካታ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ለጥቃቱ ኃላፊነት የወሰደም ሆነ ተጠያቂ የሆነ ቡድንም ሆነ ግለሰብ ስለመኖሩ በይፋ የሚታወቅ ነገር የለም።
በወቅታዊ ጉዳዮችን ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት የወጣው መግለጫ አንዳንድ የአገሪቱ ኃይሎች ከኤርትራ ጋር እንደፈጠሩት ሲነገር ስለቆየው 'ፅምዶ' ስለተባለው እንቅስቃሴም አንስቷል።
መግለጫው "የጥፋት ኃይሎች" ሲል በስም ያልጠቀሳቸው ቡድኖች "ከባዕዳን ጋር 'ፅምዶ' የሚል ቁርኝት በመፍጠር ዕኩይ ዓላማቸውን ለማሳካት ሰፊ የጥፋት ዝግጅት ሲያድርጉ ቆይተዋል" በማለት ምርጫው ለማደናቀፍ የተለያዩ ድርጊቶችን ሲፈጽሙ ነበር ሲል ከስሷል።
"አመፅ እና ሁከት ለማነሳሳት፣ ከተሞችን በሽብር ጥቃት ለማወክ፣ በመንገዶች ላይ የደፈጣ ጥቃት በመፈጸም እንቅስቃሴ ለመገደብ እና በተወሰኑ አካባቢዎች ዒላማ አድርገው ነጥሎ ለማጥቃት ተንቀሳቅሰዋል" በማለት የፀጥታ ኃይሎች ግን ዕቅዳቸውን ማክሸፋቸውን ገልጿል።
መግለጫው በማሳያነት የትጥቅ ድጋፍ ያገኙ ታጣቂዎች "በደቡባዊ ትግራይ በሚገኙ አዋሳኝ የአማራ ክልል አንዳንድ አካበቢዎች " ትንኮሳ መፈጸሙን፤ እንዲሁም በባሕር ዳር፣ በጎንደር፣ በደብረ ብርሃን እና በወልድያ ከተሞች እና በሌሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ የሽብር ጥቃት ዓላማ እንደነበር ነገር ግን "እንዲከሽፍ ማድረግ ተችሏል" ብሏል።
"በኦሮሚያ ክልል የሸኔ ሽብር ቡድን ከጽንፈኛው ፋኖ ታጣቂ ቡድን ጋር በመናበብ" መንገዶችን በመዝጋት እንቅስቃሴ ለማስተጓጎል መሞከራቸውን እና አለመሳካቱንም ገልጿል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሁለቱ ታጣቂ ቡድኖች ከምርጫው ቀን ቀደም ብሎ እና ከዚያም በኋላ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ የእንቅስቃሴ ገደብ መጣላቸውን አሳውቀው ነበር።















