ከመስከረም 1 ጥቃት ከዓመታት በፊት ሲአይኤ 'ስለሚፈነዱ አውሮፕላኖች' ማስጠንቀቂያ ደርሶት እንደነበር ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የመስከረም 1 ጥቃት ከመፈጸሙ ከሦስት ዓመታት በፊት የአሜሪካ የደኅንነት ተቋም ባለሥልጣናት "አል-ቃኢዳ ተቀጣጣይ አውሮፕላን ወደ ከተማዋ ሊያበርር የሚችልበት ዕድል እንዳለ" መወያየታቸውን አዲስ ሰነድ አሳየ።
ከዚህ ቀደም ምሥጢራዊ የነበረው ሰነድ አሁን ለሕዝብ ይፋ የሆነው ከሽብር ጥቃቱ 25ኛ ዓመት መታሰቢያ ጋር በተያያዘ ነው።
የአሜሪካ የደኅንነት ተቋም (ሲአይኤ) 71 ገጽ ፕሬዝዳንታዊ ሰነዶችን ይፋ አድርጓል። እነዚህም ከአውሮፓውያኑ 1998 ጀምሮ ጥቃቱ ከደረሰበት ቀን በኋላ እስካለው ጊዜ የተሰበሰቡ ናቸው።
በአውሮፓውያኑ መስከረም 12/2001 የተመዘገበ አንድ ሰነድ እንደሚያሳየው በአክራሪ ቡድኖች ዘንድ ጥቃት የመጸም ሴራ መኖሩ "በስፋት የሚታወቅ" ነበር።
ለፕሬዝዳንቶች በየቀኑ የሚሰጡ ማብራሪያዎች በአሜሪካ መንግሥት በጥብቅ ምሥጢር የሚያዙ የደኅንነት መረጃዎች ናቸው። ከ40 እስከ 50 ዓመት ድረስም ለሕዝብ ይፋ ሳይሆኑ ይቆያሉ።
የሲአይኤ ዳይሬክተር ጆን ራትክሊፍ "ከ25 ዓመት በፊት የ9/11 ጥቃት አገራችንን አናውጧል፤ ነገር ግን አልሰበሩንም" ብለዋል።
"ለዓመታት የሲአይኤ ባልደረቦች ለተገደሉት አሜሪካውያን ፍትሕ እንዲሰፍን እና አል-ቃኢዳ ዳግመኛ አገራችንን እንዳይጎዳ ሲታገሉ ቆይተዋል" ሲሉም አክለዋል።
ይፋ ከተደረጉት 71 ሰነዶች መካከል 69 ያህሉ ከዚህ ቀደም ለሕዝብ ያልተገለጹ ናቸው።
ይፋ የተደረጉት ሰነዶች በክሊንተን እና በቡሽ አስተዳደር ወቅት የተሰበሰቡ ናቸው። ከሰነዶቹ ይዘት ለሕዝብ ይፋ እንዳይወጡ የተቀነሱ መረጃዎች ሊኖሩ ይችላሉ።
አል-ቃኢዳ እና መሪው ኦሳማ ቢን ላደን አስጊነታቸው እየጨመረ እንደነበር ሰነዶቹ ይጠቁማሉ።
የአሜሪካ ደኅንነት ተቋም በተደጋጋሚ ስጋት እዳለ ጥቆማ ሲሰጠው እንደነበር የሚያሳይም ነው። ሆኖም ግን የስጋቱ መጠን እና ምን ሊከሰት ይችላል የሚለውን በተመለከተ ስለነበረው መረጃ ዝርዝር ነገር አልተጠቀሰም።
በአውሮፓውያኑ መስከረም 10/1998 የተመዘገበ መረጃ፤ ቢን ላደን አሜሪካ ላይ ጥቃት ለማድረስ እንደሚፈልግ እና ዋነኛ ዒላማው ዋሽንግተን እንደሆነች ያሳያል።
የሲአይኤ ባለሙያ "የሚፈነዳ አውሮፕላን በከተማዋ ላይ ሊያበርር ይችላል" ብለዋል።
ስለ መስከረም 1 ጥቃት ምርመራ እንዲያደርግ የተሰማራው ኮሚቴ በ2004 ባወጣው መረጃ መሠረት አል-ቃኢዳ ለጥቃቱ አውሮፕላን የመጠቀም ዕቅድ እንደነበረው ያሳያል።
ይህ ማስጠንቀቂያ ከቀድሞው ፕሬዝዳንት ቢል ክሊንተን ዘንድ መድረሱን በተመለከተ ግልጽ መረጃ የለም።
በ1988 የአሜሪካ የስለላ ባለሙያዎች ስለ ቢን ላደን እና አል-ቃኢዳ ያውቁ ነበር።
በዚያው ዓመት በኬንያ እና በታንዛኒያ በሚገኙ የአሜሪካ ኤምባሲዎች ላይ ባደረሱት ጥቃት 224 ሰዎች ሲገደሉ፤ አሜሪካ በምላሹ በአፍጋኒስታን እና በሱዳን በክሩዝ ሚሳዔሎች ጥቃት ፈጽማለች።
ነሐሴ 28/1998 የተመዘገበ መረጃ እንደሚያሳየው ኤምባሲዎቹ ላይ ጥቃት ከደረሰ ከ21 ቀናት በኋላ እንዲሁም አሜሪካ የአጸፋ እርምጃ ከወሰደች ከስምንት ቀናት በኋላ፤ ቢን ላደን "አሜሪካ ላይ ጥቃት ለመፈጸም" በንቃት እየተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል።
ይፋ ከተደረጉት ሰነዶች አንደኛው ከጥቃቱ በኋላ የተመዘገበ ሲሆን፣ ከመጀመሪያው ጥቃት ከ20 ሰዓታት በኋላ ለዋይት ሐውስ የተላከ ነው።
በአፍጋኒስታን እና በፋርስ ባሕረ ሰላጤ የሚገኙ አክራሪዎች "ጥቃቱ እንደሚፈጸም እንደሚያውቁ በርካታ ማስረጃ እንደነበር" ይጠቁማል።
ሌላ ይዘቱ ተቀንሶ ለሕዝብ ይፋ የሆነ ሰነድ እንደሚያሳየው ደግሞ ቢን ላደን በአፍጋኒስታን ወደምትገኘው ካቡል መዘዋወሩን እንዲሁም ጥቃቱ መቀነባበሩን አክራሪዎች "በስፋት ያውቁ" ነበር።
ቢን ላደን ወደ ካቡል የተዘዋወረው ከታሊባን መሪዎች ጋር ላለመጋጨት ሲሆን ጥቃቱን ለመፈጸም ባወጣው ዕቅድ ከታሊባን መሪዎች ጋር "መጋጨቱ" ተጠቅሷል።
ከጥቃቱ በኋላ የያኔው የታሊባን መሪ ሙላህ ኦማር እና ቤተሰቦቻቸው ከደቡባዊ የአፍጋኒስታን ከተማ እንዲወጡ ተደርጓል። አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አሜሪካ እና አጋሮቿ አል-ቃኢዳን ለማጥፋ አፍጋኒስታንን ወርረዋል።















