ህወሓትን "ተገንጣይ" ያሉት ሩቢዮ በአዲስ አበባ የድሮን ጥቃት ተፈፅሞ እንደነበር ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ላለፉት ሦስት ሳምንታት ከፌደራል መንግሥቱ እና ከአጋሮቹ ጋር እየተዋጋ የሚገኘውን ህወሓት "ተገንጣይ ቡድን" በማለት በአዲስ አበባ የድሮን ጥቃት ተፈጽሞ እንደነበር ተናገሩ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቅዳሜ ጥቅምት 7/2019 ዓ.ም. በሜሪላንድ በሚገኘው አንድሪው የጦር ሰፈር ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ በኢትዮጵያ ውስጥ ጥቃት የሚፈጽሙ "ተገንጣይ ቡድኖች" መኖራቸውን እና ለዚህም የኢትዮጵያ መንግሥት ምላሽ እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም ማንም ቢሆን ሽብርተኝነትን አይደግፍም ካሉ በኋላ አዲስ አበባን ዒላማ ያደረገ የድሮን ጥቃት መፈፀሙን ተናግረዋል።
"ማንም ቢሆን ሽብርተኝነትን፣ . . . በዋና ከተማቸው ላይ የተፈጸመውን የድሮን ጥቃቶች ጨምሮ የሚደግፍ የለም።"
መስከረም 21/2019 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ እና ቢቢሲ ያነጋገራቸው ግለሰቦች ሌሊቱን ከባድ ፍንዳታ መስማታቸውን ተናግረው ነበር።
ሮይተርስ እና የፈረንሳይ የዜና ወኪሎች በበኩላቸው የዲፕሎማቲክ ምንጮችን ጠቅሰው በአዲስ አበባ እኩለ ሌሊት ፍንዳታ መሰማቱን ዘግበዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው እና በጎተራ እና በቤተል አካባቢ የሚኖሩ ግለሰቦች ፍንዳታውን የሰሙት ከእኩለ ሌሊት 6፡20 በኋላ መሆኑን ተናግረዋል።
በወቅቱ ቢቢሲ ከተለያዩ የመንግሥት ኃላፊዎች ስለፍንዳታው ምንነት ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
መስከረም 13/2019 ዓ.ም. ህወሓት በትግራይ ክልል የሚገኙ ሦስት አውሮፕላን ማረፊያዎችን በቁጥጥሩ ስር ማዋሉን ካስታወቀ በኋላ ክልሉን ከአማራ እና ከአፋር ጋር በሚያዋስኑ ሥፍራዎች የተቀሰቀሰው ጦርነት ወደ ኤርትራ አዋሳኝ ድንበሮች ተገፍቷል።
በህወሓት ኃይሎች እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መካከል ይፋዊ ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ የኤርትራ ወታደሮች ተሳታፊ መሆናቸውን የኢትዮጵያ መንግሥት ተናግሯል።
የኤርትራ መንግሥት በኢትዮጵያ ያሉ ታጣቂዎችን በመርዳት የአገሪቱን ሰላም ለማናጋት እየጣረ መሆኑን በመግለጽ ቢከስም፣ የኤርትራ መንግሥት ግን ክሱ በአገር ውስጥ ያለውን ችግር አቅጣጫ ለማስቀየር ነው በሚል ውድቅ ያደርጋል።
የአሜሪካ መንግሥት በቅርቡ ከኢትዮጵያ በተያያዘ ጥሏቸው የነበሩ አንዳንድ ማዕቀቦችን ማንሳቱን ተከትሎ፣ ውሳኔው በአፍሪካ ቀንድ ያለውን ውጥረት ለማርገብ እና አሜሪካ የአስታራቂነት ሚናዋን እንድትጫወት ያለመ መሆኑን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ደም አፋሳሹ የትግራይ ጦርነት በፕሪቶሪያ ስምምነት አማካኝነት እንዲገታ ከፍተኛ ሚና ከነበራቸው አካላት መካከል አሜሪካ ቀዳሚዋ ነች።
አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ተጥሎ የነበረውን የጦር መሣሪያ ማዕቀብ ማንሳቷን ያስታወቀችው ግንቦት 3/2018 ዓ. ም. ነበር።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአገር መከላከያ ንግድ ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት በኢትዮጵያ ላይ ይከተል የነበረውን የክልከላ ፖሊሲንም አንስቷል።
ሩቢዮ ትናንት ለጋዜጠኞች ሲናገሩ ማዕቀቦቹን ማንሳት ስህተት ነው ብለው እንደማያስቡ ገልጸው፣ የተነሱት ማዕቀቦች እጅግ አነስተኛ መሆናቸውን እና መሬት ላይ እየተፈጠረ ካለው እውነታ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንደሌላቸው ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የጦር መሣሪያ ዝውውር ደንብ (ITAR 126.1) ዝርዝር ውስጥ ከሚገኙ አገራት ተርታ እንድትሰረዝ የተደረገው በትግራይ ክልል እንዲሁም በኢትዮጵያ እና በኤርትራ እንዲሁም በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ያለው ውጥረት በተባባሰበት ወቅት ነበር።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ያለው ውጥረት እየጨመረ በመምጣቱ ስጋት እንዳላቸውም ገልጸዋል።
ሁለቱም አገራት በድንበሮቻቸው አቅራቢያ ወታደሮቻቸውን ማስጠጋታቸውን ጠቅሰው፣ ይህም ሌሎች ጎረቤት አገራትን የሚያካትት ሰፊ ቀጣናዊ ጦርነት ሊያስከትል ይችላል በሚል ስጋታቸውን ተናግረዋል።
ባለፈው ሳምንት ጥቅምት 4/ 2019 ዓ.ም. ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር በስልክ የተወያዩት ማርኮ ሩቢዮ በሁለቱም ወገኖች በኩል ውጥረት እንዲረግብ ጥሪ አቅርበዋል።
ማርኮ ሩቢዮ "ሁሉም የአፍሪካ ቀንድ አገራት የጎረቤቶቻቸውን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ማክበር አለባቸው" ማለታቸው ተጠቅሷል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አክለውም አገራቱ "ድንበር ተሻጋሪ ወረራ እንዳይፈጽሙ" አሳስበዋል።
ላለፉት ዓመታት ከኤርትራ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያልነበራት አሜሪካ፣ ማዕቀቦቹን በማንሳት እና ግንኙነቷን በማሻሻል የሰላም አስከባሪነት ሚናዋን መጫወት እንደምትፈልግም ሩቢዮ ለጋዜጠኞች በሰጡት ምላሽ ወቅት አስረድተዋል።
ከሁለቱም ወገኖች ጋር መነጋገር ካልተቻለ የአደራዳሪነት ሚናን መወጣት አስቸጋሪ እንደሚሆን በማመን፣ ባለፉት ጥቂት ወራት ከኤርትራ ጋር ከተለመደው የተሻለ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ መቻሉን አውስተዋል።
ሩቢዮ በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር መነጋገራቸውን አስታውሰው ዋሽንግተን ባለፉት በርካታ ወራት ከኤርትራ ጋር የዲፕሎማሲ ግንኙነት እንዳሳደገች ገልጸዋል።
በአንጻሩ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር እጅግ የጠበቀ ግንኙነት እንዳላቸው ያስታወሱት ማርኮ ሩቢዮ፣ እርሳቸውም በግላቸው በቅርቡ ከመንግሥት ኃላፊዎች ጋር መነጋገራቸውን ጠቁመዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ መንግሥት ለሚያጋጥሙት ፈተናዎች የሚሰጠው ምላሽ ጥበብ የተሞላበት እና ሚዛናዊ ሊሆን እንደሚገባ ገልጸው፣ እርምጃው ሌሎች አገራትን ጭምር አሳትፎ ወደ አውዳሚ ጦርነት እንዳያመራ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ሩቢዮ በስተመጨረሻም ዓለም በአሁኑ ሰዓት ሌላ ተጨማሪ ጦርነት እንደማይፈልግ በማስመር ማብራሪያቸውን አጠናቀዋል።




































