የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ስለተመሠረተው የታጣቂ ቡድኖች ጥምረት ምን አለ?

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ዋና አዛዥ አማካሪ የሆኑትን አቶ ጂሬኛ ጉደታ
የምስሉ መግለጫ, የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ዋና አዛዥ አማካሪ የሆኑት አቶ ጂሬኛ ጉደታ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ተለይቶ የትጥቅ እንቅስቃሴ የሚያደርገው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (ኦነሠ) አዛዥ አማካሪ ከቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ስለ ኢትዮጵያ ቀጣይነት እና በቅርቡ ስለ ተመሠረተው እና አባል ስለሆነበት የታጣቂ ቡድኖች ጥምረት ተናግረዋል።

ከህወሓት እና ከፋኖ ጋር በመሆን "ትብብር ለኅልውና" የሚል ጥምረት የመሠረተው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት "በኢምፓየሯ [ኢትዮጵያ] ያለው ሥርዓት መፍረስ አለበት" የሚለውን አቋሙን እንዳልተወ አስታውቋል።

ሰባት ታጣቂ ቡድኖች የኢትዮጵያ መንግሥትን በኃይል ለመጣል በማቀድ "ትብብር ለኅልውና" የተሰኘ ጥምረት መመሥረታቸውን ይፋ ያደረጉት ባለፈው ሳምንት እሁድ ዕለት ነበር።

በጥምረቱ ውስጥ ከተካተቱት የታጣቂ ቡድኖች መካከል የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት፣ ህወሓት እና የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን) ይገኙበታል።

ከእነዚህም በተጨማሪ የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦነብግ)፣ የአፋር ብሔራዊ አንድነት አብዮታዊ ግንባር፣ የቤኒሻንጉል ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ እና የጉሙዝ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ የጥምረቱ አካል ናቸው።

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አዛዥ አማካሪ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ከህወሓት እንዲሁም ከፋኖ ጋር ስለመሥራት እና ስለመተባበር ሲጠየቁ ቡድናቸው "የጥንቱ አቋማችን ላይ ነን፤ የኢምፓየሩ ሥርዓት መፍረስ አለበት የሚለውን አቋማችንን አልተውንም" ሲሉ መልሰዋል።

በኦሮሚያ ክልል በተለይም በምሥራቅ ወለጋ እና ሆሮ ጉዱሩ ዞኖች ኦነሠን ጨምሮ የተለያዩ ታጣቂ ቡድኖች በሚፈጽሙት ጥቃት የተነሳ የአካባቢው ሕዝብ ላለፉት አምስት ዓመታት በሰላም እጦት እየተሰቃየ ነው።

ነዋሪዎቹ በተለያየ ጊዜ ለቢቢሲ "በሦስት ጥይት እየተመታን ነው" ሲሉ ከመንግሥት ወታደሮች እንዲሁም በፋኖ ስም ከሚንቀሳቀሱ እና ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አማፂያን ላይ ቅሬታቸውን ያሰማሉ።

Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከፋኖ ጋር በመሆን "ትብብር ለኅልውና" የሚል ጥምረት የመሠረተው በዚህ ሁሉ ቅሬታ መካከል ነው።

ቢቢሲ አፋን ኦሮሞ፣ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ዋና አዛዥ አማካሪ የሆኑትን አቶ ጂሬኛ ጉደታን ከፋኖ ጋር ባላቸው ግንኙነት ምን ያህል እንደሚተማመኑ ሲጠይቃቸው "በፖለቲካ ውስጥ መተማመን የሚባል ነገር የለም፤ ያለው የሕዝብ ጥቅምን ማስጠበቅ ብቻ ነው" ብለዋል።

አቶ ጂሬኛ አክለውም "አሁን የሚነደውን ትልቅ እሳት ትተን፣ ትንንሽ እሳት ያላቸውን አሳንሰን አናይም" ሲሉም በክልሉ እንደሚንቀሳቀስ ከተናገረው ፋኖ ጋር ወደፊት "በግልጽ እንደሚነጋገሩ" አስረድተዋል።

ድርጅታቸው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት የኦሮሞ ሕዝብ ጥቅም የሚያስጠብቅ ቡድን መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ከ50 ዓመት በፊት ሲመሠረት ጀምሮ ሕዝቡ ነጻ ሆኖ ራሱን እንዲያስተዳድር ማድረግ ከዓላማዎቹ መካከል አንዱ ነበር።

ኦነግ የትጥቅ እንቅስቃሴ የጀመረው የደርግ ወታደራዊ መንግሥት ሥልጣን ላይ ሳለ ነው።

ኦነግ የትጥቅ ትግል ሲያካሂድ ቆይቶ በደርግ መውደቂያ አቅራቢያ ከኤርትራው ህግሓኤ እና ከህወሓት ጋር ግንባር በመፍጠር የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም እና አሁን ያለው የአገሪቱን ሕገ መንግሥት በማዘጋጀት ጉልህ ሚና ነበረው።

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከኦሮሞ ነፃነት ግንባር ተገንጥሎ የወጣ ታጣቂ ቡድን ሲሆን፣ በተለያዩ የኦሮሚያ ክፍሎች ውስጥ ይንቀሳቀሳል።

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከዚህ ቀደም ኦነግን ወደ ጫካ ዳግም እንዲመለስ ካደረገው ህወሓት እንዲሁም በኦሮሚያ ታጣቂዎች እንዳሉት ከገለጸው ፋኖ ጋር የሚሠራው እንዴትት እንደሆነ አቶ ጂሬኛ ተጠይቀዋል።

አማካሪው ሲመልሱም በትብብር ለኅልውና ውስጥ የታቀፉት ታጣቂዎች በፖለቲካ አስተሳሰብ አንድ አለመሆናቸውን ተናግረዋል።

"እኛ ያደረግነው ትብብር የአሠራር ሂደት ብቻ ነው እንጂ አንድ አልሆንም።... በመጀመሪያ፣ አንድ ነን ብሎ መናገር ትልቅ ስህተት ነው። እኛ የተነጋገርነው በውይይት ሂደት እና ሕዝባችን የራሱን ሚና በነፃነት በሚወስንበት ሂደት ላይ ነው" ብለዋል።

አቶ ጂሬኛ አክለውም "ትብብር ለኅልውናን" ለመመሥረት ያነጋገሯቸው አካላት ወደ ኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መምጣታቸውን ገልጸው፣ "እነርሱ ናቸው ወደ እኛ የመጡት፣ እኛ አይደለንም ወደ እነርሱ የሄድነው" ብለዋል።

አቶ ጂሬኛ ይህንን ሲያብራሩም የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ኢትዮጵያ "ለማፍረስ" ያላውን አቋም አለመተዉን ተናግረዋል።

"እኛ ያለንበት ቦታ ያው ነው። የኢምፓየሩ ሥርዓት መፍረስ አለበት የሚለው አቋማችንን አልተውንም። እነርሱ መጥተው ያንን ሥርዓት፣ ያንን ኢምፓየር እንደሚያፈርሱት ሲናገሩ እንደግፋቸዋለን። ከስትራቴጂያችን አላፈነገጥንም።"

አቶ ጂሬኛ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን ወደ "ትብብር ለኅልውና" እንዲቀላቀል ግብዣ ያቀረበለት ማን እንደሆነ አልተናገሩም።

ነገር ግን "የኢምፓየሩን ሥርዓት እናፍርስ? ብለው ሲጠይቁን 'አይሆንም' ካልክ፣ ሞኝ ነህ ማለት ብለዋል።

ቡድኑ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ድርደር ባደረገበት ወቅት አቋሙ ተመሳሳይ እንደነበር አቶ ጂሬኛ አስታውሰዋል።

"እኛ ያደረግነው የሁሉም ሕዝቦች መብት የሚከበርበትን አሠራር መዘርጋት ነው። ይህ ስህተት ሊሆን አይችልም። ከብልጽግና ፓርቲ ጋር ስንደራደርም ያደረግነው ይህንኑ ነው።"

ቢቢሲ አቶ ጂሬኛን ፋኖ ካለው አቋም ጋር እንዴት ተስማምተው እንደሚሠሩ ሲጠይቃቸው "እኛ የተባበርንበት ምክንያት ሕዝባችንን የሚገድል አካል አለ፤ የደኅንነት ስጋትም አለ።. . . ይህ ደግሞ የሚያመለክተው ዛሬ ያለውን ሁኔታ ነው፤ ማለትም የመንግሥት ሥልጣን በእጁ ያለውን አካል ነው" ብለዋል።

በሥልጣን ላይ ያለው አካል ፋኖ እና ህወሓት አለመሆናቸውን በመግለጽም "ሕዝቡ የራሱን ዕድል በራሱ የሚወስንበትን ሥርዓት ካልተቃወሙ" በስተቀር ችግር እንደማይኖርባቸውም አስረድተዋል።

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በ'ትብብር ለኅልውና" ውስጥ በመሳተፉ "የሚያጣው ነገር የለም። አመራሩ በትግል ሜዳ ላይ ነው ያለው። እንደ ቀድሞው ወጥመድ ውስጥ እንገባ ይሆን? ብለን መጨነቅ አያስፈልገንም። ሠራዊቱ ታጥቆ ነው ያለው፤ ትጥቁን አልፈታም፤ ዓላማውም በልቡ ውስጥ ነው። ታዲያ በዚህ ጉዳይ ምን የሚያስጨንቀው ነገር አለ?" ሲሉ አስረድተዋል።

በክልሉ በፋኖ ታጣቂዎች ስለሚፈጸሙ የተለያዩ ጥቃቶች የተጠየቁት አቶ ጂሬኛ "በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀልን ማንም ይፈጽመው ማንም ወንጀል ነው፤ የአገር ጠላትነት ነው" ካሉ በኋላ ታጣቂዎች ያላቸው አቅም ግን የፌደራል መንግሥቱ ከታጠቀው ጦር መሣሪያ እና ድሮን ጋር ማወዳደር እንደማይቻል ይናገራሉ።

አቶ ጂሬኛ የቡድናቸው ርዕዮተ ዓለም ከሌሎቹ በ"ትብብር ለኅልውና" ውስጥ ከተካተቱት ጋር እንደማይገናኝ ሲጠየቁም "በመጀመሪያ፣ ትልቅ አደጋ አለ፤ ትልቁ አደጋም 'ፒፒ' (ብልጽግና ፓርቲ) ነው። ከዚህ የበለጠ አደጋ አለ ብለን አናምንም። ስለዚህ፣ ይህንን አደጋ እናስወግዳለን። ከዚያም፣ ያንን ኃላፊነት ስንወስድ፣ ጊዜያዊው መንግሥት ተቋቁሞ ሥራውን ይጀምራል" ብለዋል።

የሽግግር መንግሥት ከተመሠረተ በኋላ የማያስማሙ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ቢኖሩ ለሕዝበ ውሳኔ እንደሚቀርብም ተናግረዋል።

ነገር ግን በዚህ ሂደት ውስጥ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከአቋሙ እንዳይዛነፍ የሚያደርግ አመራር መኖሩን ጨምረው ተናግረዋል።

"አሁን ያለው ትውልድ እንዲህ ዓይነት ኪሳራ እንዳይደርስበት የሚጠብቅ አመራር ቦታውን ይዞ ነው ያለው። ሠራዊቱ በእርሱ ቁጥጥር ስር ነው፤ እንደታጠቀ ነው፤ ዓላማውም በአእምሮው እና በልቡ ውስጥ ነው" ብለዋል።

የትብብር ለኅልውና አባላት የማይስማሙባቸው ጉዳዮችን በሕዝበ ውሳኔ እንደሚፈቱም ተናግረው "በማንስማማባቸው ጉዳዮች ላይ ያለንን ልዩነት ለሕዝብ እናቀርባለን፤ ሕዝቡ ውሳኔ ይሰጣል፤ ከዚያም ሕዝቡ የወሰነውን እንቀበላለን" ብለዋል።

የጥምረቱ አባል ቡድኖች ባጋሩት መገለጫ ላይ በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት በማስወገድ "በሽግግር ቻርተር የሚመራ አካታች የሽግግር መንግሥት" ለመመሥረት ዓላማ አላቸው።