በሱዳን ወሲባዊ ጥቃትን እንደ "ጦር መሣሪያ" መጠቀም መባባሱን ተመድ አስታወቀ

ሱዳናዊት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በሱዳን ወሲባዊ ጥቃት እንደ "ጦር መሣሪያ" ጥቅም ላይ የሚውልበት መጠን እየጨመረ መምጣቱን የተባበሩት መንግሥታት አስታወቀ።

ወሲባዊ ጥቃትን "ለጦርነት መሣሪያነት" በማዋል ንጹኃን ዜጎችን የማሸበር ድርጊት መስፋፋቱን ተመድ ባወጣው ሪፖርት አመልክቷል።

ዩናይትድ ኪንግደም እና ስድስት የአውሮፓ አገራት በጋራ ባወጡት መግለጫ በኤል-ኦቤይድ እየተፈጸመ ያለው ጥቃት እንዲቆም ጠይቀዋል።

የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) ከተማዋን ለመቆጣጠር ጥቃት ያደርሳል በሚል በርካቶች ስጋት ውስጥ ወድቀዋል።

የዩኬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጸሐፊ የቬት ኩፐር ከተማዋ "ለነውጥ መጋለጧን" ተናግረዋል።

አርኤስኤፍ የፈጸማቸው የድሮን ጥቃቶች መሠረተ ልማቶች ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ተናግረዋል።

የሸቀጥ ዝውውርን በማስተጓጎል ግማሽ ሚሊዮን ሕዝብ መሠረታዊ አቅርቦት እንዳያገኝ መደረጉንም አክለዋል።

ዩኬ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ አየርላንድ፣ ጣሊያን፣ ኔዘርላንድስ እና ኖርዌይ በጋራ ባወጡት መግለጫ "በቅርቡ የከፋ ጥቃት እንደሚፈጸም ምልክቶች ታይተዋል። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እርምጃ መውሰድ ያለበት በዚህ አንገብጋቢ ወቅት ነው" ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የተመድ የሰብአዊ መብቶች ቢሮ እንዳለው ከግጭት ጋር የተያያዙ 546 የወሲባዊ ጥቃት ኬዞችን መዝግቧል።

ይህም የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ከሦስት ዓመታት በፊት ከተጀመረ አንስቶ የተፈጸመ በቡድን መድፈር እና የወሲብ ባርነትን ይጨምራል።

በወሲባዊ ጥቃቱ ቢያንስ 838 ሰዎች ሰለባ መሆናቸውን ሪፖርቱ ያመለክታል። 539 አዋቂ ሴቶች እና 286 ታዳጊ ሴቶች እንዲሁም ስምንት አዋቂ ወንዶች እና ሰባት ታዳጊ ወንዶች ይገኙበታል።

"ይህ አሐዝ የጥቃቱን ውስን ክፍል ነው የሚያሳየው። የተፈጸመው መጠነ ሰፊ ወሲባዊ ጥቃት አልተመዘገበም" ይላል ሪፖርቱ።

ከተረጋገጡት ጥቃቶች አብዛኞቹ የተፈጸሙት በአርኤስኤፍ እና አጋሮቻቸው በሆኑ ሚሊሻዎች እንደሆነ ተገልጿል።

የሱዳን ጦር እና አጋሮቹም ወሲባዊ ጥቃት በማድረስ ተከስሰዋል።

የተመድ የሰብአዊ መብቶች ኃላፊ ቮልከር ቱርክ፤ ወሲባዊ ጥቃት እንደ "ጦር መሣሪያ" ጥቅም ላይ ውሏል ብለዋል።

"ይህ የጦር ወንጀል ነው፤ የስልታዊ ጥቃት እና ሰብአዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል አካልም ነው" ሲሉም አክለዋል።

አርኤስኤፍ እና የሱዳን ጦር በሪፖርቱ ላይ እስካሁን አስተያየት አልሰጡም። ከዚህ ቀደም ግን መሰል ክሶችን አስተባብለዋል።

በዓለም የከፋውን ሰብአዊ ቀውስ ባስከተለው የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ሳቢያ 11 ሚሊዮን ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። 28 ሚሊዮን ሰዎች ለአስከፊ ረሃብ መጋለጣቸውን የተራድኦ ድርጅቶች ገልጸዋል።

በሌሎች አካባቢዎች የሚፈጸም ጥቃትን በመሸሽ ወደ 200,000 የሚጠጉ ሰዎች በኤል-ኦቤይድ ከተማ ተጠልለዋል። አሁን ከተማዋ ዋነኛ የጦር አውድማ በመሆኗም ለአደጋ ተጋልጠዋል።

አርኤስኤፍ እግረኛ ጦር ከማስገባቱ በፊት የድሮን ጥቃት እየፈጸመ እንደሚገኝ የሚጠቁሙ ሪፖርቶች ወጥተዋል።

አንድ የከተማው ነዋሪ "ተፈናቅለን እዚህ ከመጣን በኋላ ለሞት ተጋልጠናል፤ ፈርተናል" ስትል ለቢቢሲ ገልጻለች።

"እዚህ ከመጣን በኋላ እጣ ፈንታችን ይሄ ሆነ። መብላትም መጠጣትም አንችልም። የት እንሂድ? ከዚህ ወዴት እንሂድ?" በማለትም ተናግራለች።

ሌላ ሴትም የድሮን ጥቃት እንዳስፈራት ተናግራለች።

"በጣም ፈርተናል። በሥነ ልቦናም በአካላም ደኅንነታችን አደጋ ተጋርጦበታል" ብላለች።

ከተማዋ አርኤስኤፍ በሚቆጣጠራቸው የሱዳን ምዕራባዊ አካባቢዎች እና በሱዳን ጦር ሥር ባሉ ምሥራቃዊ ከተማዎች መካከል ስለምትገኝ ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታዋ የጎላ ነው።

በነዳጅ በበለጸገችው ኮርዶፋን ግዛት ስለምትገኝ ከተማዋን የሚቆጣጠው ኃይል ጫና ማሳደር እንደሚችል ተንታኞች ይናገራሉ።

አርኤስኤፍ በዳርፉር ግዛት ኤል-ፋሽርን ሲቆጣጠር እንደተፈጸመው ዓይነት መጠነ ሰፊ ጥቃት በኤል-ኦቤይድም ሊደርስ ስለሚችል ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ ዩኬ እና የአውሮፓ አገራት ባወጡት መግለጫ አሳስበዋል።

"አምና በኤል-ፋሽር ዓለም የተመለከተው ለዘር ጭፍጨፋ የቀረበ ጥቃት ነው። ይሄ እንዲደገም መፍቀድ የለብንም" ብለዋል።

አርኤስኤፍ ኤል-ፋሽርን ሲቆጣጠር በሦስት ቀናት ብቻ ከ6,000 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ተመድ አስታውቋል።