"በአርሲ የሚስተዋለው በደልና ግፍ 'እስከ መቼ?' የሚል...ጥያቄን ፈጥሯል" - አቡነ ማትያስ

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት

የፎቶው ባለመብት, EOTC TV

የምስሉ መግለጫ, ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን በምእመናን እና በአብያተ ክርስቲያናት ላይ የሚፈጸመው ጥቃት መቀጠሉ "እስከ መቼ" የሚል ሐዘን እንደፈጠረ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ባስተላለፉት መልዕክት አስታወቁ።

ባለፈው እሁድ እና ሰኞ በምሥራቅ አርሲ ዞን ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ በታጣቂዎች በተፈጸሙ ጥቃቶች 13 የሚሆኑ ሰዎች ሲገደሉ፣ አንድ ቤተክርስቲያን በእሳት የወደመ መሆኑን እና ሌላ ቤተክርስቲያን ላይ ዘረፋ እና ጉዳት መድረሱን የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ እና ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ይህንን ተከትሎ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በአርሲ ሀገረ ስብከት በቤተ ክርስቲያኗ እና በምእመናን ላይ የደረሰውን ጥቃት በማስመልከት መልዕክት አስተላልፈዋል።

አቡነ ማትያስ በአርሲ ሀገረ ስብከት በአሰኮ፣ በሽርካ፣ በሆንቆሎ፣ በዋቤ እና በሙኔሳ ወረዳዎች በተፈጸሙት ጥቃቶች "በመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን እና በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ላይ ስለደረሰው አሰቃቂ ጥቃት የሰማነው በተሰበረ ልብ ነው" ብለዋል።

በጥቃቱ "በርካታ ምእመናን በግፍ መሰዋታቸው እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ከቀዬአቸው መፈናቀላቸው ቤተ ክርስቲያናችንን በእጅጉ ያሳዘነ ክስተት ነው" ያሉት ፓትሪያርኩ፤ "በአርሲ ምድር በተደጋጋሚ የሚስተዋለው በደል እና ግፍ በሁላችንም ልቡና ውስጥ "እስከ መቼ?" የሚል የቁጭት እና የሐዘን ጥያቄን ፈጥሯል" ብለዋል።።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች እና የቤተክርስቲያኗ ምእመናን ጥቃቱ እሁድ ዕለት ጀምሮ እስከ ሰኞ ድረስ የቀጠለ መሆኑን እና ዕድሜያቸው ከ80 አስከ 25 ዓመት የሆናቸው ሰዎች በታጣቂዎቹ መገደላቸውን እንዲሁም ዝርፊያ እና የቤቶች ቃጠሎ መፈጸሙን ገልጸዋል።

ጥቃቱ የተፈጸመበት የአርሲ እና ሶማሌ ክልል ጅግጅጋ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ በጥቃቱ "13 ኦርቶዶክሳውያን መገደላቸውን፣ ከ280 በላይ ምእመናን መፈናቀላቸውን እና የ101 ዓመት ቤተ ክርስቲያን መቃጠሉን" የሟቾችን ስም በመዘርዝር አስታውቀዋል።

ፓትሪያርክ አቡነ ማትያስም "የእምነት ነፃነት ተደፍሮ መቶ ዓመታት ያስቆጠረው የጠላታ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን" መቃጠሉን፣ እንዲሁም "የካራ ኩፍቴና መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን መዘረፉን" በመልዕክታቸው ላይ አመልክተዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የቤተክርስቲያናቱ አባላት የተቃጠለውን የተዘረፈውን ቤተ ክርስቲያን "ምእመናን ጽላቱን ይዘው ተሰደዋል፤ መኖሪያ ቤታቸውም ተቃጥሏል" ብለዋል።

ቤተ ክርስቲያኗ "በምድራዊ መከራ ውስጥ ያሉትን ምእመናን በምታጽናናበት በዚህ ወቅት፣ ራሷ በፈተና ውስጥ ሆና መቸገሯን" የጠቀሱት ፓትሪያርኩ፣ በአርሲ ውስጥ በተደጋጋሚ የሚፈጸመው ጥቃት ከመቆም ይልቅ እየባሰ መምጣቱን በመግለጽ የሚመለከታቸው አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

"ይህ መከራ እያበቃ ሳይሆን እየሰፋ በመምጣቱ የዜጎችን ደኅንነት የመጠበቅና ሰላምን የማስፈን አደራ የተጣለባችሁ የፀጥታ አካላትና ኃላፊዎች…ይህንን የጥቃት ሰንሰለት በማስቆምና ወንጀለኞችን ለሕግ በማቅረብ ከታሪክ ባለዕዳነት ትድኑ ዘንድ በቤተ ክርስቲያናችን ስም አበክረን እናሳስባለን።"

ከቀናት በፊት የተከሰተውን የበርካታ ሰዎች ሕይወት የጠፋበት እና መፈናቀል ያስከተለውን ጥቃት በተመለከተ ከፌደራል መንግሥቱ፣ ከኦሮሚያ ክልል አስተዳደርም ሆነ ከዞኑ ኃላፊዎች እስካሁን የተባለ ነገር የለም።

ቢቢሲ በደረሰው ጥቃት ላይ መረጃ ለመጠየቅ ለኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ እና የክልሉ ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አራርሳ መርዳሳ በተደጋጋሚ ቢደውልም ስልካቸው ባለመነሳቱ ምላሽ ማግኘት አልቻለም።

ቢቢሲ አፋን ኦሮሞ የአርሲ ዞን ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑትን አቶ ሶሪ ወጊን ስለተፈጸመው ጥቃት ማክሰኞ አመሻሽ ላይ ላቀረበላቸው ጥያቄ "እስካሁን የደረሰን መረጃ የለም፤ እናጣራለን" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ጥቃቱ ከተፈጸመባቸው አካበቢዎች አንዱ የሆነው የሆንቆሎ ዋቤ ወረዳ አስተዳዳሪ ሐሰን መሐመድም ሰዎች ስለሞቱበት እና ንብረት ስለወደመበት ክስተት "መረጃ የለንም" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ከጥቃቱ ጋር ስሙ እየተነሳ ያለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በሰሜን አሜሪካ የሚገኙት የቡድኑ ቃል አቀባይ መሆናቸውን የሚገልጹት ጂሬኛ አያና ምላሽ እንዲሰጡ ቢቢሲ በጽሑፍ መልዕክት ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን ዘገባው እስከወጣበት ጊዜ መልስ አልሰጡም።

በኦሮሚያ ክልል በሚገኘው አርሲ ዞን ውስጥ በሚገኙ ቦታዎች በተለያዩ ጊዜያት በተፈጸሙ ጥቃቶች በርካታ ሰዎች መገደላቸው የተዘገበ ሲሆን፣ ነዋሪዎች ጥቃቱ እምነትን መሠረት ያደረገ እና ዒላማ የተደረጉት ሰዎችን መኖሪያ፣ ንብረት እና አብያተክርስቲያን ጭምር ያወደመ መሆኑን ይናገራሉ።

በአርሲ ዞን በተመሳሳይ ስፍራዎች በተደጋጋሚ እየተፈጸሙ ለሰዎች ሕይወት መጥፋት እና ለንብረት ውድመት ምክንያት የሆኑት ጥቃቶች በማን እንደሚፈጸሙ አስካሁን በግልጽ የታወቀ ነገር የለም።

በተደጋጋሚ በሚከሰቱት ጥቃቶች የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዒላማ እንደሚሆኑ ነዋሪዎች ከመናገራቸው በተጨማሪ እነሱን ከጥቃቱ ለመታደግ የሞከሩ የአካበቢው ነዋሪ የሆኑ የሌላ እምነት ተከታዮችም የጥቃቱ ሰለባ መሆናቸው ተዘግቧል።

ባለፈው ጥቅምት ወር አጋማሽ ላይ በአካባቢው በተፈጸመ ጥቃት 25 ሰዎች ከተገደሉ በኋላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በምእመናኖቹ ላይ የሚፈጸመው ጥቃት እየተባባሰ መሆኑን በመጥቀስ መንግሥት የዜጎችን በሕይወት የመኖር መብት እንዲያስከብር መጠየቁ ይታወሳል።