ወላጆች የልጆቻቸው ሕይወት እስከሚያልፍ ድረስ እንዲጾሙ አስገድደዋል የተባሉት ፓስተር ፍርድ ቤት ቀረቡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፖል ማኬንዚ የተባሉት የኬንያ ፓስተር የዓለም መጨረሻ ደርሷል በማለት የበርካታ ሰዎች ሕይወት እንዲያልፍ አድርገዋል በሚል ፍርድ ቤት ቀርበዋል።
ማኬንዚ እና 29 የሚሆኑ ተከታዮቻቸው የ191 ሰዎችን ሕይወት በማጥፋት ክስ ቀርቦባቸዋል። ከሟቾቹ ውስጥ ከአንዱ በስተቀር ሁሉም ሕፃናት ናቸው።
ፓስተሩ ከፈጣሪ ጋር ለመገናኘት እንድትችሉ በሚል ሕፃናቱ ሕይወታቸው እስከሚያልፍ ድረስ እንዲጾሙ ማድረጋቸው ተገልጿል።
የዓለም ፍጻሜን የተመለከተው የፓስተሩ አስተምህሮት ዘመናዊ መድኃኒቶችን እንደ “መጥፎ” የሚቆጥር እና ትምሕርትን የሚከለክል ነው።
ማኬንዚ እና 29 ተከታዮቻቸው በቀረበባቸው የግድያ ክስ ጥፋተኛ አይደለንም ሲሉ ክሱን ውድቅ ያደረጉ ሲሆን ማንም እንዲሞት አልተገደደም በማለት ተናግረዋል።
የአገሪቱ ባለሥልጣናት እንደተናገሩት፤ ማኬንዚ ከተለያየ አካባቢ የሚመጡ ተከታዮችን በሚመሩበት በኬንያ የባሕር ዳርቻ በሚገኝ ሻካሆላ ጫካ ውስጥ 400 አስክሬን ከመቃብር ውስጥ ተቆፍሮ ወጥቷል።
ከመቃብር ቆፋሪዎቹ ውስጥ ጀምስ የተባለ እማኝ “እያንዳንዱ መቃብር ቢያንስ 3 አስክሬኖች ነበሩት። አንዳንዱ አስክሬን የጥቂት ሳምታት ዕድሜ ያላቸው ሕፃናት ናቸው” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
“በመቃብሩ በአንድ ጊዜ 12 የሕፃናት አስክሬን ልክ እንደ ልብስ ተደርድሮ አግኝተናል” ሲልም የተመለከተውን ተናግሯል።
አንዳንዶቹ አስክሬኖች “እጅ እና እግራቸው የታሰሩ እንዲሁም በአንሶላ የተጠቀለሉ” መሆናቸው ተገልጿል።
ስቲፈን ማዊቲ የተባሉ የ 48 ዓመት እናት በማኬንዚ አስተምህሮ 6 ልጆጃቸው እንደሞቱባቸው ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Salim Karisa






