ለፍቅር ግንኙነት የተዋወቋቸውን ሰዎች በሚሊዮኖች ያጭበረበሩ ናይጄሪያውያን ለአሜሪካ ተላልፈው ተሰጡ

ሞባይል የያዘች ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ በአሜሪካ ያሉ ሴቶችን በኢንተርኔት አማካይነት ቀርቦ የፍቅር ግንኙነት በመጀመር የማጭበርበር ወንጀሎችን በመፈጸም የሚፈለጉ ስድስት ናይጄሪያውያንን ለኤፍቢአይ አሳልፎ ሰጠ።

የደቡብ አፍሪካ ባለሥልጣናት እንዳሉት፣ ናይጄሪያውያኑ በአሜሪካ ውስጥ ከ100 በላይ ሴቶችን በማጭበርበር ከ6 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ በመዝረፍ ይከሰሳሉ።

ለአሜሪካ ተላልፈው የተሰጡት ግለሰቦች በ2021 ታስረው ነበር፤ እንዲሁም "ብላክ አክስ" የተባለ ከሰዎች ዝውውር፣ ከበይነ መረብ ማጭበርበር እና ከግድያ ጋር የተያያዘ የናይጄሪያ የማፍያ ዓይነት የወንጀል ቡድን አባላት እንደሆኑ ይታመናል።

ገንዘባቸውን ከተጭበረበሩት መካከል ጡረተኞች እና ነጋዴዎች እንዳሉበት ተገልጿል። እነዚህ ሰዎች "ገንዘባቸውን ለመውሰድ የተራቀቁ የኢንተርኔት ግንኙነቶችን በመጠቀም ዒላማ ተደርገው ነበር" ሲል የደቡብ አፍሪካ ልዩ የፖሊስ ኃይል ገልጿል።

የፖሊስ ቃል አቀባይ ኮሎኔል ካትሌጎ ሞጋሌ በሰጡት መግለጫ፣ ቡድኑ "ከኬፕ ታውን እስር ቤት ወደ አውሮፕላን ማረፊያ ተወስዶ" ለኤፍቢአይ እና ለዩናይትድ ስቴትስ ሲክሬት ሰርቪስ ባለሥልጣናት እንደሚሰጥ ተናግረው ነበር።

ግለሰቦቹ አሜሪካ እንደደረሱ በማጭበርበር እና በወንጀል የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ በማስመሰል ወንጀሎች ይከሰሳሉ።

እስካሁን ድረስ የአሜሪካ እና የደቡብ አፍሪካ ባለሥልጣናት ለአሜሪካ የሚሰጡትን ግለሰቦች ስም አልገለጹም። ቢቢሲም ለኢንተርፖል፣ ለኤፍቢአይ፣ ለሲክሬት ሰርቪስ እና ለአሜሪካ የፍትሕ መምሪያ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ ጥያቄ አቅርቧል።

ብላክ አክስ (Black Axe) በከፍተኛ ጥቃት እና ጭካኔ የሚታወቅ፣ እንቅስቃሴውን በአፍሪካ፣ በአውሮፓ እና በሰሜን አሜሪካ የሚያካሂድ ምስጢራዊ የወንጀል አውታረ መረብ ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በ2021 የቢቢሲ አይ (BBC Eye) ምርመራ እንደጠቆመው፣ ይህ ቡድን በዓለም ላይ ካሉ በጣም ሰፊ ተጽእኖ እና አደገኛ ከሆኑ የተደራጁ የወንጀል ቡድኖች አንዱ ሆኖ አድጓል።

ናይጄሪያ የቡድኑ ዋና የምልመላ ማዕከል ሲሆን፣ ብዙ አባላቱ ዩኒቨርሲቲ የተማሩ ሰዎች ናቸው፤ በትምህርት ዘመናቸውም ወደ ቡድኑ እንደሚገቡ ይነገራል።

መጀመሪያው የናይጄሪያ የተማሪዎች ማኅበር እንደነበረ ቢገለጽም፣ ለብዙ ዓመታት በሕግ አስከባሪ ተቋማት ትኩረት ውስጥ ቆይቷል።

በወንጀል ቡድኑ ላይ የኤፍቢአይ የተደረጉት ምርመራዎች ከስድስት ዓመት በፊት ነበር የተጀመሩት። በዚህም ከ35 በላይ ሰዎችን በርካታ ሚሊዮን ዶላሮችን በበይነ መረብ አማካይነት በማጭበርበር ተከስሰዋል።

ከዚያ ወዲህ በኢንተርፖል ቅንጅት በተለያዩ አገራት ብላክ አክስን ለመቆጣጠር በርካታ ዘመቻዎች ተካሂደዋል።

ኢንተርፖል ነሐሴ ላይ እንደገለጸው፣ ከኅዳር እስከ ሰኔ በተካሄደው የቅርብ ጊዜ ዘመቻ፣ በደቡብ አፍሪካ በፍቅር ግንኙነት አማካኝነት እና ከኢንቨስትመንት ማጭበርበር ጋር የተያያዘ ቡድን የሚጠቀምባቸው ሰባት ቦታዎች ተፈትሸለል።

ይህም 39 ሰዎች እንዲታሰሩ፣ ገንዘብ እንዲያዝ እና ከ250 በላይ የባንክ ሂሳቦች እንዲታገዱ ምክንያት ሆኗል።

ከአምስት ዓመት በፊት የአሜሪካ ፍትሕ መሥሪያ ቤት ከብላክ አክስ ጋር በተያይዘ ተጠርጥረው በነበሩ ስምንት ወንዶች ላይ የፌዴራል ክስ መመሥረቱን አስታውቆ ነበር።

ዐቃቤ ሕጎች እንደገለጹት፣ እነዚህ ግለሰቦች የፍቅር ማጭበርበርና ቅድመ ክፍያ በመቀበል የማጭበርበር ዘዴዎችን በመጠቀም ሰፊ የበይነ መረብ ማጭበርበር ውስጥ የተሳተፉ ቡድን አባላት ነበሩ።

ተከሳሾቹ በአሜሪካ ያሉ ተጎጂዎችን ለመፈለግ እና ቃላቸውን ለመቀበል ማኅበራዊ ሚዲያን፣ የፍቅር አጋር መፈለጊያ ድረ ገጾች እና በኢንተርኔት የሚደረጉ የስልክ ጥሪዎችን በተለያዩ የውሸት ስሞች ተጠቅመዋል ተብሏል።

ቡድኑ የተጎጂዎችን የባንክ ሂሳቦች፣ እንዲሁም በአሜሪካ የባንክ ሂሳብ ያላቸውን ሌሎች ሰዎች ሂሳቦች በመጠቀም ገንዘብ ወደ ደቡብ አፍሪካ እንዳስተላለፈ ይከሰሳል። በአንዳንድ ሁኔታዎች ደግሞ ተጎጂዎቹ በአሜሪካ የባንክ ሂሳቦች እንዲከፍቱ በማሳመን፣ ተከሳሾቹ እነዚያን የባንክ ሂሳቦችን እንዲጠቀሙባቸው ያደርጉ ነበር።

በኒው ጀርሲ ግዛት ለተጎጂዎች በተሠራጨ መጠይቅ፣ ኤፍቢአይ የቡድኑ አባላት በተለያዩ የውሸት ስሞች በመጠቀም ከተጎጂዎች ገንዘብ ለመውሰድ እንደሞከሩ ገልጿል።

አጭበርባሪዎቹ ብዙ ጊዜ የሚጠቀሙት ታሪክ፣ በኢንተርኔት የተዋወቁትን የፍቅር አጋር ለአንድ የኮንስትራክሽን ሥራ ወደ ደቡብ አፍሪካ እንደሄዱ በመግለጽ፣ ከዚያም በሌቦች መዘረፉን በመግለጽ ስልክ እና ሌሎች የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ወደ ደቡብ አፍሪካ እንዲላኩለት ይጠይቃል።

እንዲሁም ተጎጂዎች በኢንተርኔት የተዋወቋቸው የፍቅር አጋር በግንባታ ቦታ የተበላሸ ከባድ ማሽን ለማስጠገን፣ ለደረሰ አደጋ የሚሰስፈልግ የሕግ ወጪ ለመክፈል ወይም ግብር በመክፈል በጣም ብዙ ገንዘብ እንዲለቀቅለት ብድር እንደሚያስፈልገው በመንገር ካልጠረጠሩ ሰለባዎች ከፍተኛ ገንዘብ እንዲተላለፍላቸው ያደርጋሉ።