በዩኬ የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ሲዘጋጁ ነበር የተባሉ አምስት ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

መሣሪያ የያዙ ፖሊሶች እና የፖሰስ መኪኖች
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በዩናይትድ ኪንግደም የሽብር ድርጊት እና የፈንጅ ጥቃት ለመፈፀም በዝግጅት ላይ ነበሩ የተባሉ አምስት ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ።

ግለሰቦቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሦስት አጠራጣሪ ተሽከርካሪዎች ወደ ራፍ የጦር ሠፈር አቅጣጫ ካመሩ በኋላ መሆኑን ፖሊስ ገልጿል።

እሑድ ዕለት ስለክስተቱ ሪፖርት ከተደረገ በኋላ በግላውሴስተርሻየር አውራጃ፣ ራፍ ፌርፎርድ በተባለው የሮያል አየር ኃይል ጣቢያ አቅራቢያ ያሉ በርካታ ነዋሪዎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ተደርጓል።

በጦሩ ፈንጅ አስወጋጅ ቡድንም የአሜሪካ አየር ኃይል ይጠቀምበት በነበረው የጦር ሠፈሩ አቅራቢያ ያሉትን ተሽከርካሪዎች የፈተሸ ሲሆን ፀረ ሽብር ፖሊስም ምርመራ እያካደሄ ነው።

በአቅራቢያው ከሚገኘው ዌልፎርድ መንደር እንዲወጡ የተደረጉ ነዋሪዎችም እሁድ ምሽቱን ወደ ቤታቸው መመለስ እንደማይችሉ ተነግሯቸዋል። ሆኖም ባለሥልጣናት የታቀደው ጥቃት በቁጥጥር ሥር ውሏል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል።

አንድ የአካባቢው ነዋሪ በጦር ሠፈሩ አጠራጣሪ ነገር ካየች በኋላ ለፖሊስ ማሳወቋን ለቢቢሲ ተናግራለች።

ስሟ እንዲጠቀስ ያልፈለገችው ነዋሪዋ መጀመሪያ ወደ መከላከያ ሚኒስቴር ፖሊስ መደወሏን እና ማንም እንዳልመለሰላት ከዚያ ግን ወደ ድንገተኛ አደጋ የጥሪ ማዕከል 999 መደወሏን አስረድታለች። ነዋሪዋ ሦስት ተሽከርካሪዎች እና ማስክ ያደረጉ ሰዎች መመልከቷን ተናግራለች።

መከላከያ ሚኒስቴር ነዋሪዋ ባለችው ላይ አስተያየት ለመስጠት አልፈቀደም።

አምስቱ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ሲውሉ የሚያሳይ ምሥልም ለቢቢሲ ተልኳል። ምሥሉ በዌልፎርድ በቁጥጥር ሥር የዋሉትን ግለሰቦች ያሳያል።

ቢቢሲ የምስሉን ዋነኛ ምንጭ ባያረጋግጥም ቢቢሲ ቬሪፋይ አካባቢው ትክክለኛ መሆኑን አረጋግጧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አንዲይ በርንሃም " እጅግ አሳሳቢ" ስለሆነው ሁኔታ እንዲያውቁ ተደርገዋል።

አካባቢው ከአሜሪካ ጦር ጋር የሚጋራው ረዥም ታሪክ ያለው ሲሆን በቅርቡም የአሜሪካ የጦር አውሮፕላኖች በኢራን ጦርነት ወቅት ማረፊያ ሆነው አገልግለዋል።

ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በአሁኑ ክስተት በቁጥጥር ሥር የዋሉ ግለሰቦች ትልቅ ውድመት ለማድረስ ሲፈልጉ የነበሩ ናቸው ብለዋል። " ለረዥም ጊዜ ስንከታተላቸው ነበር፤ አሁን አግንተናቸዋል" ሲሉም አክለዋል።

የዩኬ የመከላከያ ሚኒስትር ዌስ ስትሪቲንግ በበኩላቸው ከአሜሪካው አቻቸው ፒት ሄግሴት ጋር በጉዳዩ ላይ መነጋገራቸውን ገልጸዋል።

የአሜሪካ አየር ኃይል ቃል አቀባይ እንዳሉት ወታደሮቹ በጥንቃቄ ሲከታተሉት መቆየታቸውን የጠቀሱ ሲሆን ኃይሉ ራሱን ስለሚጠብቅበት የተለየ መንገድ አለመነጋገራቸውን ተናግረዋል።

የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር የአሜሪካ አየር ኃይል ተዋጊ አውሮፕላኖች ማረፊያ በነበረውና በሰፎልክ አውራጃ በሚገኘው ራፍ ላክንኸልዝ የተፈጠረውን የደኅንነት ስጋትም ሁለተኛ ደረጃ ላይ አስቀምጦታል።

የፀረ ሽብር ፖሊስ እና የግላውሴስተርሻየር ፖሊስ ምርመራው ገና ጅምር ላይ መሆኑን ገልጸው አምስቱ ተጠርጣሪዎች ከእሁድ ምሽት ጀምሮ በቁጥጥር ሥር መሆናቸውን አስታውቀዋል።