በኡጋንዳ የኢቦላ ወረርሽኝ እየተስፋፋ መሆኑ ተነገረ

ታትሟል

ከአንድ ሳምንት በፊት በበሽታው የተያዘ ግለሰብ በተገኘባት ኡጋንዳ በኢቦላ እንደተያዙ የሚጠረጠሩ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው።

የአገሪቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንዳለው አስካሁን 34 በበሽታው የተጠረጠሩ ሰዎች እንዳሉ ሲገልጽ፣ 21 ሰዎች በኢቦላ ቫይረስ ሳይሞቱ አይቀርም ብሎ ያምናል።

የጤና ባለሙያዎች በበሽታው ከተያዙ ሰዎች ጋር ንክኪ ያላቸውን ለማግኘት ማፈላለጋቸውን እንደቀጠሉ ባለሥልጣንት ገልጸዋል።

ወረርሽኙ የጀመረው በማዕከላዊ ኡጋንዳ ሙቤንዴ ወረዳ ቢሆንም ወደ ሁለት አጎራባች ወረዳዎች ተዛምቷል።

ነገር ግን በአገሪቱ ርዕሰ መዲና ካምፓላ በኢቦላ ተያዘ ሰው ስለመኖሩ እስካሁን የተረጋገጠ ነገር የለም።

ኡጋንዳ የኢቦላ ወረርሽኝ ሲያጋጥማት ይህ ለአራተኛው ጊዜ ነው።

ይህን ተከትሎ ጎረቤት አገራት በሽታው ወደ ግዛታቸው እንዳይዛመት በተጠንቀቅ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

እንደ ዓለም ጤና ድርጅት ከሆነ ኢቦላ በቫይረስ የሚተላለፍ በሽታ ሲሆን የመጀመሪያ ምልክቶቹም ድንገተኛ ትኩሳት፣ ከፍተኛ ድካም፣ የጡንቻ እና የጉሮሮ ቁስለት ናቸው።

ይህ የበሽታው የመጀመሪያ ምልክት ሲሆን በመቀጠልም ማስታወክ እና ማስቀመጥን ጨምሮ አንዳንዴ ውስጣዊ እና ውጫዊ መድማት ያጋጥማል።

እንደ ቺምፓንዚ ያሉትን ጨምሮ ቫይረሱ ካለባቸው እንስሳትን ጋር ቀጥተኛ ንክኪ ሲኖር ቫይረሱ ወደ ሰዎች ይተላለፋል።

ከሰዎች ወደ ሰዎች ደግሞ የሚተላለፈው በደም ንክኪ፣ ከሰውነት በሚወጣ ፈሳሽ እና በቫይረሱ ከተበከለ አካባቢ ጋር በሚኖር ግንኙነት ይተላለፋል።

በቫይረሱ ሕይወቱ ያለፈ ግለሰብ አስከሬንንን መንካትም ለቫይረሱ ያጋልጣል።

ቫይረሱ ምልክት ለማሳየት ከሁለት እስከ ሦስት ሳምንት ሊፈጅበት ይችላል።

ህክምናውም ቢሆን አስቸጋሪ የሚባል ነው።

በሽታው በአፍሪካ ተደጋግሞ ሲያጋጥም አንድ ጊዜ ደግሞ በፊሊፒንስ መከሰቱ ታውቋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ከኢቦላ ራስን ለመጠበቅ በሽታው ካለባቸው ሰዎች እና ከሰውነታቸው ከሚወጣ ፈሳሽ ጋር አለመነካካትን እንደ መፍትሔ ያቀርባል።

የጋራ መገልገያዎችንም አለመጠቀምንም ይመክራል።

በበሽታው ከተያዙ ደግሞ ራስን በመለየት የባለሙያዎችን ድጋፍ መጠየቅ ይገባል።

ሕክምናውን በደንብ በፍጥነት ከተከታተሉ ህሙማን የመዳን ተስፋ አላቸው።