በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው ጦርነት ሊሰፋ ይችላል በሚል ስጋት ውስጥ የሚገኙት የትግራይ ነዋሪዎች

መቀለን የሚጠብቁ የጸጥታ ኃይሎች
የምስሉ መግለጫ, የትግራይ መዲና የሆነችውን መቀለን የሚጠብቁ የጸጥታ ኃይሎች
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

በህወሓት ኃይሎች እና በፌደራል መንግሥቱ መካከል ዳግም ውጊያ የተቀሰቀሰው ረቡዕ ዕለት ነበር።

በ2012 ተጀምሮ ለሁለት ዓመት ከቆየው ጦርነት ያላገገሙት የትግራይ ነዋሪዎች ዳግም ወደ ሁሉን አሳታፊ ጦርነት ይገባ ይሆናል በሚል ፍርሃት ውስጥ ናቸው።

አርብ ዕለት በኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት እና በአማፂያኑ መካከል በተለያዩ ግንባሮች ከባድ ጦርነቶች ሲደረጉ መዋላቸው ተሰምቷል።

በትግራይ የኢትዮ ቴሌኮም የስልክ እና የኢንተርኔት መስመር የተቋረጠ ሲሆን ይህም በሸቀጦች ግብይት እና በገንዘብ ዝውውር ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩን ነዋሪዎች ለሮይተርስ እና የፈረንሳይ ዜና ወኪሎች ተናግረዋል።

ህወሓት በክልሉ የሚገኙ ሦስት አውሮፕላን ማረፊያዎችን በቁጥጥሩ ሥር በማድረግ "ተከፈተብን" ያለውን ጥቃት ለመከላከል ታጣቂዎቹ እርምጃ እንዲወስዱ ማዘዙን ያስታወቀው ረቡዕ ዕለት ነበር።

ሐሙስ ሌሊት ጀምሮ በትግራይ የኢትዮቴሌኮም የስልክ አገልግሎት መቋረጡን ተከትሎ በርካታ የክልሉ ነዋሪዎች አማራጭ ሲምካርድ ለመግዛት ሲሯሯጡ ተስተውለዋል።

በርካታ የክልሉ ነዋሪዎች በ2012 ዓ.ም በተቀሰቀሰው እና ለሁለት ዓመት በቆየው ደም አፋሳሽ ጦርነት ወቅት እንደታየው በክልሉ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የባንክ አገልግሎት እንዲሁም የእርዳታ መቋረጥ ሊያጋጥም ይችላል የሚል ፍርሃት ውስጥ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በትግራይ ለሁለት ዓመት በተካሄደው እና በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተፈረመው የሰላም ስምምነት በተቋጨው ጦርነት ከ600,000 በላይ ሰዎች መሞታቸው ይገመታል።

Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የፈረንሳይ የዜና ወኪል ያነጋገራቸው የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅት ሠራተኛ ወደ አፋር ለመግባት የሞከሩ የትግራይ ኃይሎችን ለመከላከል ሐሙስ "ሌሊቱን ከባድ ውጊያ" መካሄዱን እና ትግራይን እና አፋርን በሚያዋስነው አካባቢ በምትገኘው በአባላ ከተማ ተራራማ ስፍራዎች የድሮን ጥቃቶች መፈጸማቸውን ተናግረዋል።

እኚሁ ምንጭ አክለውም በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሊፈናቀሉ ይችላሉ ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

የፖለቲካ ግጭቶችን፣ የትጥቅ ውጊያዎችን የሚከታተለው አክሌድ በበኩሉ በምዕራብ ትግራይ ማይ ጋባ እና ጸሊሞ አካባቢዎች ግጭት መቀስቀሱን አስታውቋል።

አክሎም በርካቶች በአካባቢው ለሚገኝ የፌደራል መንግሥቱ ኃይሎች እጃቸውን ቢሰጡም ወዲያውኑ ግን ቁጥራቸው ምን ያህል እንደሆነ በግልጽ የማይታወቅ አዲስ ተዋጊዎች መተካታቸውን ጠቅሷል።

ሐሙስ ዕለት በሰሜን ወሎ በታሪካዊቷ ላሊበላ ግጭቶች ተቀስቅሰው እንደነበር ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል። በዚህም የተነሳ ወደ አካባቢው የሚደረግ የአውሮፕላን በረራ የተቋረጠ ሲሆን ዳግም ስራ ስለመጀመሩ እስካሁን ድረስ አልታወቀም።

የዜና ወኪሉ ያነጋገራቸው እና ስማቸው ያልተጠቀሰ አንድ የፖለቲካ ተንታኝ ህወሓት ከዚህ ቀደም በነበረው ጦርነት የተጠቀመበትን ስልት ዳግም እየተገበረው ይመስላል ብለዋል።

የህወሓት ታጣቂዎች ወደ አዲስ አበባ ለሚያደርጉት ጉዞ በደቡብ በኩል ጫና በመፍጠር እና ውጊያዎችን በማድረግ ለመግፋት እየሞከሩ እንደሚመስል እኚሁ ተንታኝ ገልጸዋል።

በአፋር በኩል የሚደረገው ውጊያ እንዲሁ የአገሪቱ ነዳጅን ጨምሮ የወጪ እና የገቢ ንግድ የሚጓጓዝበትን የጂቡቲ መስመር ለመቁረጥ ያለመ ሊሆን እንደሚችል ተንታኙ ጨምረው ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ መንግሥት ከፍተኛ የሆነ የወታደራዊ ብልጫ አለው የሚሉት የፖለቲካ ተንታኙ ይህም በርካታ ድሮኖች፣ ወደ 500,000 የሚጠጉ ወታደሮች ያሉት እንደሚያካትት አብራርተዋል።

የአክሌድ ኃላፊ ክሊዮናህ ሬሌይ ባወጡት ሪፖርት ሁኔታው ገና ወደ ሙሉ ጦርነት ባይሸጋገርም፣ ግጭቱ ከዚህ በላይ እንዳይባባስ የሚያግድ "ምንም ዓይነት መቆጣጠሪያ ዘዴ" እንደማይታይ ገልጸዋል።

የባሕር በር አልባ የሆነችው ኢትዮጵያ ወረራ በመፈጸም በቀይ ባሕር ወደብ ለማግኘት እያቀደች ነው የሚል ስጋት ያላት ጎረቤት አገር ኤርትራም በዚህ ግጭት ከአማፂያኑ ወገን እንድትሳተፍ ሊያደርጋት ይችላል ብለዋል።

ራሌይ እንደሚሉት፣ አሁን ላይ በርካታ ቡድኖች እና የተለያዩ ፍላጎቶች በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ውስጥ ስለተሳተፉ፣ ጦርነቱ እየቀዘቀዘ ይሄዳል ወይም ቀደም ሲል ወደነበረው በአንጻራዊ ሁኔታ ውስን ወደሆነው ውጊያ ይመለሳል ተብሎ አይጠበቅም ብለዋል።

የአሜሪካ፣ የፈረንሳይ እና የዩናይትድ ኪንግደም ኤምባሲዎች በዚህ ሳምንት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጎን በመቆም በህወሓት ጥቃት "ቅር መሰኘታቸውን" አስታውቀዋል።

በመቀለ ሱቅ ደጃፍ የቆሙ ሰዎች
የምስሉ መግለጫ, በትግራይ ነዋሪዎች መሠረታዊ የምግብ ፍጆታዎችን ለመግዛት ሲጣደፉ ታይተዋል

በትግራይ ነዋሪዎች ምግብ ነክ ሸቀጦችን በመግዛት ለማከማቸት ሲጣደፉ የመሠረታዊ እቃዎች ዋጋ ጨምሯል።

"በማኅበረሰቡ ውስጥ ድንጋጤ አለ" ሲሉ በትግራይ ዋና ከተማ መቀለ በሚገኝ የቅመማ ቅመም ሱቅ ውስጥ የሚሠራው የ37 ዓመቱ ሳሙኤል ገብረስላሴ ሐሙስ ዕለት ለኤኤፍፒ ተናግሯል።

"ባንኮች፣ የስልክ አገልግሎት፣ የኤሌክትሪክ ኃይል እና መሠረታዊ እቃዎች እንደገና ሊቋረጡ ይችላሉ የሚል ትልቅ ፍርሃት አለ"

ኤኤፍፒ ያነጋገራቸው የመቀለ ነዋሪዎች በፌዴራል መንግሥቱ እና ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ለመጣል እንደሚፈልጉ በተናገሩት አማፂያን መካከል የሚደረገው ውጊያ ፍርሃት መጫሩን ተናግረዋል። ብዙዎቹም ከግጭቱ ለማምለጥ ወደ ሌሎች ክልሎች ለመሸሽ እየሞከሩ እንደሆነ ተዘግቧል።

አንዳንዶች ለአሶሼትድ ፕሬስ እንደተናገሩት በሰሜን ኢትዮጵያ ክፍሎች የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡን እና የትግራይ ሰሜናዊውን ክፍል ከአጎራባች አፋር ክልል ጋር የሚያገናኙ መንገዶች ለመኪና እንቅስቃሴ ተዘግተዋል።

በትግራይ ዋና ከተማ መቀለ ውስጥ ነጭ ሽንኩርት የምትሸጥ ሰላም ፋንታይ "የፍርሃት ድባብ አለ" ብላለች። "የትራንስፖርት አገልግሎቶች መቋረጡ የዳግም ግጭት መከሰትን ያመለክታል ሲሉ ሰዎች በጣም ያሳስባቸዋል።"

የፈረንሳይ የዜና ወኪል መንገዶች ለመኪና እንቅስቃሴ ዝግ መሆናቸውን በገለልተኛነት ማረጋገጥ አልቻለም።

በመቀለ የሚኖሩት ነጋዴው ኃይላይ መለስ በበኩላቸው የመጓጓዣ መስመሮች መስተጓጎል የአስፈላጊ ሸቀጦች ዋጋ እንዲጨምር ሊያደርግ ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ተናግረዋል። "ይህ ግጭት እስካለ ድረስ የመሠረታዊ ሸቀጦችን ዋጋ ከፍ ማድረጉን ይቀጥላል" ሲሉ አቶ ኃይላይ ተናግረዋል።

የአፋር አርብቶ አደር ልማት ማኅበር መስራች አባል የሆኑት ቫለሪ ብራውኒንግ፣ ብዙ ሰዎች ከትግራይ ወደ አፋር እየሸሹ መሆናቸውን ተናግረዋል። ተኩሶች እና ፍንዳታዎችም ሌሊቱን ይሰሙ እንደነበር ገልጸዋል።

እርሳቸው እንደሚሉት "እጅግ ብዙ ሰዎች እየተፈናቀሉ ነው። አምቡላንሶችን ጨምሮ ተሽከርካሪዎቻችን ለመንግሥት የጦርነት አገልግሎት እየተወሰዱብን ነው" ብለዋል።

መንግሥት ዳግም ስለተቀሰቀሰው ግጭት ምን አለ?

በዚህ ሳምንት ለተቀሰቀሰው ጦርነት ህወሓትን ተጠያቂ ያደረገው የፌደራል መንግሥቱ በተጨማሪ አዲሱን ጥምረት አገሪቱን ለማተራመስ የተደረገ ሙከራ አድርጎ በመግለጽ ተችቷል።

ኤርትራንም በኢትዮጵያ ውስጥ የታጠቁ ቡድኖችን በመደገፍ የከሰሰ ቢሆንም አሥመራ ግን ይህንን አስተባብላለች።

በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው የሁለት ዓመቱ ጦርት ወቅት ኤርትራ ከኢትዮጵያ ወታደሮች ጎን ተሰልፋ ተዋግታለች።

ይህንንም ተከትሎ ጠቅላይ ሚነስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ግንኙነታቸውን ያደሱት ሁለቱ አገራት ዳግም ተቃቅረዋል።

አለመግባባታቸው ማዕከል ያደረገው በቀይ ባሕር እና በወደብ ላይ ያተኮረ ነው።

ኢትዮጵያ የባሕር በር ያጣችው እና ወደብ አልባ የሆነችው በሐምሌ 1983 ዓ.ም. ኤርትራ በራሷ ፈቃድ ነፃ ወጥታ የራሷን ሪፐብሊክ ማቋቋሟን ተከትሎ ነው።

ጦርነቱ ወደሌሎች አካባቢዎች ሊስፋፋ ይችላል?

አሁን በትግራይ እና በአጎራባች ክልሎች ድንበር አካባቢ የተቀሰቀሰው ጦርነት ወደሌሎች ክልሎች ሊስፋፋ ይችላል የሚል ስጋት አለ።

ጦርነቱ በትግራይ ድንበር አካባቢዎች እየተካሄደ ሲሆን መንግሥት ደግሞ በተመሳሳይ ጊዜ በሌሎች ክልሎች በተለይም በአማራ እና በኦሮሚያ በሚካሄዱ የትጥቅ ግጭቶች ላይ እየተዋጋ ነው።

አዲሱ ጥምረት ከእነዚህ ግጭቶች ውስጥ ብዙዎቹን በፖለቲካዊ እና በወታደራዊ ጉዳዮች ሊያገናኝ ይችላል።

ኤርትራ በዚህ ጦርነት ዳግም መንግሥትን በመቃወም ልትሳተፍ ትችላለች የሚል ስጋት በተለያዩ አካላት ዘንድ ይንጸባረቃል።

የአፍሪካ ኅብረትም በተለይ ሁሉም አጎራባች አገራት ቀውሱን የበለጠ ሊያባብሱ ከሚችሉ እርምጃዎች እንዲቆጠቡ አሳስቧል።