የኢራን ልዑክ ወደ አሜሪካ የሄደው "ለሰላም ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር" መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤን ለመታደም ከፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን ጋር ወደ አሜሪካ የተጓዙት የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ለአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን የኢራን ልዑክ ወደ ኒውዮርክ ያመራው "ለሰላም ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር" ነው አሉ።
ሚኒስትሩ አክለውም "ኢራን ለማንኛውም ጥቃት በጽናት ትቆማለች። በተመሳሳይ ጊዜ፣ ለእውነተኛ ዲፕሎማሲም ዝግጁ ነን" ሲሉ ተናግረዋል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ይህንን አስተያየት የሰጡት፣ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሆርሙዝን የባሕር ወሽመጥ ዳግም ለመክፈት ኢራን ያቀረበችውን ሀሳብ "አለመቀበላቸውን" ተከትሎ ነው።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ዕቅዱን አለመቀበላቸው ከተሰማ በኋላ በጥቂት ቀናት ውስጥ ከኢራን ጋር ተጨማሪ ውይይቶች እንደሚደረጉ መግለጻቸው ታውቋል።
አራግቺ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ እንደተናገሩት፣ አሜሪካ በኢራን የቀረበውን ዕቅድ ከተቀበለች የሆርሙዝ የባሕር መስመር በሰባት ቀናት ውስጥ ይከፈታል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ከአሜሪካ ጋር ያለው ግጭት የሚገታው “በድርድር መፍትሔ ላይ ሲደረስ ብቻ” መሆኑን ተናግረው ነበር።።
የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመክፈት የቀረቡት ቅድመ ሁኔታዎች ከዚህ ቀደም ሰኔ ወር ላይ በኢራን እና አሜሪካ መካከል በተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ ላይ ካሉ ቅድመ ሁኔታዎች ጋር ተመሳሳይ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

