የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት በመላ አገሪቱ "መረጋጋት እና ስርዓት" እንዲሰፍን ጥሪ አቀረቡ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ቅዳሜ ዕለት የተካሄደው ከፍተኛ የተቃውሞ ሠልፍ ወደ ብጥብጥ እና ዝርፊያ ከተቀየረ በኋላ እሁድ ዕለት በፓሪስ አንዳንድ አካባቢዎች ብጥብጥ መቀጠሉን ተከትሎ "መረጋጋት እና ስርዓት" እንዲሰፍን ጥሪ አቀረቡ።
ፕሬዝዳንቱ ከቤተ መንግሥታቸው ባስተላለፉት መልዕክት በሠልፉ ላይ የተሳተፉ ሰዎች አለመረጋጋቱን "እንዳይባባሱ" አስጠንቅቀው "ሁላችንም ቁጣና ኀፍረት ይሰማናል" ሲሉ አክለዋል።
ወደ 550,000 የሚጠጉ ተቃዋሚ ሠልፈኞች የነዳጅ ዋጋ መጨመርን፣ የኑሮ ውድነትን እና ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ የሕዝብ አገልግሎቶችን እያሽቆለቆሉ በመምጣታቸው አደባባይ ወጥተው ድምጻቸውን አሰምተዋል።
ማክሮን በተቃዋሚዎች "ሕጋዊ ጥያቄዎች" እና "ውድመት በፈጸሙ፣ በሰባበሩ እና በዘረፉት" መካከል ልዩነት መደረግ አለበት ሲሉ ተናግረዋል።
የፈረንሳይ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ፖሊስ ወደ 2,400 የሚጠጉ ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ይፋ አደርጓል።
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት "ከቁጥጥር ውጪ ለሆነው" ለዚህ ጥቃት ምንም ዓይነት "ምክንያት ሊቀርብለት አይችልም" ብለው ተሳታፊዎቹ ሕግ ፊት እንደሚቀርቡ ተናግረዋል።
በፓሪስ፣ ማርሴይ እና በሌሎች ከተሞችም የተቃውሞ ሠልፈኞች ቡድኖች፣ አንዳንዶቹ ጥቁር ለብሰው፣ ጭንብል አጥልቀው መኪኖችንና ሕንፃዎችን አቃጥለዋል።
እሁድ ዕለት በዋና ከተማዋ እና በሊዮን ዝርፊያ እና ግጭት በአነስተኛ መጠንም ቢሆን ቀጥሎ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በፓሪስ በመቶዎች በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ የአስለቃሽ ጋዝ እና የአድማ ብተና ጥይቶች ተተኩሰዋል ሲል የኤኤፍፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ተቃዋሚ ሠልፈኞችም ጠርሙሶችና ድንጋዮች ወደ ፖሊስ ተወርውረዋል።
እሁድ ዕለት በመላ አገሪቱ የሚገኙ ከተሞች በዘመናዊ የፈረንሳይ ታሪክ ውስጥ እጅግ የከፋው አመጽ ነው የተባለ ተቃውሞ አስተናግደዋል።
በሊሞጅስ በ19ኛው ክፍለ ዘመን የተገነባው የከተማዋ አዳራሽ ቅዳሜ ዕለት በአመጸኛ ሠልፈኞች በእሳት ወድሟል።
በሕንጻው ላይ የተሰቀለው ግዙፍ ሰዓት እና የአዳራሹ ጣሪያ ወድቀዋል።
አኔይሴ የተባለች ነዋሪ በፈረሰው ሕንፃ አቅራቢያ ሆና "ይህ በጣም ያሳዝናል። በመንግሥት ላይ ስለተቆጣህ ብቻ ቅርሶችን መጉዳት ራስ ወዳድነት ይመስለኛል። ሁሉንም ሰው እየጎዳ ነው" ብላለች።
"በጣም አስፈሪ እና የማይታመን ነው" ያለው ጄራርድ ደግሞ "በጣም አዝነናል፤ እንደበፊቱ መልሰን ለመገንባት ረጅም ጊዜ እንደሚወስድብን አስባለሁ" ሲል ተናግሯል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የቆሻሻ መኪናዎች በአንዳንድ ትላልቅ ጎዳናዎች ላይ ፍርስራሾችን ሲያጸዱ፣ እሁድ ማለዳ ላይ የሱቅ ባለቤቶች በፓሪስ ትላልቅ የመስታወት ስብርባሪዎችን ሲያነሱ ታይተዋል።
በፓሪስ፣ ማርሴይ እና ሊል ከተሞች እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች በስፋት ዝርፊያ ተፈጽሟል።
ማክሮን እንዳሉት የአካባቢው አስተዳዳሪዎችና ከንቲባዎች ሱቆችንና የሲቪክ ሕንፃዎችን ለመጠበቅ እርምጃዎችን ይወስዳሉ።
ፕሬዝዳንቱ በተጨማሪም ፖሊስ ሠልፎቹ ላይ የወሰደውን እርምጃ በተመለከተ "ሙሉ ግልጽነት" እንደሚኖር ተናግረዋል።
ቅዳሜና እሁድ በሕዝቡ ላይ የአስለቃሽ ጋዝና ውሃ የረጩ ሲሆን አድማ በታኝ ፖሊሶችም በተለያዩ ቦታዎች ሰዎችን በዱላ ሲመቱ ታይተዋል።
የፈረንሳይ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ቅዳሜ ዕለት 1,000 የሚያህሉ የፖሊስ መኮንኖች እንደቆሰሉ እና ከእነዚህ ውስጥ ሰባቱ ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጿል።
ባለፈው ወር የተጀመረው የተማሪዎች ተቃውሞ ቅዳሜ ዕለት የሠራተኛ ማኅበራት አባላትና ሌሎች ፀረ-መንግሥት ቡድኖች ከተቀላቀሉ በኋላ ወደ አመጽ ተሸጋግሯል።



































