በጣም ትኩስ ቡና ወይም ሻይ መጠጣት የካንሰር ተጋላጭነትን እንደሚጨምር ጥናት አሳየ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አዘውትሮ በጣም ትኩስ ሻይ እና ቡና መጠጣት የካንሰር ተጋላጭነት መጠንን እንደሚጨምር በዩናይትድ ኪንግደም የተሠራ ጥናት ጠቁሟል።
ከፍተኛ ሙቀት ያለው ሻይ ወይም ቡና የምግብ ቧምቧ ካንሰር (ኢሶፋጋል ካንሰር) እንደሚያስከትል ጥናቱ ያሳያል።
ወደ አንድ ሚሊዮን ሰዎች የተሳተፉበት ጥናት፤ ከዚህ ቀደም በትኩስ መጠጥ እና ካንሰር መካከል ያለው ትስስር ላይ ከተሠሩ ጥናቶች ሰፊው እንደሆነ ተመራማሪዎቹ ገልጸዋል።
ሻይ ወይም ቡና "በጣም በትኩሱ" የወሰዱ የጥናቱ ተሳታፊዎች "በስሱ ትኩስ በሆነ መጠን" ከወሰዱት አንጻር የካንሰር ተጋላጭነታቸው በሦስት እጥፍ ጨምሯል።
በዚህ የካንሰር ዓይነት የመያዝ ዕድል ጠቅለል ባለ ሁኔታ አነስተኛ እንደሆነ ባለሙያዎቹ በአጽንኦት ገልጸዋል።
ትኩስ የሆነ መጠጥ ምግብን ከጉሮሮ ወደ አንጀት በሚወስደው ቧምቧ በኩል ሲያልፍ ሕዋሳትን ይጎዳል።
በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ የተሠራው ጥናት በዓለም አቀፉ የካንሰር ምርምር መጽሔት ላይ ታትሟል።
በ65 ዲግሪ ሴልሽየስ ወይም ከዚያ በላይ የሚሞቅ መጠጥ "በጣም ትኩስ" በሚል ይመደባል። ለአደጋም ያጋልጣል።
በቀን ውስጥ ስድስት ብርጭቆ ወይም ከዚያ በላይ ትኩስ ነገር መጠጣትም ተጋላጭነቱን ከፍ ያደርጋል።
በጥናቱ የተሳተፉት በመካከለኛ ዕድሜ ላይ የሚገኙ 977,282 ወንዶች እና ሴቶች ናቸው።
ትኩስ መጠጥ ላይ ወተት መጨመር በተወሰነ መጠን ቢያቀዘቅዘውም፤ ወተት የተቀላቀለበት ቡና ወይም ሻይ ትኩስ መሆኑ እንደማይቀር አጥኚዎቹ ያስረዳሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በ100 ዲግሪ ሴልሽየስ በጋለ ማንቆርቆሪያ የተፈላ ሻይ ትኩስ ተደርጎ ይወሰዳል። በብርጭቆ ሲቀዳ ሙቀቱ ከ90 እስከ 95 ዲግሪ ሴልሽየስ ይወርዳል።
ሻይ ወይም ቡና ቀዝቀዝ እስከሚል ድረስ የተወሰኑ ደቂቃዎችን ጠብቆ መጠጣት እንደሚያሻ ባለሙያዎቹ ይመክራሉ።
የዩናይትድ ኪንግደም የካንሰር ምርምር ተቋም እንደሚለው፤ ትኩስ መጠጥ እስከሚቀዘቅዝ ድረስ ይሄን ያህል ጊዜ ይቆይ በሚለው ላይ የተቀመጠ ትክክለኛ መረጃ የለም።
"ነገሩ የሚያስጨንቃችሁ ከሆነ ለመጠጣት ምቾች የሚሰጣችሁን ያህል ጠብቁ። በጣም ትኩስ ሳለ ከመጠጣት የተሻለ ነው" ይላል ተቋሙ።
የጥናቱ መሪ ዶ/ር ካረን ፓፒር እንደሚናገሩት፤ በርካቶች 'ሜት' የተባለውን በጣም ትኩስ የቅጠላ ቅጠል ሻይ በሚጠጡበት ደቡብ አሜሪካ ውስጥ ትኩስ መጠጥ መጠጣት እና የምግብ ቧምቧ ካንሰር መካከል ትስስር ታይቷል።
"ለካንሰር የሚኖረው ተጋላጭነት የሚጨምረው መጠጡ በምን ያህል መጠን ትኩስ ሲሆን ነው የሚለውን ለመለየት ተጨማሪ ጥናት ያስፈልጋል" ይላሉ።
ሌላ 118 ወጣቶችን ያሳተፈ ጥናት በተለያዩ የቡና ዓይነቶች ላይ ያተኮረ ነው።
ቡና ከ70 ዲግሪ ሴልሽየስ በላይ ሲሆን በጣም ትኩስ እንደሚሆን ለማወቅ ተችሏል።
አንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውል የቡና መጠጫ የሚያመርተው ተቋም 'ኤምቲፒኤኬ ኮቺ' እንደሚለው፤ ለቡና ጥሩ የሚባለው የሙቀት መጠን ከ49 እስከ 60 ዲግሪ ሴልሽየስ ነው።
ተጠቃሚዎች በጣም ትኩስ ቡና ከጠየቁ እስከ 82 ዲግሪ ሴልሽየስ ሊደርስ ይችላል።
አጥኚዎቹ እንዳሉት ከ10 የምግብ ቧምቧ ካንሰር ውስጥ አንዱ ወይም ሁለቱ በጣም ትኩስ መጠጥ ባለመጠጣት ሊወገድ ይችላል።
የምግብ ቧምቧ ካንሰር በብዛት የሚከሰት አይደለም። ለምሳሌ በዩናይትድ ኪንግደም ከአጠቃላዩ ሕዝብ በዚህ የካንሰር ዓይነት የሚያዘው አንድ በመቶው ብቻ ነው።
በጣም ትኩስ ሻይ ወይም ቡና መጠጣት የካንሰር ተጋላጭነትን ቢጨምረውም እንኳን በበሽታው የመያዝ ዕድል ውስን ነው።
በከፍተኛ መጠን ለምግብ ቧምቧ ካንሰር የሚያጋልጠው ሲጋራ ማጨስ ነው።
በዩናይትድ ኪንግደም ጥናቱን በገንዘብ የደገፈው የካንሰር ምርምር ማዕከል ውስጥ የሚሠሩት ፊዮና ኦስጉን "በዚህ ካንሰር የመያዝ ዕድልን ለመቀነስ አለማጨስ እና አልኮል መጠጥ መቀነስ ያስፈልጋል" ይላሉ።
የምግብ ቧምቧ ካንሰር ምልክቶች የደረት ማቃጠል፣ ምግብ ለማብላላት መቸገር፣ የሰውነት ክብደት መቀነስ እንዲሁም የጉሮሮ እና ደረት ሕመም ናቸው።



































