ሆርሙዝ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ካልተከፈተ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ለረሃብ ይጋለጣሉ ተባለ
የሆርሙዝ ወሽመጥ በቶሎ ተከፍቶ የማዳበሪያ ምርት በባሕረ ሰላጤው መተላለፍ ካልቻለ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የምግብ እጥረት እና ረሃብ እንደሚገጥማቸው አንድ የተበባሩት መንግሥታት ባለሥልጣን ተናገሩ።
ባለሥልጣኑ ለፈረንሳይ የዜና ወኪል ኤኤፍፒ እንደተናገሩት ወራት ባስቆጠረው የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ምክንያት በሆርሙዝ በኩል የሚደረገው የመርከቦች እንቅስቃሴ መስተጓጎሉ ለእርሻ ምርት አስፈላጊ የሆነውን የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት አደናቅፎታል።
ስለዚህም በጥቂት ሳምንታት ውስጥ የሆርሙዝ ወሽመጥ ተከፍቶ የአፈር ማዳበሪያ ምርት እና ግብዓት እንዲያልፍ ካልተፈቀደ የምግብ ምርት መስተጓጎል እና ረሃብ ሊያስከትል እንደሚችል የመንግሥታቱ ድርጅት የፕሮጀክቶች ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት ዮርግ ዳ ሲልቫ ተናግረዋል።
ባለሥልጣኑ "ከፍተኛ የሰብአዊ ቀውስ ሊሆን የሚችለውን ችግር ለመቀልበስ ያሉን ጥቂት ሳምንታት ብቻ ናቸው” ሲሉ ለዜና ወኪሉ ገልጸዋል።
አክለውም በጦርነቱ ሰበብ የአፈር ማዳበሪያ ምርቱ አቅርቦት በመስተጓጎሉ "ተጨማሪ 45 ሚሊዮን የሚሆኑ ተጨማሪ ሰዎችን ለምግብ እጥረት እና ለረሃብ የሚዳርግ ቀውስ ሊገጥመን ይችላል” ብለዋል።
ባለፈው የካቲት ወር ማብቂያ አካባቢ በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት ኢራን እና አሜሪካ በወሳኙ የባሕር መተለላፊያ የሆርሙዝ ወሽመጥ የጭነት መርከቦች እንዳይንቀሳቀሱ የሚያደርግ እገዳ ጥለዋል።