የመንግሥት ለውጥ - የሰሜኑ ጦርነት - የፓርላማ የምሬት ንግግር - ስደት ፡ የገዱ አንዳርጋቸው የለውጡ ስምንት ዓመታት

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 11 ደቂቃ

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በስደት አሜሪካ ከመግባታቸው በፊት በዚህ ዓመት መስከረም ማብቂያ ላይ በአዲስ ምክር ቤት የተተካው የቀደመው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የነበሩ ከመሆናቸው በተጨማሪ በክልል እና በፌደራል መንግሥቱ ውስጥ ከፍተኛ ባለሥልጣን ነበሩ።

አቶ ገዱ የአማራ ክልልን ከ2006 እስከ የካቲት 2011 ዓ.ም. ድረስ ለአምስት ዓመታት በርዕሰ መስተዳደርነት መርተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ ከሚያዝያ 2011 እስከ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም. ድረስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል። ከዚያም የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በተቀሰቀሰ ማግስት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደኅንነት አማካሪ ሚኒስትር ሆነው ነበር።

ከዚያ በኋላ ግን ከመንግሥት ጋር ያላቸው ግንኙነት እየሻከረ መጥቶ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዳይጣል በጥብቅ በመቃወም ንግግር ካደረጉ በኋላ ከአገር ወጥተዋል።

እዚያም ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ያጠናቀቁ ሲሆን፣ አሁን በአሜሪካ በስደት ይኖራሉ። ቢቢሲ ከሦስት ሳምንት በፊት መስረከም 17/2019 ዓ.ም. ከምክር ቤቱ ንግግር በኋላ ስላሳለፏቸው ወራት፣ ስለስደት ሕይወታቸው እና ተያያዝ ጉዳዮች ጠይቋቸዋል።

መስመር

ቢቢሲ አማርኛ፡ ወደ ስደት ከማምራትዎ በፊት የአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በመቃወም በፓርላማ መረር ያለ ንግግር አድርገዋል። ሃሳብዎን ለመጨረስ እየተማጸኑ ያደረጉት ንግግር ነበር። በወቅቱ የተሰማዎት ምን ነበር?

አቶ ገዱ፡ በ2013 ዓ.ም በተካሄደው ምርጫ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆኜ ተመርጬ ነበር። በዚያ ወቅት ከመንግሥት ጋር ያለኝ ግንኙነትም በከፍተኛ ሁኔታ እየሻከረ የነበረበት ጊዜ ስለነበር፤ ብዙም በፓርላማው ተሳትፌ አላውቅም። ምናልባት በጠቅላላው ሁለት ወይም ሦስት ቀን ሊሆን ይችላል የተሳተፍኩት።

ያኔ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አስቸኳይ ጊዜ ሲያውጅ እና ያንን ወደ ፓርላማው ሊያጸድቅ ይዞ ሲቀርብ በሕዝብ ላይ የጅምላ ሞት እንደታወጀ አድርጌ ነበር የተመለከትኩት።

እናም ዕድሉን ካገኘሁ ልናገር፣ ካላገኘሁ ቢያንስ እጄን አውጥቼ ተቃውሞ ማሰማት አለብኝ ብዬ ነበር ወደ ፓርላማ የገባሁት። ያው ስገባ በአጋጣሚ ዕድሉን አገኘሁ፤ ያንን ተናገርኩ። ያ ለእኔ ላደርግ የምችለው የመጨረሻው ነገር ነበር። ከዚያ ውጭ ላደርግ የምችለው ነገር አልነበረኝም፤ ማስቀረት አልችልም፤ ነገር ግን የራሴን ስሜት መግለጽ ነበረብኝ። ለኢትዮጵያ ሕዝብ መልዕክት ማስተላለፍ ነበረብኝ። በዚያ አጋጣሚ ያንን አደረኩ።

Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቢቢሲ አማርኛ፡ ከምክር ቤቱ እንደወጡ ማንን ነበር ያገኙት?

አቶ ገዱ፡ እዚያው ፓርላማው ወስጥ ተሳታፊ ከነበሩት ውስጥ ስወጣ ያገኘኋቸው የማልረሳቸው ሰዎች አሉ። "ክልሉ እንዲፈርስ ነው ወይ የምትፈልገው" ያሉኝ ሰዎች አሉ። እኔ ክልሉ በወታደራዊ መንገድ ይጠገናል ብዬ አላስብም። የእኔ ጥያቄ የነበረው መከላከያ ከክልሉ ይውጣ ወይም ወደ ካምፑ ይግባ እና ሰላማዊ በመሆነ መንገድ ንግግር ተደርጎ ይፈታ የሚል ነበር። የሕዝቡን ስሜት አውቀዋለሁ። ሕዝቡ በከፍተኛ ሁኔታ ተቆጥቷል። ያን የተቆጣ ሕዝብ የተወሰነ ጊዜ ማሰቃየት፣ መግደል ይቻላል፤ ግን በጉልበት ማንበርከክ አይቻልም የሚል እምነት ስለነበረኝ ያንን አስረድቻቸዋለሁ። ከሌላው ኅብረተሰብ ከብዙ ሰው ስልክ ተደውሎልኛል። ከባለሥልጣናት ግን የተደወለልኝ ወይም ያገኘኝ ሰው የለም።

ከዚያ በኋላ ግን የደኅንነት ሰዎች ተነጥለውኝ አያውቁም። ሁልጊዜ ቤቴ የሚመጡ ሰዎች "ምንድን ነው ያላቸው ግንኙነት" ተብሎ አንዳንዶች ስምንት ቀን የታሰሩ አሉ። ማንገራገር እንዲሁም አርፋችሁ ተቀመጡ ተብሎ የሚጠብቁኝ ልጆች ሳይቀሩ ማስፈራሪያ ይደርስባቸው ነበር። በሹፌርነት የሚያገለግለኝ የእህቴ ልጅ ነበር። ለዘጠኝ ቀን ከነመኪናው የት እንደወሰዱት ሳይታወቅ ለቀቁት። ምንም እንቅስቃሴ እንዳላደርግ ነበር ያን የሚያደርጉት።

በመጨረሻ ጳጉሜ 6/ 2015 ዓ.ም. የአሜሪካው የምሥራቅ አፍሪካ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሃመር ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ እርሱን ሃያት ሬጀንሲ ሄጄ ተነጋግሬ ስወጣ አምስት ስድስት መኪና የያዙ የፀጥታ ሰዎች መጥተው ቡልጋሪያ አካባቢ አውራ ጎዳና ላይ ከበቡኝ።

ጠባቂዬን ወሰዱ፤ መሣሪያውን ቀሙ፤ ስልኮቻችንን ወሰዱ፣ ሹፌሩን አስወረዱ፤ እኔንም በረበሩኝ ፣ የእጅ ስልኬን ወሰዱ። ትራፊኩ እና ሰው ሲጮህ ለቀውን ሄዱ። ልጆቹንም ዕቃውንም ይዘው ሄዱ። እኔ ወደ ቤት ሄድኩኝ። ከዚያ በኋላ ከቤት አልወጣሁም። በየቀኑ የደኅንነት ሰዎች ይመጣሉ። ሰው እስከሚተኛ ድረስ ይቆያሉ። በዚህ መንገድ የቁም እስር ዓይነት ነገር ላይ ሆኜ ነው የቆየሁት።

ቢቢሲ አማርኛ፡ በምክር ቤቱ መረር ብለው ሲናገሩ ይህ ይመጣብኛል የሚል ስጋት አልነበረዎትም?

አቶ ገዱ፡ ከ2014 ዓ.ም. አጋማሽ ጀምሮ የሚከታተሉኝ የደኅንነት ሰዎች እንደሚንቀሳቀሱ አውቃለሁ። ሰዎችም ፎቶግራፍ እያነሱ ይሰጡኝ ነበር። መረጃው ነበረኝ። ወደ ኋላ የአማራን ልዩ ኃይል ትጥቅ የማስፈታት እርምጃ ተከትሎ ተቃውሞ እየተጠናከረ በሚሄድበት ጊዜ በእኔ ላይ የነበረው ክትትልም እየተጠናከረ ሄደ።

ከሥራ ቦታ ወደ ቤቴ ነበር የምሄደው። አብዛኛውን ጊዜ ቤት ውስጥ ነበር የማሳልፈው። አንድ ምክንያት እየተፈለገልኝ እንጂ የሆነ ነገር ልደረግ እንደምችል ግምቱ ነበረኝ። እኔም ራሴን አሳምኛለሁ። እናም ምክር ቤቱ ውስጥ ለመናገር ሳስብ ግድያን ጨምሮ እስር ወይም ሌላ ነገር ሊመጣ ይችላል ብዬ ራሴን አሳምኘ ነው የተናገርኩት። የሚመጣውን መቀበል የህሊና እረፍት ነው ብዬ ነበር የማስበው።

ቢቢሲ አማርኛ፡ የቁም እስር ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የቆዩት በተፈጠረበዎት ስጋት እንቅስቃሴዎን ስለገደቡ ወይስ መንግሥት እንዳይንቀሳቀሱ ስለከለከለዎት?

አቶ ገዱ፡ ከቤቴ ግራ እና ቀኝ ሁለት መኪናዎች ሁልጊዜ ይመጣሉ። የፀጥታ ሰዎችን እናውቃቸዋለን፤ ይመላለሳሉ። ያው እንዳትወጣ ብለው ለማስፈራራት ነው። ለመውጣት ሞክሬ ነበር። አንድ ጊዜ የአውሮፓ ኅብረት አምባሳደር ጋር ቀጠሮ ነበረኝ። ወደ እርሱ ስሄድ፤ ተከተሉኝ። በግራ እና በቀኝ ሁለት መኪኖች ናቸው። ወደ በሩ አካባቢ ስቀርብ የማፈን እና የመክበብ ሁኔታ በሚመስል መንገድ አሰላለፋቸውን ሳይ እንደገና በሌላ መንገድ ዞሬ ወደ ቤቴ ተመልሼ ሄድኩ።

ዋናው ፍላጎታቸው ከሰዎች ጋር እንዳልገናኝ ማድረግ ነው እንጂ እንሰርህ ቢሉ፣ እንግደልህ ቢሉ፣ ሌላ ነገር እናድርግህ ቢሉ በእጃቸው ነው። ማን ከልካይ አላቸው። ሕግ የለ፤ ሥርዓት የለ፤ ምን የለ። እና ከቤት እንዳልወጣ ነበር ያን ሲያደርጉ የነበሩት። ባለቤቴ ወደ ቤተክርስቲያን ከሄደች 'ማን አለ' ብለው ይከተላሉ። ቤቴ እንግዳ መጥቶ ከሄደ ይከታተላሉ። ትንኮሳዎች ነበሩ። ቤቴ ውስጥ እንድቀመጥ የማድረግ ጫና ነበር። በእኔ ምክንያት አንድ ነገር ከሚሆኑ ብዬ ጠባቂዎቼንም ወዲያው ነበር ያሰናበትኳቸው። አምስት ስድስት ወር በዚህ ሁኔታ ቆየሁ።

የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የደኅንነት አማካሪ በተወካዮች ምክር ቤት ንግግር ሲያደርጉ
የምስሉ መግለጫ, አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በምክር ቤቱ ባደረጉት የመጨረሻ ንግግር የአማራ ክልል አስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በጥብቅ ተቃውመዋል

ቢቢሲ አማርኛ ፡ እንዴት ከአገር ሊወጡ ቻሉ?

አቶ ገዱ፡ ከአገር የወጣሁት ሌሊት ነው። አሁን ልነግርሽ በማልችልበት ሁኔታ ሰዎች አግዘውኛል።

ቢቢሲ አማርኛ፡ የስደት ሕይወት እንዴት ነው አሁን?

አቶ ገዱ፡ ስደት ስደት ነው። እንደ እኔ ያለ በተለይ ዕድሜ ከፍ እያለ በሚሄድበት ጊዜ ስደትን ለማንም የማልመኘው ነገር ነው። በፖለቲካው ዘርፍ አገር እና ኅብረተሰብን እለውጣለሁ ብዬ የኖርኩ ሰው ለዚህ መዳረጌ የሚያሳዝን ገጽታ አለው።

በሌላ መልኩ ደግሞ የእኔ አኗኗር ኢትዮጵያ ውስጥ ካለ ከማንኛውም ሰው የተሻለ ነው። አሜሪካ የነጻነት አገር ነው። ሕግ እና ሥርዓቱን ተከትለሽ እስከኖርሽ ድረስ፣ እዚህ አገር ከሚኖር ሰው ያልተለየ ኑሮ እየኖርኩ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ማንኛውም ሰው፣ ባለሥልጣናትም ቢሆኑ ሁሉም ስጋት አለባቸው፤ ሃብታምም ድሃም በስጋት ውስጥ ነው ያለው። እናም እግዚአብሔር ይመስገን በጥሩ ሁኔታ ነው ያለሁት።

ቢቢሲ አማርኛ፡ በቅርቡ በፓርኪንግ ሥራ ላይ ተሰማርተው የሚያሳይ ቪዲዮ ተሠራጭቶ ነበር። አንዳንዶች ከንጽሕና ጋር አገናኝተውታል። ሌሎች ደግሞ እንዴት በዚህ ደረጃ መተዳደሪያ ሊያጡ ይችላሉ የሚሉ ሃሳቦችን ሲያነሱ ነበር። እንዴት ወደዚህ ሥራ ተሰማሩ?

አቶ ገዱ፡ ወደ እዚህ አገር ስመጣ ባዶ እጄን ነበር የመጣሁት። ምንም ነገር አልነበረኝም። ለመኖር የሚያስፈልገኝን ሠርቼ ማግኘት ነበረብኝ። ይኼ ሥራ ደግሞ ለእኔ በወቅቱ ያገኘሁት ሥራ ነው።

ይህ ብቻም ሳይሆን በተወሰነ ደረጃ ኢትዮጵያ ከምኖረው በተሻለ መንገድ እንድኖር እያደረገኝ ያለ ነው። በሌላ በኩል ሰው የተለያየ ነገር ሊያነሳ ይችላል።

የአማራ ክልልን በምመራበት ጊዜ በቢሊዮን ብር በጀት የሚመድብ ክልል ነው። የውጭ ጉዳይም ትልቅ መሥሪያ ቤት ነው፤ የአገር ሃብት ጭምር የሚያንቀሳቅስ ነው። ሆኖም እነዚህ ሁሉ ለእኔ የተመደቡ ገንዘቦች አይደሉም። ደመወዝተኛ ነኝ።

ስደተኛ እሆናለሁ ብዬም አስቤ አላውቅም። ከሕዝብ ሃብት ወስጄ ኑሮዬን አሻሽላለሁ ብዬ አንድም ቀን አስቤ አላውቅም። ሰው ላያምን ይችላል። ግን አብዛኛው በተለይ አማራ ክልል የነበረው አመራር ጥሩ ባህል የነበረው ነው ማለት ይቻላል። ርዕሰ መስተዳድሮችን በምሳሌነት ማንሳት ይቻላል። በጡረታቸው ነው የሚኖሩት። የተንደላቀቀ ኑሮ የላቸውም።

አብዛኛው ሰው ኃላፊነትን ተጠቅሞ የመዝረፍ ባህልም ያልነበረበት ክልል ነው። አሁን ዕድሜ ለብልጽግና ሁሉ ነገር ተቀይሮ ሌላ ታሪክ መጥቷል። እኔ ባለፉት 26 ዓመታት አካባቢ ከፍተኛ ደመወዝ ተከፋይ ነበርኩ። ግን የኢትዮጵያ ደመወዝ ተደምሮ ሊመጣ የሚችለው ሁላችንም የምንገነዘበው ነው። ከዚያ በተረፈ ሌላ ንብረት በተለይ ውጭ አገር ገንዘብ ለማስቀመጥ የሚያስችል ፍላጎትም፤ አቅምም አልነበረም። በዚያ ምክንያት ይዤ የመጣሁት ራሴን እና ሻንጣዬን ነው።

ቢቢሲ አማርኛ፡ አሁን እየተዳደሩ ያሉት በዚህ ሥራ ነው?

አቶ ገዱ፡ አዎ። በዚህ ሥራ ነው እየተዳደርኩ ያለሁት።

ቢቢሲ አማርኛ፡ እርስዎ በተለያዩ ትላልቅ የአገር ኃላፊነቶች ላይ ሠርተዋል፤ ሦስተኛ ዲግሪዎንም አጠናቀዋል። ወደ ስደት ካመሩ በኋላ ከመሪዎች፣ ከባለሥልጣናት ወይም ከተቋማት የቀረበለዎት የሥራ ዕድል ወይም ጥያቄ አልነበረም?

አቶ ገዱ፡ እኔ በተለያዩ ድርጅቶች ክፍት ቦታዎችን እያየሁ አመለክታለሁ። እስካሁን አልተጠራሁም። ወደፊት እንደዚያ ዓይነት ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ ብዬ እገምታለሁ። ከዚያ በተረፈ በጠቅላላ ስለአገሪቱ ሁኔታ፣ በተለይ ከውጭ ጉዳይ ጋር የተያያዙ ስለኢትዮጵያ የሚያጠኑ እና ስለሰላም ከሚሠሩ ድርጅቶች ጋር እገናኛለሁ፤ እወያያለሁ። ስለኢትዮጵያ ያለኝን ዕይታ እንዳጋራቸው የሚደውሉ ብዙ አካላት አሉ። ከዚያ ውጭ ግን በግሌ የማገኘውም ሆነ ለግሌ በሚሆን መንገድ የተደዋወልኩትም ሆነ የጠየቅኩት የለኝም።

ቢቢሲ አማርኛ፡ ለውጡ ሲመጣ ብዙ ተስፋ ነበረ። ለዚህ ለውጥ መምጣት 'ቲም ለማ' በዋናነት ይጠቀሳል። አሁን እርስዎ በስደት ነው ያሉት። አቶ ለማም ዝምታን መርጠዋል። ያንን ቲም የሰበረው ምንድን ነው?

አቶ ገዱ፡ ያ ለውጥ የመጣው በጥቂት ሰዎች አይደለም። የሕዝብ ፍላጎት የወለደው ነው። የተወሰኑ ሰዎች የዚያ ለውጥ መሪዎች ነበርን ብዬ አልወስደም። ያ ለውጥ እንዲመጣ ያደረገው ኢህአዴግ ነው። የመጣውን ለውጥ ወደፊት እንዲራመድ ያደረገው ድርጅት ነው እንጂ ግለሰቦች አይደሉም። ግለሰቦችን አንስቶ አድራጊ ፈጣሪ አድርጎ የመመልከት ሁኔታዎች ነበሩ - ያ ስህተት ነበር ባይ ነኝ። በኋላ በውጤቱም ስንመለከተው ያ እንዳልሆነ አይተነዋል።

ቢቢሲ አማርኛ፡ አሁን ከአቶ ለማ ጋር ትገናኛላችሁ?

አቶ ገዱ፡ እንዲሁ አልፎ አልፎ። ዘወትር የምንገኛኝ አይደለንም። አልፎ አልፎ በስልክ እንገናኛለን። ሰላምታ እንለዋወጣለን።

ቢቢሲ አማርኛ፡ በአገሪቷ ጉዳዮች ላይ የመነጋገር ነገሮች አሉ?

አቶ ገዱ፡ አይ አልተነጋገርንም። አሁን እሱ ያለበት ሁኔታም በዚያ መልክ ብዙም ፍላጎት ስለሌለው ከሰላምታ በዘለለ ወደ ፖለቲካ አጀንዳ ውስጥ ብዙም አንገባም።

ቢቢሲ አማርኛ፡ መቼ ነው በቅርብ ጊዜ ያወራችሁት?

አቶ ገዱ፡ አላስታውስም።

ማይክ ፖምፒዮ እና አቶ ገዱ አንዳርጋቸው
የምስሉ መግለጫ, የቀድሞው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ እና ገዱ አንዳርጋቸው

ቢቢሲ አማርኛ፡ ለውጡ ሲመጣ ሌላው ንቅናቄ የኦሮ-ማራ ጥምረት ነው። የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ለመፍጠር ጥረት ሲደረግ ነበር። ሆኖም በኦሮሚያ ክልል እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች በአማራ ተወላጆች ላይ ግድያ፣ ማፈናቀል፣ እገታ መፈጸሙ ሲዘገብም ነበር። እርስዎ በሥልጣን ላይ እንደነበረ አንድ የአማራ ፖለቲከኛ ይህንን ለማስቆም ምን ተወጥቻለሁ ብለው ያስባሉ?

አቶ ገዱ፡ በኦሮሞ እና በአማራ መካከል ሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ለመፍጠር የሚሠሩ ሥራዎች ይኖራሉ። መቀጠልም አለባቸው። ነገር ግን ኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚገደሉት እና የሚፈናቀሉት ሰዎች በዋናነት የሚቀነባበረው በእኔ እምነት በመንግሥት እና መንግሥት በሚደግፋቸው አካላት ነው። መንግሥት የሚደግፋቸው ኢመደበኛ አደረጃጀቶች አሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ የመንግሥት የፀጥታ ኃይል ነው ጉዳት እያደረሰባቸው ያለው። በቅርቡ ወለጋ ውስጥ መንደሮች የተቃጠሉት በኦሮሚያ የፀጥታ ኃይል ነው። የተለያየ ምክንያት ሊኖረው ይችላል። የአርሶ አደር መንደር ተቃጥሎ ነው እንዲፈናቀሉ የተደረጉት። እንዲህ ዓይነት ልማዶች ብዙ ጊዜ የሚደጋገሙ ናቸው።

እዚያም እያለሁ ይህ እንዲስተካከል ብዙ ጥረት አድርጌያለሁ። ምን አልባት ከመንግሥት ጋር አለመግባባት እንዲፈጠር ያደረገው እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች እንዲስተካከሉ በመጠየቄ ነው።

በማንም ሰላማዊ ሕዝብ ላይ ይህ እንዳይደርስ መንግሥት ሚናውን እንዲወጣ የምችለውን ሞክሬ ነበር። አሁንም እንደ ፖለቲከኛ በንጹሃን ላይ የሚደርሰውን ግፍ መንግሥት እንዲያቆም የእነዚህን ሰዎች መብት እና ደኅንነትን እንዲያረጋግጥ የበኩሌን ትግል እያደረኩ ነው።

ነገር ግን ከመንግሥት ሥራዎች ቀዳሚ የሆነውን ኃላፊነት ለመወጣት ብዙ ዝግጁነት የለም። ይልቁንስ መንግሥት እንደ ሽፍታ 'አክት' የሚያደርግበት ነው። እንዲህ ዓይነት ሥርዓት እና አገዛዝ በግለሰቦች ትግል ይለወጣል ብዬ አላስብም። ማኅበረሰባዊ የሆነ ትግል ነው ሊያስተካክለው የሚችለው።

ቢቢሲ አማርኛ፡ ከትግራይ ጦርነት በኋላ እርስዎ የተቃወሙት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ፣ ሲመሩት የነበረው የአማራ ክልል ግጭት ውስጥ ከገባ ሦስት ዓመቱን ደፍኗል። ግጭቱ ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳት እያስከተለ ነው። እነዚህን ሁለት ክልሎች እንዲህ ያለ ቀውስ ውስጥ የከተታቸው ምንድን ነው?

አቶ ገዱ፡ በትግራይም፤ በአማራም ያለው ሁኔታ በሰላማዊ ውይይት የማይፈታ ችግር አይደለም። በድርድር፣ በንግግር መፍታት የሚቻል ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች ያሉበት ነው፤ መፈታት የሚችል ነው። ነገር ግን አገዛዙ በሰላማዊ መንገድ ችግሮችን ለመፍታት ዝግጁነት የለውም። በጦርነት አጋጣሚውን ተጠቅሞ አካባቢውን ማድቀቅ ነው የሚፈልገው።

አማራ ክልልን ስለቅ በአጠቃላይ ከአፀደ ሕፃናት ጀምሮ ወደ 6 ሚሊዮን የሚጠጋ ተማሪ ነበር። አሁን እስከ 8 ሚሊዮን ተማሪ ይጠበቅ ነበር። የሚማረው ግን 3.5 ሚሊዮን ተማሪ ነው፤ ይህም በተቆራረጠ እና በአንጻራዊነት በከተሞች አካባቢ ነው። አማራ ክልል ያሉ የተጀመሩ መሠረተ ልማቶች በሙሉ ቆመዋል። የክልሉ ገንዘብም ጭምር ለጦርነት ነው የሚውለው። የነበሩት መሠረተ ልማቶችም እየወደሙ ነው። ሆስፒታሎች እና የጤና ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች በድሮን እየተደበደቡ ነው። የገበያ ቦታ፣ የእምነት ስፍራ ላይ ያሉ ሰዎችን ሳይለይ ነው ጭፍጨፋ የሚያካሂደው።

ይህ አገዛዝ ሰበብ ፈልጎ በፖለቲካዊ መንገድ ሊፈታ የሚችለውን ወደ ጦርነት ቀይሮ አካባቢውን ለማድቀቅ ከፍተኛ ፍላጎት ያለው መሆኑን ያሳያል። በሰላም ለመፍታት ጥረት ሲያደርግም አይታይም።

ቢቢሲ አማርኛ፡ መንግሥት በአገሪቷ ያሉ ታጣቂዎች ወደ ሰላም እንዲመጡ በተደጋጋሚ ጥሪ ያቀርባል እኮ።

አቶ ገዱ፡ ምክንያት አለን ብሎ ለትግል የወጣን ኃይል እንዴት ብሎ ነው እጅ ስጡ የሚባለው። እጅ ስጡኝ እና የእኔን ተቀብላችሁ በሰላም ኑሩ ነው የሚላቸው። ያነሱትን ፖለቲካዊ ጥያቄ ለመፍታት የሚያስችል የድርድር እና የሰላማዊ ውይይት ሃሳብ የለውም። 'ተውትና ኑ ነው'፤ እንደዚያ ደግሞ ሊሆን የሚችል አይደለም። ለሰላም ምንም ዓይነት ዝግጁነት የሌለው አገዛዝ እንደሆነ ነው በተግባር እየታየ ያለው።

ቢቢሲ አማርኛ ፡ እርስዎም እኮ በትግራይ ጦርነት ወቅት የትግራይ ኃይሎችን ለመውጋት ከሌሎች ባለሥልጣናት ጋር ዘመቻ ሲመሩ ታይተዋል። ያኔ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደኅንነት አማካሪ ነበሩ።

አቶ ገዱ፡ ጦርነቱ ከመቀስቀሱ በፊት በሁለቱም ወገኖች ላይ የጦርነት ፍላጎት ነበር። በሁለቱም ወገን ፕሮፖጋንዳው ከፍተኛ ነበር። በትግራይም፣ በፌደራል መንግሥትም፣ በአማራ በኩልም። እነዚህ ሁኔታዎች ወደ ጦርነት እንዳይሄዱ ተቃውሞ ነበረኝ።

እኔ በዚያ ጦርነት የተሳተፍኩት፣ በተለይ የትግራይ ኃይሎች ወደ አማራ ክልል ገብተው ጉዳት ባደረሱ ጊዜ የመረረ ነገር ነበረኝ። የደረሰው ጥፋትም በጣም ከባድ ነበር፤ ለመከላከል የበኩሌን ድርሻ መወጣት ነበረብኝ። ያም ቢሆን ግን የመንግሥት ባለሥልጣን ስለነበርኩ 'ቦልድ' ሆኖ መናገር ባይቻልም በዚያው መዋቅር ውስጥ ጦርነት እንዳይቀሰቀስ የበኩሌን ድርሻ ለመወጣት ሞክሬያለሁ። ወደ ጦርነት የሚያመሩ ፍረጃዎች ስለነበሩ በእነዚያ ላይ ተቃውሞ ነበረኝ። በኋላ ላይ ግን ጦርነቱ በተለይ ወደ አማራ ክልል ከገባ በኋላ ሕዝቡን በማነቃነቅ ሚና ነበረኝ።

ገዱ አንዳርቸጋው እና የቀድሞው የውሃ ሚኒስትር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ
የምስሉ መግለጫ, ገዱ አንዳርቸጋው እና የቀድሞው የውሃ ሚኒስትር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ

ቢቢሲ አማርኛ፡ በፈቃደዎ ነው የዘመቱት ወይስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ትዕዛዝ?

አቶ ገዱ፡ ዘመቻው እኔንም በቀጥታ የሚመለከት ነው። የእኔ አካባቢ ነው በጦርነት እየታመሰ ያለው። ያንን ውድመት ለመከላከል የጠቅላይ ሚኒስትሩ ትዕዛዝ አያስፈልገኝም ነበር። ከሞላ ጎደል በራሴ ተነሳሽነት ነው ማለት ይቻላል። ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላም እንደ መንግሥት ባለሥልጣን ሚና አልነበረኝም።

በትግራይ ጦርነት ጊዜ እንደ መንግሥት ባለሥልጣን በጠቅላላው ብዙ ሚና አልነበረኝም። የትግራይ ኃይሎች ወደ አማራ ክልል በሚገቡበት ጊዜ ያኔ በንቃት የአማራ ሕዝብ ራሱን ለመከላከል በሚያደርገው ጥረት የበኩሌን ሚና ተወጥቻለሁ ማለት እችላለሁ።

ቢቢሲ አማርኛ፡ የጦርነቱ ውጤቱ ይታወቃል። በትግራይም፣ በአማራም፣ በአፋርም ከፍተኛ ውድመት ነው ያደረሰው። በዚያች ዘመቻ ላይ መሳተፈዎ ይቆጭዎታል?

አቶ ገዱ፡ ጦርነት በጠቅላላው አውዳሚ ነው። በዚህ አውዳሚ ሁኔታ መሳተፌ በጠቅላላው ያሳዝነኛል። በሌላ መልኩ ደግሞ የሚደግፈው በሌለ ሕዝብ ውስጥ ዝም ብዬ መመልከት ነበረብኝ ብዬ አላምንም። አሁንም በአማራ ሕዝብ ላይ የሚደርሰውን በደል አጥብቄ እቃወማለሁ። በሌሎች አካባቢዎች የሚደርሰውንም እየተቃወምኩ ነው። በዚያ ጦርነት ውስጥ መሳተፌ፣ ጦርነቱ ራሱ መኖሩ አሳዛኝ ነው።

ቢቢሲ አማርኛ፡ አሁን ደግሞ ኢ- መደበኛ እና በኋላ ላይ ፋኖ በሚል የተደራጁ የክልሉ ኃይሎች ሲዋጓቸው ከነበሩ ኃይሎች ጋር መንግሥትን ለመጣል ጥምረት መስርተዋል። እንዴት አዩት ጥምረቱን?

አቶ ገዱ፡ በመጀመሪያ ደረጃ ሥልጣን ላይ ያለውን የብልጽግና አገዛዝን የሚዋጉት ብቻ ሳይሆኑ ፣ በሥልጣን ላይ ያለው ኃይል ከእነዚህ ኃይሎች ጋር ተወያይቶ ችግሩን መፍታት ቢችል ደስታውን አልችለውም።

ነገር ግን አገርን ለኅልውና አደጋ ያጋለጠ ኢትዮጵያን ከመኖር ወደ አለመኖር ሊቀይር የሚችል የከፋ አደጋ ተደቅኗል። በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ በየተራ ጦርነት እየከፈተ ለሁላችንም የኅልውና አደጋ የደቀነ አገዛዝ አለ። ይህ አገዛዝ በኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም እና መረጋጋት የሕግ የበላይነት ማምጣት እንዳልቻለ በስምንት ዓመቱ ተረጋግጧል።

ስለዚህ እነዚህ ኃይሎች የተለያየ አቋምና የተለያየ አመለካከት ቢኖራቸውም በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያም፤ የሕዝቦቿም ስጋት ይህ አገዛዝ ስለሆነ ይህን አገዛዝ በጋራ እናስወግድ ብለው ነው ልዩነቶቻቸውን በውይይት መፍታትን ታሳቢ አድርገው የተጣመሩት።

ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ የተለያዩ ኃይሎች በተለይ የመተባበር መንፈስ ይዘው ወደዚህ ደረጃ መምጣታቸውን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ትልቅ እምርታ አድርጌ ነው የምመለከተው።

ቢቢሲ አማርኛ፡ ይህ ጭራሽ አገሪቷን ወደ ባሰ ቀውስ ውስጥ አይከታትም?

አቶ ገዱ፡ አገሪቱ እኮ አሁንም ቀውስ ውስጥ ነች። ከዚህ የከፋ ቀውስ ሊመጣ ይችላል ወይ የሚለው ሊያጠያይቅ ይችላል። አገሪቷ የከፋ ቀውስ ውስጥ ነች። ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ የሉዓላዊነት ቀውስ፣ በጠቅላላ ኢትዮጵያ እንደ አገረ መንግሥት መቀጠል የማትችልበት ሁኔታ ነው ያለው። ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ነው። ይህንን ችግር ለመፍታት ነው እነዚህ ኃይሎች ትብብር እያደረጉ ያሉት። በመግለጫዎቻችው ግልጽ ያደረጉትም ይህንኑ ነው። አሁን በሥልጣን ላይ ያለው ኃይል ሁኔታውን አባባሰው እንጂ ሊፈታው አልቻለም። ልፍታ ቢልም እንደማይችል በተግባር ተረጋግጧል።

ቢቢሲ አማርኛ፡ ከዚህ ቀደም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በመሥራትዎ እንደሚያፍሩበት እና እንደሚያዝኑበት ገልጸዋል። አሁን ወደ ኋላ ወደ ለውጡ መመለስ ቢችሉ ምን ያስተካክላሉ?

አቶ ገዱ፡ እኔ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር መሥራቴ በፖለቲካ ታሪኬ የማዝንበትም፣ የማፍርበትም ነው ብያለሁ። ምክንያቴም ያ ለውጥ መቀልበሱ እና ለውጡ ለመጥፎ ዓላማ መዋሉም ብቻ አይደለም። ለአገር መሪነት የማይበቃ ኃይል፣ አገርን የሚያፈርስ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ አሁን ላለው ምስቅልቅል የዳረገ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር የተወሰነ ጊዜም ቢሆን መሥራቴ ያሳፍረኛል።

በመጀመሪያ ደረጃ የኢትዮጵያ ሕዝብ የፖለቲካ ሥልጣኑን የሚቆጣጠርበት፣ ሲፈልግ የሚሽርበት፣ ሲፈልግ የሚያወርድበት ተቋማዊ የሆነ ሥርዓት መኖር አለበት ብዬ አምናለሁ። አንድ ግለሰብ ሥልጣኑን ተቆጣጥሮ የፈለገውን የሚያደርግበት ሁኔታ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ዳግም ላይመለስ በሚያደርግ መንገድ መዘጋት አለበት ብዬ አምናለሁ።

የመንግሥት ሥልጣን በዲሞክራሲያዊ ምርጫ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ይሄ 'ፖፑሊስት' የሆነ የመንጋ ፖለቲካ ብዙ ሰዎችን ለስህተት የዳረገ ነው ብዬ አስባለሁ። በሆይ ሆይታ፣ በምክንያት ሳይሆን በሆነ መንገድ ጥላቻ ካለ ያንን በመቀስቀስ ወይም ምናባዊ የሆነ ቅዠት በማምጣት ወደ ሥልጣን ለመምጣት የሚደረግ የፖለቲካ እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተገቢ ትምህርት ሊወስድበት ይገባል ብዬ አስባለሁ።

ቢቢሲ አማርኛ፡ ከዚህ በኋላ የፖለቲካ ሃሳብዎን እንዴት ነው ማሳካት የሚፈልጉት?

አቶ ገዱ፡ ከወጣትነቴ ጀምሮ አብዛኛውን ዕድሜዬን በፖለቲካ ውስጥ ነው ያሳለፍኩት። ምንም እንኳን በመጨረሻ ምርቃቱ ስደት ቢሆንም፣ አገሬን ይጠቅማል ብዬ ባሰብኩት የፖለቲካ ሃሳብ ላይ አስተያየት ከመስጠት አልቆጠብም። ነገር ግን ለጊዜው የማደርገው ሃሳቤን ማጋራት ነው፤ ፓርቲ ማቋቋምም ሆነ ፓርቲ ውስጥ የመግባት ሃሳብ የለኝም።