በደቡብ አፍሪካ ፖሊስ የግድያ ጉዳዮችን እየመረመረ ባለበት ወቅት 10ኛ የሴት አስከሬን ተገኘ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ ከጆሃንስበርግ በስተምሥራቅ በምትገኘው ኤኩሩሌኒ አካባቢ ሌላ የሴት አስከሬን መገኘቱን ገለፀ።
ይህም በዚያ አካባቢ በቅርብ ወራት ውስጥ ሞተው የተገኙ ሴቶችን ቁጥር ወደ 10 ከፍ አድርጎታል።
አስከሬኑ ቅዳሜ ጠዋት የተገኘ ሲሆን፣ ከሟቿ ጋር ባለፈው ምሽት በአንድ መጠጥ ቤት የነበረች ጓደኛዋ ማንነቷን አረጋግጣለች።
በኤኩሩሌኒ በተከሰቱት 10 ሞቶች እና በሶዌቶ በተመዘገበው ሌላ ሞት መካከል ተመሳሳይነቶች እንዳሉ በማንሳት፣ ተከታታይ ግድያዎችን የሚፈፅም ገዳይ በነጻነት እየተንቀሳቀሰ ሊሆን ይችላል የሚለውን ግምት ማጣጣል አንችልም ሲሉ የአካባቢው ፖሊስ ኮሚሽነር ተናግረዋል።
እነዚህ ግድያዎች ከፍተኛ የሆነ ፆታ-ተኮር ጥቃት ካለባቸው የዓለም አገራት መካከል በምትመደበው ደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ ቁጣ አስነስተዋል።
የቅርብ ጊዜው አስከሬን የተገኘው ከጆሃንስበርግ በስተሰሜን ምሥራቅ በሚገኘው ተምቢሳ ሰፈር ውስጥ ባለ የመቃብር ስፍራ ነው።
ፖሊስ አስከሬኑ ከተገኘ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ባወጣው መግለጫ፣ መርማሪዎች በስፍራው ተገኝተው ማስረጃዎችን እየሰበሰቡ መሆኑን ገልጿል። ባለሥልጣናቱ የሟቿን ማንነት እስካሁን በይፋ አልገለፁም።
የሟች ጓደኛ ለአገሪቱ ብሔራዊ ሚዲያ ኤስኤቢሲ እንደተናገረችው፣ የአስከሬኑን ፎቶ ሲያሳዩአት ጓደኛዋ ባለፈው ምሽት የለበሰቻቸውን ልብሶች በማየት ለይታታለች።
"ለልጆቿ ምን እንደምል አላውቅም" ስትል እንባዋን እየጠረገች ተናግራለች። "በጣም ያማል።"
የጋውቴንግ ግዛት የፖሊስ ኮሚሽነር ቶሚ ምቶምቤኒ፣ ገና በመጀመሪያ ደረጃ ምርመራ ላይ በመሆናቸው የዚህች ሴት ሞት ከሌሎቹ ጉዳዮች ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ ለመናገር "ጊዜው በጣም ገና ነው" ብለዋል።
ይሁን እንጂ ቀደም ሲል የተገኙት አስከሬኖች "ተመሳሳይ የጉዳት ባህሪያት" እንዳላቸው እና ይህም ተመሳሳይ "የወንጀል አፈጻጸም" መኖሩን እንደሚያመለክት ኮሚሽነሩ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ ተናግረዋል። ይህም ፖሊስ ይህ የቅርብ ጊዜ ሞት ከቀደሙት ሞቶች ጋር የተገናኘ መሆኑን ለመወሰን ያግዛል ብለዋል።
"በአሁኑ ወቅት ተከታታይ ግድያዎችን የሚፈፅም ገዳይ አለ ወይም የለም ብለን ሙሉ በሙሉ ልንደመድም አንችልም" ሲሉ ሌተናል ጄኔራል ምቶምቤኒ ተናግረዋል።
ደቡብ አፍሪካ በዓለም ላይ ከፍተኛ ግድያ ከሚፈፀምባቸው አገራት መካከል ስትሆን፣ በአውሮፓውያኑ ካለፈው ሚያዝያ እስከ ሰኔ ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ 5,427 ሰዎች ተገድለዋል።
ነገር ግን በቅርቡ በጆሃንስበርግ አካባቢ የተፈፀሙት ግድያዎች ባህሪ ብዙ ሴቶችን እያስደነገጠ ሲሆን፣ የሟቾች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱም ስጋታቸውን አባብሶታል።
ከሐምሌ ወር ጀምሮ የተገኙት 10 አስከሬኖች ተመሳሳይነት ባለው ሁኔታ የተገኙ ናቸው። አብዛኞቹ የተገኙት ከተምቢሳ አጎራባች በሚገኘው ኬምፕተን ፓርክ አካባቢ ነው።
ብዙዎቹ አስከሬኖች የወጣት ሴቶች ሲሆኑ፣ ከመሞታቸው በፊት እጅግ ከባድ ጥቃት እንደደረሰባቸው ታውቋል።
የአገሪቱ መንግሥት ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃት ብሔራዊ አደጋ መሆኑን ካወጀ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የተከሰቱት እነዚህ ሞቶች በመንግሥት ላይ ያለውን ጫና አበርትተዋል።
የደቡብ አፍሪካ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ባለፈው ሳምንት እንዳስታወቀው፣ ከሚያዝያ እስከ ሰኔ ባለው ጊዜ ውስጥ 569 ሴቶች ተገድለዋል፤ ሌሎች 1,052 ሴቶች ደግሞ ከግድያ ሙከራዎች ተርፈዋል።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ሦስት ወንዶች ከከዚህ ቀደም ከተመዘገቡት ዘጠኝ ግድያዎች በአንዱ ተሳትፎ አላቸው በሚል ተከሰው ፍርድ ቤት ቀርበዋል።
ፖሊስ በግድያዎቹ ተሳትፎ ያላቸው ሌሎች ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ ምርመራውን እንደቀጠለ ነው።



































