በሕንድ ክርስቲያኖች ወደ ቤተ እምነታቸው ሲሄዱ በፈቃዳቸው ስለመሆኑ እንዲፈርሙ የሚጠየቁት ለምንድን ነው?

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
የሕንድ የንግድ ከተማ የሆነችው ሙምባይ እና በሌሎች አካባቢ ምዕመናን ወደ ቤተ ክርስትያን ሲመጡ "ወደዚህ ለመፀለይ የመጣሁት በገዛ ፈቃዴ ነው" ብለው እንዲፈርሙ ይጠየቃሉ።
ምዕመናኑ ሙሉ ስማቸውን አንዳንዴ የመታወቂያቸውን ቁጥር አስፍረው ቤተክርስትያን ለመምጣት ማንም እንዳላስገደዳቸው ገልጸው ፊርማቸውን ያኖራሉ።
ቢቢሲ የተመለከተው ይህ ሰነድ ሕጋዊ የመንግሥት ሰነድ አይደለም። አብያተ ክርስቲያናት ይህን ሰነድ አስፈርመው የሚይዙት፣ የአምልኮ ሥርዓታቸው ተቃውሞ ቢገጥመውና አባላቱ በቤተ ክርስትያን ውስጥ ያገኟቸውን ሰዎች እምነታቸው ለማስለወጥ በመሞከር ቢከሰሱ ለመከላከል ነው።
ይህ የተጀመረው በሙምባይ ስር በምትገኘው ማሃራሽትራ ሃይማኖትን መቀየር የሚከለክል አዲስ ሕግ ተግባራዊ መሆኑን ተከትሎ ነው።
ሕጉ በኃይል፣ በማታለል፣ በግፊት ወይም በተለያዩ ማባበያዎች የሚደረጉ የሃይማኖት ለውጦችን ይከለክላል።
እንዲሁም በፈቃደኝነት ሃይማኖታቸውን ለመቀየር የሚፈልጉ ሰዎች ለሚመለከታቸው አካላት አስቀድመው ማሳወቅ እንዳለባቸው ይደነግጋል።
ሕገ ወጥ የሆነ የሃይማኖት ለውጥ እስከ ሰባት ዓመት የሚደርስ የእስር ቅጣት ሊያስከትል የሚችል ሲሆን ድርጊቱ ሲደገም ደግሞ ቅጣቱ እስከ 10 ዓመት ሊደርስ ይችላል።
የማሃራሽትራ አስተዳደር እንደሚለው ይህ ሕግ ሰዎችን በተለይም በማኅበራዊ ወይም በኢኮኖሚ ተጋላጭ የሆኑትን ሃይማኖታቸውን እንዲቀይሩ በግዴታ ወይም በማታለል ከመገፋፋት ይጠብቃል።
ይሁን እንጂ ተቺዎች እንደሚሉት ሕጉ ያካተታቸው አንቀጾች ያላቸው ሰፊ ትርጓሜ እና ከባድ ቅጣቶች በፈቃደኝነት የሚደረጉ የሃይማኖት ለውጦችን ያግዳሉ።
አክለውም መንግሥት እና ፖሊስ የአንድ ሰው የግል ውሳኔ ውስጥ ጣልቃ እንዲገቡ ይፈቅዳል ሲሉ ይሞግታሉ።
ቢቢሲ ለግዛቲቱ አስተዳዳሪ በተደጋጋሚ ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ አላገኘም።
ዴቭዳን ትሪቡቫን የምዕመናኑን ጭንቀት በቅርበት አይቷል።
ክርስቲያን የሆነው ትሪቡቫን በሙምባይ ውስጥ ላሉ ማኅበረሰቦች የሕግ ድጋፍ የሚሰጥ ድርጅት አባል ነው። ከቅርብ ወራት ወዲህ በርካታ ክርስትያኖች ስለተመሰረተባቸው ክሶች ሳይሆን ስለተስተጓጎሉ አምልኮዎች እና ምን ለማድረግ ነፃ እንደሆኑ ምክር ለመጠየቅ በተደጋጋሚ አግኝተውታል።
አንዳንዶች ወደ ቤተክርስቲያኖቻቸው አባል ያልሆኑ ሰዎች መጥተው ያገኙትን "ስምህ ማን ነው? እዚህ ምን ትሰራለህ? ማባበያ የሰጠህ ሰው አለ?" የሚሉ ጥያቄዎችን እንደሚያቀርቡ ነግረውታል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ትሪቡቫን አንድ ምዕመን የክርስቲያን የማይመስል ስም ሲኖረው ጥያቄዎቹ የበለጠ እርሱ ላይ እንደሚያነጣጥሩ ያስረዳል።
"ወደዚህ እንድትመጣ ያስገደደህ ሰው አለ? ማባበያ ተሰጥቶሃል?" የሚሉ ጥያቄዎችም እንደሚቀርቡለት ጨምሮ ገልጿል።
ወደ እርሱ የሚመጡት ብዙዎቹ ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ አይፈልጉም። ነገር ግን ለመፀለይ መሰብሰብ ብቻ በሃይማኖት ለውጥ ሕጉ መሠረት እንዲከሰሱ ያደርጋቸው እንደሆነ ማወቅ ይፈልጋሉ።
በሐምሌ ወር 'ዘ ኢንዲያን ኤክስፕረስ' የሠራው የምርመራ ዘገባ ባለፈው ዓመት ከሚያዝያ እስከ ሐምሌ ባሉት አራት ወራት በሙምባይ ዙሪያ አምስት የክርስቲያኖች የአምልኮ ስብሰባዎች መስተጓጎላቸውን ዘግቧል።
ፖሊስ ዘጠኝ ክሶችን መመስረቱ በዘገባው ላይ ተመልክቷል።
ከእነዚህ ክሶች መካከል ሰባቱ በአምልኮ ላይ በነበሩ ግለሰቦች ወይም በአገልጋዮቹ፣ ሁለቱ ደግሞ በሂንዱ ብሔር ቡድን ባጅራንግ ዳል አባላት ላይ ነው የተመሰረቱት። ፖሊስ ስለክሶቹ ወይም ስለተወሰደው እርምጃ ዝርዝር መረጃዎችን ቢጠየቅም ምላሽ አልሰጠም።
"ለጸሎት መሰብሰብ ራሱ ሃይማኖትን መቀየር ነው?" ሲል ትሪቡቫን ጠየቀ።
በሙምባይ የትሪቡቫን ጥያቄ በጣም ወሳኝ ነው። ከተማዋ ያደገችው ከመላው ሕንድ እና ከተለያዩ አካባቢዎች በመጡ ሰዎች ነው።
እነዚህ ነዋሪዎች የማምለኪያ ሥፍራዎች ይገነባሉ እንዲሁም የአምልኮ ሥርዓቶቻቸውን ያከናውናሉ። የቤተክርስቲያን ደወል ከመስጊድ አዛን እኩል ሊሰማ ይችላል፤ የአንድ እምነትን የማምለኪያ ስፍራ የሌላ እምነት ተከታዮች ሊጎበኙ ይችላሉ።
የተለያዩ እምነት ተከታዮች የሙስሊም አባት ወደ ሆኑት ሀጂ ይጎርፋሉ። ሂንዱዎች በከተማዋ በሚገኘው የካቶሊክ ማርያም ቤተክርስትያን ሻማ ያበራሉ። በሂንዱ የጋኔሽ ቻቱርቲ ክብረ በዓል ወቅት በላልባውግ ዙሪያ ያሉትን ጎዳናዎች የተለያየ እምነት ባላቸው ሰዎች ይሞላሉ። ዓመቱን ሙሉም ወደ ሲዲሂቪናያክ ቤተመቅደስ ይጎርፋሉ።
ማሃራሽትራ የሃይማኖት ለውጥን ከገደቡ ከአስራ ሁለት በላይ ግዛቶች መካከል የመጨረሻዋ ናት።
ሕጎቹ የተለያዩ ናቸው፤ ነገር ግን በቅርብ ዓመታት ውስጥ በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ባራቲያ ጃናታ ፓርቲ በሚተዳደሩ ግዛቶች ውስጥ ተፈጻሚነታቸው ሰፍቷል። በርካቶች በጠቅላይ ፍርድ ቤት ፊት ቀርበው የቀረበባቸውን ክስ ተከታትለዋል።
ከዚህ የሕግ ተፈጻሚነት መስፋት በስተጀርባ የሂንዱ ብሔርተኛ ቡድኖች ለረዥም ጊዜ ሲያቀርቡት የነበሩት ክሶች ይገኛሉ።
ክርስቲያኖች ድሆችንና የተለያዩ ጎሳ አባላትን ከሂንዱ እምነት ለማራቅ ገንዘብ፣ ትምህርት ወይም የሕክምና አገልግሎት ይጠቀማሉ የሚለው ቀዳሚው ነው።
ሌላው ሙስሊም ወንዶች የሂንዱ ሴቶችን አግብተው እምነታቸውን እንዲቀይሩ ያበረታታሉ ይህም "የፍቅር ጂሃድ" ይባላል ሲሉ ይወነጅላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ተቺዎች እንደሚሉት እንዲህ ያሉት ክሶች ፖሊስ የክርስትያኖችን አምልኮ እንዲያደናቅፍ፣ የተለያየ ሃይማኖት በሚከተሉ ጥንዶች መካከል በሚፈጸመው ጋብቻ ጣልቃ እንዲገባ መንገድ የሚከፍት መሆኑን ይናገራሉ።
የማሃራሽትራ አስተዳደር አዲሱ ሕግ ሰዎች በምርጫቸው ሃይማኖታቸውን እንዲቀይሩ ነፃነት እንደሚሰጥ ተናግሯል።
አክሎም አሁን ያሉትን ሕጎች ማስቆም ያልቻሉትን በግዴታ ሃይማኖት የማስለወጥ ተግባር መጨመር ለመግታት ይህ ሕግ እንደሚያስፈልግ ይገልጻል።
ተቺዎች በኃይልና በምርጫ መካከል ያለውን መስመር የት ላይ ነው ሲሉ ይጠይቃሉ።
"በኃይል የሚደረጉ ለውጦችን አንደግፍም" ሲሉ የሙስሊም ሳቲያሾዳክ ማንዳል ፕሬዝዳንት ሳምሱዲን ታምቦሊ ተናግረዋል። የእርሳቸው ስጋት ሕጉ እንደ ማበረታቻ የሚቆጥረው ነገር ነው።
ሕጉ "መማረክ/መሳብ" ለሚለው የሚሰጠው ሰፊ ትርጉም ነው። ይህም የሥራ ቅጥርን፣ በሃይማኖታዊ ተቋም የሚሰጥ የነጻ ትምህርትን፣ የጋብቻ ቃል ኪዳንን፣ "የተሻለ ሕይወት" ወይንም "የፈውስ አገልግሎትን" ያካትታል" ካሉ በኋላ አንድን እምነት ከሌላው አስበልጦ ማሞካሸት ራሱ በዚህ ብያኔ ስር ይወድቃል ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
የቦምቤይ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ የነበሩት አብሃይ ቲፕሴይ "የቃሉ ፍቺ በጣም ግልጽ ስላልሆነ ለአንድ ሰው የሚሰጥ ማንኛውም ጥቅማ ጥቅም ያንን ሰው ወደ ሃይማኖቱ ለመሳብ እንደሆነ ተደርጎ ሊወሰድ ወይም ሊቀርብ ይችላል" ብለዋል።
"አንድ ሰው የተወሰነ ጥቅም ካገኘ እና በዚያ ምክንያት ሆን ብሎ ለመለወጥ ከመረጠ፣ ለምን የተሳሳተ እንደሆነ ሊቆጠር ይገባል?" ሲሉም ይጠይቃሉ።
ሕጉ ወላጆች፣ ወንድሞች እና እህቶች እንዲሁም ሌሎች ዘመዶች ሕገ ወጥ የእምነት ለውጥ አለ ብለው ሲያምኑ ለፖሊስ ጥቆማ እንዲሰጡ ያበረታታል። ይህም ድርጊቱን በማነሳሳት ወይም በመርዳት የተከሰሰው ግለሰብ ሕጋዊ መሆኑን እንዲያስረዳ ያስገድዳል።
ሕጉን የሚነቅፉ አካላት እንደሚሉት ይህ ሕግ ቀድሞውኑ ከቤተሰብ ተቃውሞ የሚገጥማቸውን ከተለያየ ሃይማኖት የሚመጡ ጥንዶችን ተጨማሪ ተግዳሮት እንዲገጥማቸው ያደርጋል።
የሕንድ ሕግ የተለያየ እምነት ያላቸው ሰዎች ሃይማኖታቸውን ሳይቀይሩ ጋብቻ እንዲፈጽሙ ይፈቅዳል። ነገር ግን ከአንድ ወር በፊት ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል።
የተለያዩ እምነት ተከታይ ሆነው ትዳር የመሠረቱ ጥንዶችን የሕግ ከለላ እንዲያገኙ የረዳችው ጠበቃ ላራ ጄሳኒ፣ ትዳር ለመመስረት ያሰቡ ሰዎች ዝርዝር በዚያ የማሳወቂያ ጊዜ ውስጥ ለዘመዶች እና ለሂንዱ ብሔርተኛ ቡድኖች ደርሰው ተቃውሞ እንደሚያስተናግዱ ታስረዳለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጠበቃ ላራ ጄሳኒ ተበዳዮችን ወክላ ፍርድ ቤት በቆመችባቸው ጊዜያት ቤተሰቦች ሴቶችን ከወሳኝ ኩነት ቢሮ ሲወስዱ መመልከቷን ትናግራለች።
አዲሱ ሕግ ቤተሰቦችን ወይም አክራሪ ቡድኖች የተለያየ እምነት ያላቸው ጥንዶችን ዒላማ እንዲያደርጉ አዲስ መንገድ ይከፍታል ስትል ትፈራለች።
"ሁለቱም ጥንዶች ሃይማኖታቸውን ለመለወጥ ባያስቡም እንኳ [ጥንዶቹ] አንዱ ዘመዳቸው ሃይማኖታቸውን ለመለወጥ እያሰቡ ነው ብሎ ይከስሰናል ሲሉ ይሰጋሉ።"
የማሃራሽትራ መንግሥት ስለእነዚህ ስጋቶች ከቢቢሲ ለቀረቡለት ዝርዝር ጥያቄዎች ምላሽ አልሰጠም።
ነገር ግን ሕጉ ሲፀድቅ ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑት ፓንካጅ ቦያር ይህ ሃይማኖትን የመቀየር መብትን የሚጥስ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
የአንድ ወር የማሳወቂያ ጊዜ የሃይማኖት ለውጡ በፈቃደኝነት የተፈጸመ መሆኑን ለማረጋገጥ፣ በማጭበርበር፣ በማስገደድ ወይም በማባበል የሚደረጉ የሃይማኖት ቅየራዎች ላይ መንግሥት እርምጃ እንዲወስድ ለማስቻል የታሰበ መሆኑን ተናግረዋል።
ነገር ግን ትሪቡቫን አሁንም ስጋት እና ፍርሃት አለው። ይህም ቤተ ክርስቲያን በጣም ርቆ በሚገኝበት አካባቢ በመኖሪያ ቤት አቅራቢያ የሚደረጉትን ትናንሽ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን እና ፀሎቶችን ያሰጋል የሚል ነው።
ሃምሳ ሰዎች አንዳንድ ጊዜ 100 በጉባዔው ላይ ሊታደሙ እንደሚችሉ እና ክርስቲያን ያልሆነ ሰውም እንደሚሳተፍ ይናገራል።
"ሌላ ሰው መጥቶ ሊፀልይ ከፈለገ ልናስቆመው አንችልም" ካለ በኋላም "ይህንን ነው የመምረጥ መብት ብለን የምንጠራው" ብሏል።
ጡረታ ለወጡት ዳኛ ቲፕሴይ ደግሞ ሕጉ ወደ አንድ ትልቅ ጥያቄ ይመራል።
"አንድ አዋቂ ሰው ማንን ማግባት እንዳለበትን የመሳሰሉ ትላልቅ ውሳኔዎችን የመወሰን ሥልጣን ካለው እና የመምረጥ መብት ከተሰጠው ለምን ይህን ውሳኔ የማሳለፍ ሥልጣን ይነፈጋል?" ሲሉ ጠይቀዋል።



































