በ10 ዓመት 6 መሪዎች፡ ለምን የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትሮች በቶሎ ይለዋወጣሉ?

ሰር ኪር ስታርመር በ10 ዓመታት ውስጥ ሥልጣን የለቀቁ ስድስተኛው ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሰር ኪር ስታርመር በ10 ዓመታት ውስጥ ሥልጣን የለቀቁ ስድስተኛው ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ሰር ኪር ስታርመር በ10 ዓመታት ውስጥ ሥልጣን የለቀቁ ወይም ተገፍተው ከመሪነት የወረዱ ስድስተኛው የዩናይትድ ኪንግድም ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው።

ይሄ በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ የተለመደ አይደለም። በ18ኛው ክፍለ ዘመን ለጠቅላይ ሚኒስትር ሥልጣን መስጠት ከተጀመረ አንስቶ መሪ የነበሩ ፖለቲከኞች እያንዳንዳቸው እስከ አምስት ዓመታት አገልግለዋል።

ባለፉት 10 ዓመታት ውስጥ ግን የጠቅላይ ሚኒስትሮች የአገልግሎት ዘመን ወደ 18 ወራት ወርዷል።

ስድስቱም ሥልጣን የለቀቁ ጠቅላይ ሚኒስትሮች የተለያየ ምክንያት አላቸው። ሆኖም ግን በዩናይትድ ኪንግድም (ዩኬ) ጠቅላይ ሚኒስትሮች በፍጥነት የሚቀያየሩት ለምንድን ነው? የሚለውን ጥያቄ አለማንሳት አይቻልም።

ዴቪድ ካሜሩን በአውሮፓውያኑ 2016 ዩኬ ከአውሮፓ ኅብረት እንድትወጣ የሕዝበ ውሳኔ ሐሳብ አቅርበው ስላልተሳካ ሥልጣን ለቅቀዋል።

ዩኬ ከአውሮፓ ኅብረት ከወጣች (ከብሬግዚት በኋላ) ከኅብረቱ ጋር ያላት ግንኙነት ምን መምሰል አለበት በሚል ያቀረቡት ምክረ ሐሳብ ተቀባይነት ስላላገኘ ቴሬሳ ሜይ ከመሪነት ወርደዋል።

ቦሪስ ጆንሰን ሥልጣን የለቀቁት በአብዛኛው ከባህሪያቸው ጋር በተያያዘ ነው። ከታማኝነት እና ከውሳኔ ሰጪነት ጋር በተያያዘ ወግ አጥባቂ የሕዝብ እንደራሴዎች የድግፋ ስለነፈጓቸ በምርጫው ውጤት እንደማያገኙ በማመን ከሥልጣን እንዲወርዱ ጫና አሳድረዋል።

በዜጎች መካከል ዋልታ ረገጥ ልዩነቶች እየታዩ ነው

የፎቶው ባለመብት, PA Media

የምስሉ መግለጫ, በዜጎች መካከል ዋልታ ረገጥ ልዩነቶች እየታዩ ነው

ሊዝ ትረስ ከሥልጣን ለመነሳታቸው ምክንያቱ የአገሪቱ ምጣኔ ሃብት ጉዳይ ነው። የግብር ቅነሳ ዕቅዳቸው ወጪ ለመሸፈን ገንዘብ ካለመመደቡ ጋር በተያያዘ ክፍተት ፈጥሯል።

ሌላኛው ወግ አጥባቂ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ምርጫን ተከትሎ ከጠቅላይ ሚኒስትርነት የወረዱ ብቸኛው መሪ ናቸው።

ለ14 ዓመታት የወግ አጥባቂ ፓርቲው አስተዳደር ያማረራቸው ዜጎች ድምጻቸውን አልሰጧቸውም።

ሰር ኪር ስታርመር የሌበር ፓርቲ የሕዝብ እንደራሴዎችን ድጋፍ በማጣተቸው ከመሪነት ወርደዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድጋፍ ማጣታቸው ፓርቲውን ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል በሚል ከሥልጣን እንዲወርዱ ጫና አሳድረዋል።

ከጠቅላይ ሚኒስትሮቹ የመልቀቅ ምክንያቶች ጀርባ በአገሪቱ ሕዝብ ዘንድ ክፍፍል እና ምሬት የፈጠሩ ክስተቶችም ይጠቀሳሉ።

የጤና ባለሙያዎች በብሔራዊ ጤና አገልግሎት ምሬታቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የጤና ባለሙያዎች በብሔራዊ ጤና አገልግሎት ምሬታቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል

ደስታ ማጣት

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የሕዝብ አስተያየት መለኪያዎች፣ የቡድን ውይይቶች እና ምስክርነቶች እንደሚያሳዩት ፖለቲከኞች በዋነኛ ለዜጎች ደስታ የማጣት ምክንያት ሆነዋል።

ቀዳሚው ጉዳይ የኑሮ ሁኔታ ነው። ይህም ከአውሮፓውያኑ 2008 የፋይናንስ ቀውስ ጀምሮ ታይቷል።

የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ሥልጣን መልቀቅ የጀመሩት ከ2016 አንስቶ ነው።

በ19ኛው ክፍለ ዘመን በአውሮፓ ከነበረው የናፖሌኒክ ጦርነት በኋላ ባልታየ ሁኔታ የኑሮ ሁኔታው አስከፊ የሆነበት ወቅት ነው።

ዜጎች ኑሮ ሲከብዳቸው እና መንግሥት መፍትሔ እንዳልሰጣቸው ወይም ቀጣዩ ትውልድ በተሻለ ሁኔታ እንዲቀጥል ለማስቻል የገባውን ቃል እንዳላከበረ ሲሰማቸው መከፋታቸው አይቀርም።

ከአውሮፓውያኑ 1978 ወዲህ በከፍተኛ ሁኔታ የአገሪቱ ዜጎች በምጣኔ ሃብት ሁኔታው ደስተኛ አይደሉም። የዋጋ ንረት ሲባባስ ምርታማነት ቀንሷል።

ትራንስፖርት፣ የፍትሕ ሥርዓት እና ሌሎችም የሕዝብ አገልግሎቶች በአግባቡ እየሠሩ አይደሉም የሚለው የሕዝብ አስተያየት ጎልቶ ይሰማል።

ይህም በተወሰነ ደረጃ የምጣኔ ሃብቱ መላሸቅ ውጤት ነው።

አገሪቱ ዕድገት አለማሳየቷ መንግሥታት ገቢ እንዳያገኙ እንዲሁም በመሠረተ ልማት፣ በትምህርት፣ በጤና እና በሌሎችም ዜጎች ዋጋ በሚሰጧቸው ዘርፎች ላይ ላይ ገንዘብ እንዳያፈሱ አድርጓል።

በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለው ልዩነት እየሰፋ መምጣቱም ለሕዝባዊ ደስታ ማጣት ሚና አለው።

80 በመቶ የአገሪቱ ነዋሪዎች መከፋፈላቸውን የተሰበሰቡ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ባለፉት ዓመታት የስደተኞች ቁጥር መጨመር እና የተከሰተው ውድቀት ለዚህ ምክንያት መሆኑን የሚያምኑ አሉ።

ወደ አገሪቱ የሚገቡ ስደተኞች በዚያው ኑሯቸውን መቀጠላቸውን የሚጠቅሱም አልታጡም።

ይሄ ምልከታ ትክክልም ይሁን ስህተት ድምጽ ሰጪዎች እንደሚሉት ከሆነ ዩናይትድ ኪንግደም በተለወጠችበት መንገድ ደስተኛ እንዳልሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሮች እየተረዱ አይደለም።

የተለያዩ ባህሎች ባሉበት እና ሕብረ ብሔራዊነት በሚታይበት ማኅበረሰብ ውስጥ ኑሮ ምን መምሰል አለበት የሚለውን በተመለከተ እንደ ሌሎች የአውሮፓ አገራት ሁሉ በዩናይትድ ኪንደምም ስምምነት የለም።

የአገሪቱ ዜጎች በነገሮች ደስተኛ ካለመሆናቸው ባሻገር ስሜታቸውን ከማሳየትም ወደኋላ አይሉም።

ለዚህ ምክንያቱ ማኅበራዊ ሚዲያ ወይም ሌላም ሊሆን ይችላል። ጠቅላይ ሚኒስትሮችን ጨምሮ ፖለቲከኞች ላይ በግልጽ ጥላቻን ማሳየት እየተለመደ መጥቷል። ከዓመታት በፊት ይሄ የተለመደ አልነበረም።

እምቢተኝነት

ዩናይትድ ኪንግደም በእምቢተኛነት ወይም አልገዛም በሚል ሕዝብ ተሞልታ ይሆን? የሚለውም ጥያቄ ተያይዞ ይነሳል።

በ10 ዓመት ውስጥ ሰባተኛ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊሾም ነው።

አብዛኞቹ ፖለቲከኞች እንደሚሉት ዩኬ በእምቢተኝነት ተሞልታለች ከሚለው ይልቅ ዓለም ከባድ እና ውስብስብ ቅርጽ የያዘችበት ወቅት ላይ እንገኛለን የሚለው ሚዛን ይደፋል። የሕዝቦች ክፍፍልም የሰፋበት ዘመን ነው።

ያለፉት ስድስት ጠቅላይ ሚኒስትሮች ከአውሮፓውያኑ 2008 የፋይናንስ ቀውስ እና ከ2016 ዩኬ ከአውሮፓ ኅብረት ከወጣች (ከብሬግዚት በኋላ) አንስቶ ያለውን ጨለምተኛነት መቅረፍ አልቻሉም።

አስካሁን አጭር ጊዜ ሥልጣን ላይ ቆይተው ከተሰናበቱት ስድስቱ ጠቅላይ ሚኒስትሮች በተሻለ ሰባተኛው ጠቅላይ ሚኒስትር ይሄንን ማሳካት ይችሉ ይሆን? የሚለው ለብዙዎች አጠያያቂ ነው።