የትግራይ ቴሌቪዥን ዋና መሥሪያ ቤት የድሮን ጥቃት እንደደረሰበት ኤኤፍፒ ዘገበ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እሁድ ዕለት በመቀለ በሚገኘው የትግራይ ቴሌቪዥን ዋና መሥሪያ ቤት የድሮን ጥቃት እንደተፈጸመበት የፈረንሳይ ዜና ወኪል (ኤኤፍፒ) ዘገበ።
ኤኤፍፒ ያነጋገራቸው እና ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ምንጭ "ከፍተኛ የድሮን ጥቃት ድምጽ ሰምተን ከሕንፃው ሮጠን ወጣን" ሲሉ ተናግረዋል።
መስከረም 17/2018 ዓ.ም. እሁድ ዕለት ተፈጸመ ስለተባለው ጥቃት እስካሁን ድረስ ክልሉን እያስተዳደረ ካለው ህወሓትም ሆነ ከፌደራል መንግሥቱ ምንም የተሰጠ አስተያየት የለም።
ቢቢሲ የጣቢያውን ኃላፊዎች እንዲሁም ነዋሪዎችን ለማነጋገር ያደረገው ጥረት የመገናኛ ዘዴዎች በመቋረጣቸው አልተሳካም።
የትግራይ ቴሌቪዥን የክልሉ መንግሥት ልሳን በመሆን የሚያገለግል ሲሆን ከሳምንት በፊት ሰባት አማፂያን ጥምረት መመስረታቸውን ይፋ ሲያደርጉ መግለጫው በዋናነት የተላለፈው በዚሁ ጣቢያ ነው።
ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን የትግራይ ቴሊቪዥንን ላልተወሰነ ጊዜ ያገደው ማገዱን ያስታወቀ ሲሆን ይህን ጣቢያ ምንጭ አድርገው የሚዘግቡ መገናኛ ብዙኃን ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል።
ኤኤፍፒ በአካባቢው የነበረ ጋዜጠኛ ያነሳውን ምሥል ያጋራ ሲሆን የዋና መሥሪያ ቤቱ ሕንፃ የተሰባበሩ መስታዎቶች እና በጭስ የጠቆረ ክፍል ይታያል።
ሌላ ጋዜጠኛ በበኩሉ ጣቢያው 400 ያህል ጋዜጠኞች እንዳሉት ገልጾ ከጥቃቱ በኋላ ሥርጭቶች መቋረጣቸውን ለኤኤፍፒ አስታውቋል።
በጥቃቱ ስለደረሰው ጉዳት እስካሁን ድረስ የተባለ ነገር የለም።
ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ዕለት በህወሓት የሚመሩት የትግራይ ኃይሎች በክልሉ የሚገኙ ሦስት የአውሮፕላን ማረፊያዎች በቁጥጥር ሥር ካዋሉ በኋላ ጦርነት ተቀስቅሷል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድም "ላልተወሰነ ጊዜ" ወደ ክልሉ የሚያደርጋቸውን በረራዎች ማቋረጡን አስታውቋል።
በፌዴራል ኃይሎች እና በትግራይ ኃይሎች መካከል የተቀሰቀሰው ይህ አዲስ ግጭት እየተስፋፋ መምጣቱን ተከትሎ፣ አርብ ዕለት በሰሜን ኢትዮጵያ የኢትዮ ቴሌኮም የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጧል።
የህወሓት ታጣቂዎች ክልሉን ከአማራ እና ከአፋር ጋር በሚያዋስኑት አካባቢዎች ጥቃት መክፈታቸውን ተከትሎ ውጊያዎች ተጠናክረው መቀጠላቸው እየተነገረ ነው።
ኤኤፍፒ ያነጋገራቸው በሰብዓዊ እርዳታ ድርጅት ውስጥ የሚሰሩ ምንጮች ክልሉ ከአፋር ጋር በሚዋሰንበት አካባቢ የምትገኘው ኤርብቲ ከተማ እሁድ ዕለት በህወሓት እና በአጋሮቹ ቁጥጥር ሥር መዋሏን አስታውቋል።
አክለውም አማፂያኑ ወደ አፍዴራ ከተማ እየተቃረቡ መሆናቸውን ጨምረው አስታውቀዋል።
ቢቢሲ የኤኤፍፒ ዘገባን ከገለልተኛ ወገን ማጣራት አልቻለም።
ኤኤፍ ፒ ያነጋገራቸው ምንጭ ቢያንስ 150 ሺህ ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸውን ገልጸው፤ ነገር ግን ትክክለኛውን ቁጥር ለማስቀመጥ አስቸጋሪ መሆኑን ተናግረዋል።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በበኩላቸው ከኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት መገናኛ ብዙኃን ከአራት ቀን በፊት በሰጡት ቃለ ምልልስ "እየተዋጋን ያለነው የውጪ ኃይሎችን ፍላጎት ለማስፈጸም ከተሰባሰቡ እና ከተደራጁ ኃይሎች ጋር ነው" ብለዋል።
አክለውም "ሻዕቢያ [ኤርትራ] እና ቲፒኤልኤፍ [ህወሓት] ያለ ሱዳን፣ ያለ ግብጽ እና ከዚያም ባሻገር ያሉ ኃይሎች ካልደገፏቸው ብቻቸውን ተጣምረውም ቢሆን ዋጋ የላቸውም። ሲነጣጠሉ ደግሞ ትርጉም የላቸውም" ሲሉ ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም የኤርትራ፣ የሱዳን እና የግብጽ መንግሥታት የኢትዮጵያ አማፂያንን ያስታጥቃሉ የሚለውን ውንጀላ አስተባብለዋል።
ለሁለት ዓመት በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት ኃይሎች መካከል የተካሄደው ደም አፈሳሽ ጦርነት በፕሪቶሪያ ስምምነት ቢቋጭም ከቅርብ ወራት ወዲህ ግን አንዳቸው ሌላኛቸውን ስምምነቱን በመጣስ ሲካሰሱ ተደምጠዋል።
በአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት ጦርነቱ ሲቋጭ ወደ 600,000 የሚጠጉ ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል።
ህወሓት ባለፈው ሳምንት "የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን መንግሥት ለመጣል" ከሌሎች ስድስት የታጠቁ ቡድኖች ጋር ጥምረት መመስረቱን አስታውቋል።
በዚህ ሳምንት ለተቀሰቀሰው ጦርነት ህወሓትን ተጠያቂ ያደረገው የፌደራል መንግሥቱ አዲሱን ጥምረት አገሪቱን ለማተራመስ የተደረገ ሙከራ አድርጎ በመግለጽ ተችቷል።
በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው የሁለት ዓመቱ ጦርነት ወቅት ኤርትራ ከኢትዮጵያ ወታደሮች ጎን ተሰልፋ ተዋግታለች።
ይህንንም ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ግንኙነታቸውን ያደሱት ሁለቱ አገራት ዳግም ተቃቅረዋል።
የክልሉ መገናኛ ብዙኃን ዋና መሥሪያ ቤት ሕንጻ በድሮን መመታቱ የተሰማው ከ2013 እስከ 2015 ዓ.ም. የነበረውን አውዳሚ የትግራይ ጦርነት መልሶ ሊቀሰቅስ ይችላል የሚለው ስጋት በእጅጉ በጨመረበት ወቅት ነው።
ኤኤፍፒ እንደዘገበው፣ የትግራይ ኃይሎች ረቡዕ ዕለት ጀምሮ ወደ አጎራባች አፋር እና አማራ ክልሎች ጥቃት ሰንዝረዋል።
አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ (ዩኤኢ) እና ሌሎች አገራት ህወሓት እና አጋሮቹ በኢትዮጵያ የፌዴራል ኃይሎች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን አውግዘዋል።
የትግራይ ባለሥልጣናት በበኩላቸው ጥቃቱን የሰነዘሩት የፌዴራል ኃይሎች ጥቃት ካደረሱባቸው በኋላ እንደሆነ የተናገሩ ቢሆንም ስለ ግጭቱ የቀረቡት ክሶች በገለልተኛ አካል አልተረጋገጡም።
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አርብ ዕለት ስጋታቸውን የገለጹ ሲሆን፣ "በተለይም ድሮኖች ጥቅም ላይ ስለዋሉበት ሁኔታ እንዲሁም በሲቪል ሰዎች ላይ ጉዳት ስለደረሰባቸው ክስተቶች የተሰሙት ሪፖርቶች እጅግ እንዳሳሰቧቸው" ቃል አቀባያቸው ተናግረዋል።
በትግራይ ድንበር አካባቢዎች ጦርነቱ እየተካሄደ ሲሆን መንግሥት በተመሳሳይ ጊዜ በሌሎች ክልሎች በተለይም በአማራ እና በኦሮሚያ በሚካሄዱ የትጥቅ ግጭቶች እየተዋጋ ነው።
አዲሱ ጥምረት ከእነዚህ ግጭቶች ውስጥ ብዙዎቹን በፖለቲካዊ እና በወታደራዊ ጉዳዮች ሊያገናኝ ይችላል።
ኤርትራ በዚህ ጦርነት ዳግም መንግሥትን በመቃወም ልትሳተፍ ትችላለች የሚል ስጋት በተለያዩ አካላት ዘንድ ይንጸባረቃል።
የአፍሪካ ኅብረትም በተለይ ሁሉም አጎራባች አገራት ቀውሱን የበለጠ ሊያባብሱ ከሚችሉ እርምጃዎች እንዲቆጠቡ አሳስቧል።



































