በከፍተኛ ሙቀት ሳቢያ በፈረንሳይ፣ ጣልያን እና ስፔን ማስጠንቀቂያ ተሰጠ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ፈረንሳይ በከፍተኛ ሙቀት ሳቢያ ለግማሽ የአገሪቱ ክፍል የሙቀት ማዕበል ማስጠንቀቂያ ሰጠች።
ከዚህ ቀደም ከተመዘገበው መጠን በላይ የሆነ ሙቀት እየተጠበቀ ሲሆን፤ በደቡብ ምዕራብ ቦርዶክስ ከተማ እስከ 40 ዲግሪ ሴንቲግሬድ እንደሚደርስ ተገምቷል።
ከፍተኛው ሙቀት ከሰሀራ በረሃ ተነስቶ በምዕራብ እና ማዕከላዊ አውሮፓ የአየር መታፈን የሚፈጥር ነው።
የጣልያን ባለሥልጣኖችም ቦሎኛ፣ ፍሎረንስ፣ ሚላን፣ ሲድኒ እና ቱረንን ጨምሮ ለስምንት ከተሞች ከፍተኛ የሙቀት ማዕበል ማስጠንቀቂያ (ቀይ) ሰጥተዋል።
የስፔን የሜትሮሎጂ ባለሥልጣንም ቀይ እና ብርቱካናማ (መለስተኛ የሙቀት ማዕበል) ማስጠንቂያዎችን በተለያዩ የአገሪቱ ግዛቶች ሰጥቷል።
በስፔን ግዙፍ ከተሞች ውስጥ ሙቀቱ እስከ 40 ዲግሪ ሴንቲግሬድ እንደሚደርስ ተገልጿል።
በፈረንሳይ ባለፉት ቀናት ከፍተኛ ሙቀት እየጨመረ ሲሆን የመንግሥት ሥራ ላይ እና መጓጓዣ ላይም እክል ፈጥሯል።
የፈረንሳይ መንግሥት በዚህ ከፍተኛ ሙቀት ሳቢያ በጎዳና ላይ የሙዚቃ ፌስቲቫል የአልኮል መጠጥ እንዳይቀርብ ክልለካ ጥሏል።
ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው አደባባዮች የሚካሄደው ዓመታዊ ብሔራዊ የሙዚቃ ፌስቲቫል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ታዳሚዎች ያስተናግዳል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰባስሽያን ለኮርኑ ቢሮ ባወጣው መግለጫ "የመንግሥት ተቋማት በሚያዘጋጇቸው መሰናዶዎች ላይ አልኮል ማቅረብ አይቻልም" ብሏል።
የአልኮል መጠጥ ላይ እገዳ የተጣለው "የድንገተኛ ጊዜ ሕክምና ሰጪዎችን አገልግሎት ላለማስተጓጎል እና ሁሉም የሕክምና ባለሙያዎች ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ለማስቻል ነው" ተብሏል።
ዛሬ ሰኞ በአገሪቱ ከፍተኛ ሙቀት እንደሚመዘገብ ይጠበቃል። ከዚህ ቀደም ከተመዘገበው የላቀ እንደሚሆንም ተገልጿል።
ከፍተኛ የሙቀት ማዕበል ማስጠንቀቂያ (ቀይ) አብዛኛውን የፈረንሳይ ምዕራባዊ እና ማዕከላዊ አካባቢዎች ያዳርሳል።
የተቀሩት የአገሪቱ ክፍሎች መለስተኛ ማስጠንቀቂያ (ብርቱኳናማ) ተሰጥቷቸዋል።
ዛሬ ወደ 850 ትምህርት ቤቶች እንደሚዘጉ እና 1,500 ገደማ ታዳጊዎች እረፍት እንደሚሰጣቸው ተገልጿል።
በዩናይትድ ኪንግደም ከትናንት እሑድ አንስቶ ለአራት ቀናት የሚቆይ የከፍተኛ ሙቀት ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል።
ሙቀቱ እስከ 38 ዲግሪ ሴንቲግሬድ እንደሚደርስም ይጠበቃል።















