በኢንተርኔት ግንኙነት እናቱን ያጭበረበረውን ናይጄሪያዊ ፍለጋ አህጉራትን ያቋረጠው ስፔናዊ

የፎቶው ባለመብት, Carlos Barragán
"ውስብስ መንገድ የሚጠቀሙ ሆነው አላገኘኋቸውም። ብልህም አልነበሩም… እጅግ ያስገረመኝም እርሱ ነው" ይላል ካርሎስ ባራጋን።
ካርሎስ አፍቃሪ ሰው መስሎ እናቱን ያጭበረበረውን ግለሰብ ለማግኘት ወደ ናይጄሪያ ሲጓዝ፣ የተካነ አጭበርባሪ ሰው እንደሚያገኝ ጠብቆ ነበር።
በሶሪያ ከሚገኝ አሜሪካዊ ወታደር እንደሆነ የገለጸው ግለሰብ በላካቸው ኢሜይሎች ላይ ያለው የበይነ መረብ (አይፒ) አድራሻ የሚያሳየው ናይጄሪያ ውስጥ እንዳለ ነበር።
ካርሎስ ወደ ናይጄሪያ ከሄደ በኋላ ግን ወንጀለኛውን የማጋለጥ ዕቅዱን ትቶታል። ይልቁንም ለአራት ዓመታት ያህል 'ናሁ ቦይስ' ተብለው የሚታወቁትን የናይጄሪያ ወጣት አጭበርባሪዎች ማጥናት ተያያዘ። ከእነዚህ ወጣቶች ውስጥ አብዛኞቹ በትምህርታቸው ያልገፉ፣ ገንዘብ የሌላቸው እና ዕድል ያልተመቻቸላቸው ናቸው።
ናይጄሪያ ከሄደ በኋላ ያጋጠመው ነገር እናቱን ስላስጨረበረበው ሰው የነበረውን አስተሳሰብ ተፈታትኖታል። በዘመናዊው ዓለም ውስጥ ብቸኝነት ስለሚፈጥረው ተጽዕኖ እንዲጠይቅም አድርጎታል።
የአሜሪካው ወታደር 'ብራያን'

የፎቶው ባለመብት, Carlos Barragán
ካርሎስ እናቱን 'ጠንካራ እና በራሷ የቆመች ሴት' ሲል ይገልጻታል። ሕክምና ያጠናችው እና የጥርስ ክሊኒክ ያላት እናቱ፣ ትጭበረበራለች ተብላ የምትገመት አይደለችም። ለዚያም ነበር እሱ እና ወንድሞቹ እናታቸው በአጭበርባሪ ሰው እንደታለለች ሲረዱ የደነገጡት።
እንዴት ለዚህ እንደበቃች የሚያስረዳ ፍንጭ ያገኙት ለአዲሱ ፍቅረኛዋ "ብራያን" የላከችውን ኢሜይል ሲመለከቱ ነው።
የኢሜይል መልዕክቱ፤ "መጀመሪያ እናቴን ከዚያም ታናሽ እህቴን ስንከባከብ ነበር፤ ቀጥሎ ደግሞ ባለቤቴን እና ልጆቼን ተንከባከብኩ። ሕይወቴን በሙሉ ሌሎችን ስንከባከብ ነበር፤ አሁን እኔን የሚንከባከበኝ ሰው እፈልጋለሁ" ይላል።
ይህ ከመፈጠሩ ወራት አስቀድሞ፣ ከባለቤቷ የተፋታችው እናቱ ብቸኝነት እንደተሰማት ያስተዋለው ካርሎስ፣ 'ቲንደር' የተባለውን የፍቅረኞች መገናኛ እንድትጠቀም አበረታትቷት ነበር።
በ50ዎቹ አጋማሽ ላይ የሚገኝ ሸበላ ከሆነው እና በሶሪያ የተሰማራ አሜሪካዊ ወታደር እንደሆነ ከገለጸው 'ብራያን' ጋር የተገናኘችው ብዙም ሳይቆይ ነው
ወታደር የነበረው የካርሎስ ታላቅ ወንድም ወዲያውኑ ጥርጣሬውን ለእናቱ ገልጿል።
እናቱ በልጇ ከተሰጣት ማሳሰቢያ በኋላ ስለግንኙነቱ ከእሱ ጋር ማውራት ብታቆምም፣ አልፎ አልፎ ከብሪያን የተላኩለትን ኢሜይሎች ለካርሎስ ታሳየው ነበር።
የኢሜይል ልውውጦቹ በፍቅር እና በጥልቅ ስሜት የተሞሉ ነበሩ። ብራያን ብዙም ሳይቆይ አብረው ከመኖር ወደ ስፔን እንደሚመጣ መናገር ጀመረ። ግንኙነቱ እዚህ የደረሰበት ፍጥነት የካርሎስን እናት ጭምር ያስገረመ ነበር።
"በተወሰነ መልኩ ትጠራተር የነበረ ይመስለኛል" ይላል ካርሎስ።
ቀጥሎ ደግሞ ብራያን ጥፍጥፍ ወርቆችን ወደ ቤታቸው እንደሚልክ ሲናገር በቤተሰቡ ውስጥ አለመግባባት ተፈጠረ።
ካርሎስ ይህንን ነገር ማጣራት የጀመረው፣ እናቱ ሁለት ቀለበቶችን ይዛ ወደ ቤት መጥታ፣ በቅርቡ አብረው መኖር እንደሚጀምሩ ስትናገር ነው።
ከዚያም የብራያን ኢሜይሎች የተላኩት ከናይጄሪያዋ ሌጎስ ከተማ መሆኑን የሚያረጋግጥ መረጃ ለእናቱ አሳያት። ብዙ ነገር አልተናገረችም። ከቀናት በኋላ አብዛኞቹን የኢሜይል መልዕክቶች አጠፋቻቸው። ሐዘን ገብቷት ነበር።
ካርሎስ፣ እናቱ ከብቸኝነት ጋር ስትታገል ማየቱ በውስጡ አንዳች ነገር ጫረበት። ወደ ናይጄሪያ ተጉዞ ድብቁን አጭበርባሪ ለማግኘት ወሰነ።
"ያሁ ቦይስ"

የፎቶው ባለመብት, Carlos Barragán
ካርሎስ አካባቢውን በሚያውቅ ሰው አማካኝነት ናይጄሪያ ውስጥ ባገኘው ቢጊ የተባለ አጭበርባሪን ተዋወቀ። ቢጊ ደግሞ ከጓደኞቹ ጋር ሊያስተዋውቀው እንዲሁም "ሁሉም ሰው ገንዘብ ለማግኘት የሚሯሯጥበት" ኢኮቱን የተባለ የሌጎስ ሰፈርን ሊያሳየው ተስማማ።
በ20ዎቹ መጨረሻ ላይ የሚገኘው ቢጊ፣ ከካርሎስ ጋር እኩያ ናቸው። ብልህ እና "እጅግ ተጫዋች" ነው።
ካርሎስ አብዛኛውን ጊዜውን ከቢጊ ጋር ባሳለፈ ቁጥር፣ በአስገራሚ ሁኔታ ይቀርበው ጀመር።
"እንደ እርሱ ያለ ሰው እንዴት ሌሊቱን ሙሉ በኢንተርኔት ብቸኛ ሰዎችን ሲያወራ የሚያድር አጭበርባሪ ሆነ?" ብሎ ያስብ እንደነበር ይናገራል።
ካርሎስ የአካባቢውን ሰዎች ሲያነጋገር ሰፊ የአጭበርባሪዎች መረብ እንዳለ ተረዳ። 'ያሁ ቦይስ' በመባል የሚታወቁት እነዚህ ወጣቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ መሆናቸውን ተገነዘ። አጭበርባሪዎቹ ይህንን መጠሪያ ያገኙት በፊት ይጠቀሙበት በነበረው 'ያሁ' የኢሜይል አገልግሎት ምክንያት ነው።
ካርሎስ ከሐሰተኛ ስም እና ኢሜይል አድራሻ ብቻ ይዞ ከ240 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ባላት ናይጄሪያ ውስጥ የሚገኘውን የእናቱን አጭበርባሪ ማግኘት እንደማይችል በጊዜ ሂደት ተረዳ።
በምትኩም ስለ 'ያሁ ቦይስ' ዓለም እያጠና ራሱን አገኘው።

የፎቶው ባለመብት, Carlos Barragán
ነጭ አውሮፓዊ የሆነው ካርሎስ በሂደበት ተለይቶ ይታይ ነበር። ብዙ ሰዎችም የኤፍቢአይ ወኪል ወይም ቻይናዊ የንግድ ሰው እንደሆነ ያስቡ እንደነበር ይናገራል።
ሰዎች የሚጠሩት "ማጋ" ብለው ነበር፤ ቀላሉ ሊታለል የሚችል ሞኝ ሰው ማለት ነው።
እንዲያም ሆኖ ግን በቢጊ አማካኝነት ማጭበርበር ላይ የተሰማሩ 50 ወጣቶችን ማነጋገር ችሏል።
ከአጭበርባሪዎቹ አንዱ ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኘው 300 ዩሮ ነበር። ይህ የገንዘብ መጠን ለአንድ ዓመት ተኩል ፋብሪካ በሰራበት ጊዜ ከተከፈለው የሚበልጥ ነበር።
የሚጭበረበር ሰው ግን በቀላሉ አይገኝም። "በመቶዎች ካልሆነም በሺህዎች በሚቆጠሩ ሰዎችን መሞከር ይኖርብሃል" ይላል ካርሎስ።
ካርሎስ በ14 ዓመቱ ማጭበርበር ከጀመረው አዚዝ የተባለ ሌላ 'ያሁ ቦይ' ጋር ተቀራረበ። ከገጠር ወደ ሌጎስ የመጣው አዚዝ፣ ከእናቱ እና ከሕፃን እህቱ ጋር በጠባብ የአፓርታማ ክፍል ውስጥ ይኖራል።
አዚዝ የአንዲት ቆንጆ ነጭ ሴት ፎቶን በመጠቀም እና ስሙ 'ቫኔሳ' እንደሆነ በመግለጽ ከአሜሪካውያን ወንዶች ጋር ይተዋወቃል።
መጀመሪያ ላይ አልተሳካለትም። እንግሊዘኛው እምብዛም ነበር፤ ፍቅረኛ ይዞም፣ አሜሪካ ሄዶም አያውቅም ነበር።
ካርሎስ "እያወራን ያለነው ስለ ምዕራቡ ዓለም ብዙም ዕውቀት ስለሌላቸው ትናንሽ ልጆች ነው" ይላል።
አዚዝ በጊዜ ሂደት አዚዝ የመጀመሪያውን 5 ዶላር አገኘ። ምግብ ቤት ሄዶ ዶሮ በላበት።
ትምህርት ያልቀመሱ የመንገድ ላይ ምግብ ሻጮች የሆኑት የአዚዝ እናት እና አያት ግን የሚያደርገው ነገር ስህተት መሆኑን ተረድተው ነበር። አያቱ ማጭበርበር የማያቆም ከሆነ ከቤተሰቡ እንደሚባረር የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጡት።
ከዚያ ጊዜ አንስቶ አጭበርብሮ አያውቅም።

የፎቶው ባለመብት, Carlos Barragán
ካርሎስ ወደ ናይጄሪያ ሲጓዝ፣ አጭበርባሪዎቹ ውስብስብ የሆነ የወንጀል ቡድን አካል ይመስሉት እንደነበር ይናገራል። ከአዚዝ ጋር የፈጠረው ግንኙነት ግን ይህንን ግምቱን መልሶ እንዲያጤነው አስገድዶታል።
"ስልኩን ከያዘ ከዚህ ልጅ ይልቅ በምዕራብ አፍሪካ የሚገኝ ኃይለኛ የወንጀል መረብ እየጎዳን ነው ብሎ ማመን ይቀላል" ይላል።
ካርሎስ፣ እነዚህ ወጣቶች ራሳቸው ሲጭበረበሩ ተመልክቷል። በማጭበርበር ያገኙትን ገንዘብ ይዘው የሚታዩት እነዚህ ወጣቶች ራሳቸውን የሌሎች ኃይለኛ ወንጀለኞች ሰለባ ይሆናሉ።
አሁንም ግን አንድ ጥያቄ ምላሽ አላገኘም፤ ትምህርታቸውን እንኳ ያላጠናቀቁ ታዳጊዎች እንደ ካርሎስ እናት ያሉ አዋቂዎችን እንዴት ማሳመን ቻሉ?
አጭበርባሪዎቹ ለሰዎቹ የሚያቀርቡት ብዙዎች ያጡትን 'ጥልቅ ትስስር' እንደሆነ ለካርሎስ ነግረውታል።
"'ትኩረት መስጠት ብቻ ነው ያለብህ' ይሉኝ ነበር። ከጎናቸው የመገኘት ጉዳይ ነው። 'እንዴት አደርሽ? የኔ ፍቅር እንዴት ነሽ? ማሬ እንደምን አለሽ? ምሳ ምን በላሽ?' እያሉ መጠየቅ ነው" ሲል ከእነርሱ የሰማውን ያስረዳል።
ይህ ከሰዎች ጋር ትስስር የመፈለግ ጉዳይ ከብቸኝነት የሚመነጭ እንደሆነ ይናገራል። ካነጋገራቸው የተጭበረበሩ ሰዎች ውስጥ ብዙዎቹም ይህንን እንዳነሱለት ይጠቅሳል።
አንድ የማጭበርበር ሰለበ፣ "ይህንን በዓለም ላይ እጅግ አሳዛኙ ወንጀል የሚያደርገው የሚወስዱት ገንዘብህን ብቻ አለመሆኑ ነው። ስሜትህን ጭምር አሟጠው ይጨርሱታል። ያ ሰው በድንገት ሲጠፋ የሚሰማህ ባዶነት አለ። ማኅበረሰቡ ደግሞ ሞኝ እንደሆንክ እና ጥፋተኛው አንተው እንደሆንክ ይነግርሃል" ሲል ለካርሎስ ነግሮታል።
ካርሎስ የናይጄሪያ አጋጣሚውን በተመለከተ 'ዘ ያሁ ቦይስ' (The Yahoo Boys) የሚል መጽሐፍ አሳትሟል።















