ተወልደ ገብረማሪያም የሚረከቡት የሕንዱ አየር መንገድ በምን አይነት ሁኔታ ውስጥ ያለ ነው?

ተወልደ ገብረማሪያም

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተወልደ ገብረማሪያም 'ኤር ኢንዲያ'ን እንዲመሩ ተሹመዋል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተወልደ ገብረማሪያም ከፍተኛ የፋይናንስ ኪሳራ ውስጥ የሚገኘውን እና ባለፈው ዓመት የ260 ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ የአውሮፕላን አደጋ ያጋጠመውን 'ኤር ኢንዲያ' እንዲመሩ ተሹመዋል።

ተወልደ የአየር መንገዱን ዋና ሥራ አስፈጻሚነት የተረከቡት ባለፈው ሚያዝያ ላይ ከኃላፊነቱ የወረዱትን ካምፔል ዊልሰንን ተክተው ነው።

ኢትዮጵያዊው ጉምቱ የኤቪዬሽን መሪ ከ30 ዓመት በላይ የቆዩበት እና ለ11 ዓመታት የመሩትን የኢትዮጵያ አየር መንገድ የለቀቁት በመጋቢት 2014 ዓ. ም. ነበር። በኃላፊነት ዘመናቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድን በአፍሪካ ቀዳሚው የአየር ትራንስፖርት አቅራቢ አድርገውታል።

በዋና ሥራ አስፈጻሚነት ቆይታቸው የአየር መንገዱ ገቢ በሦስት እጥፍ ያደገ ሲሆን ያሉት አውሮፕላኖች ቁጥርም በሦስት እጥፍ ገደማ ጨምሯል።

አሁን የሚረከቡት 'ኤር ኢንዲያ' በሕንድ መንግሥት ሥር የነበረ ነው። በአውሮፓውያኑ 2022 'ታታ ግሩፕ' የተባለው የአገሪቱ ግዙፍ የንግድ ቡድን ገዝቶታል።

በአሁኑ ሰዓት አስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ እያለፈ የሚገኘው ይህ አየር መንገድ፣ 198 አውሮፕላኖች አሉት። በሕንድ እና በውጭ አገራት ወደሚገኙ 91 መዳረሻዎቹ በሳምንት 5,000 ገደማ በረራዎችን እንደሚያደርግ ከድረ ገጹ የተገኘ መረጃ ያሳያል።

አዲስ ሥራ አስፈጻሚ ለማግኘት መጠነ ሰፊ ፍለጋ ሲያከናውን የነበረው የአየር መንገዱ ቦርድ ተወልደን የሾመው በሙሉ ድምፅ እንደሆነ ተገልጿል። ተወልደ ያላቸው የአመራር እና የሥራ ልምድ የአየር መንገዱን "ቀጣይ የእድገት ምዕራፍ" ለመምራት እንደሚያስችላቸው ተጠቅሷል።

የኤር ኢንዲያ ሊቀመንበር ኤን ቻንድራሴካራን "[በቀድሞው ሥራ አስፈጻሚ] ካምፕቤል አመራር የመጀመሪያ ምዕራፍ አካል የሆኑትን መረጋጋት፣ መዋሃድ እና ከአውሮፕላኖች ጋር የተያያዙ ተግባራት ያጠናቀቀው ኤር ኢንዲያ፣ አሁን ወሳኝ ወደሆነው የትግበራ እና የማስፋፊያ ዘመን እየገባ ነው" ብለዋል።

የቀድሞው የሲንጋፖር አየር መንገድ ሥራ አስኪያጅ ካምፔል ዊልሰን ኤር ኢንዲያን እንዲመሩ የተሾሙት ታታ ግሩፕ ከአራት ዓመት ገደማ በፊት ተቋሙን በገዛበት ወቅት ነው።

የቀድሞው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ከኃላፊነት እንደሚለቅቁ የጠቆሙት 2024 ላይ ነበር። በዘንድሮው ዓመት ከመልቀቃቸው አስቀድመውም አየር መንገዱ የተለሳለሰ የአመራር ሽግግር እንዲኖረው ሲሰሩ ቆይተዋል።

አሁን ተተኪ ሆነው የመጡት ተወልደ ገብረማሪያም፣ "የሕንድን ልዩ የኢኮኖሚ አቅም የሚያንፀባርቅ" እና "ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አየር መንገድ" ለመገንባት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ተወልደ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድን በአፍሪካ ትርፋማው የአየር ትራንስፖርት አቅራቢ በማድረግ ምስጋና የሚቸራቸው የአመራር ሰው ቢሆኑም፣ በኤር ኢንዲያ ቆይታቸው ከባድ ሥራ ይጠብቃቸዋል። የተረከቡት አየር መንገድ በተከታታይ የደኅንነት እና የሥራ ተግዳሮቶችን እያተስናገደ ነው።

የተከሰከሰ አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ባለፈው ዓመት ወደ ለንደር ሲበር የነበረ የኤር ኢንዲያ አውሮፕላን ተከስክሶ የ260 ሰዎች ሕይወት አልፏል

ባለፈው ዓመት ሰኔ ላይ ከሕንድ አህመዳባድ ወደ ለንደን ጉዞ ሲያደርግ የነበረው አውሮፕላኑ መከስከሱ ለአየር መንገዱ የእድገት ግስጋሴ መሰናክል ሆኗል። የአውሮፕላን አደጋው የመጨረሻ ሪፖርት የሚወጣው በመጪው ዓመት ጥቅምት ላይ ነው።

አየር መንገዱ ወደ የግል ይዞታነት ከተመለሰ ወዲህ የፋይንስ ችግሮች አጋጥመውታል። 2.3 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ኪሳራ እንዳስመዘገበ ባለፈው ወር አስታውቋል።

የኤር ኢንዲያ ሊቀመንበሩ ቻንድራሴካራን ይህንን የአየር መንገዱን ሁኔታ ለመቀየር እስከ አስር ዓመት ሊወስድ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል። በተጨማሪም አየር መንገዱ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑትን ዓለም አቀፍ በረራዎቹን አጥፏል።

ተቋሙ ያጋጠመው ኦፕሬሽናል ተግዳሮትም ኩባንያውን የዜና ርዕሰ ጉዳይ ያደረገ ሌላኛው ምክንያት ነው። መጋቢት ላይ ከዴልሂ ወደ ቫንኩቨር ይበር የነበረ አውሮፕላን ወደ ካናዳ የአየር ክልል ለመግባት ፈቃድ ባለማግኘቱ ምክንያት ለስምንት ሰዓታት ያህል ከበረረ በኋላ ለመመለስ ተገድዷል።

አየር መንገዱ እነዚህ ተግዳሮቶች ያጋጠሙት የሕንድ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ በዋጋ መናር፣ በኢራን ጦርነት በተፈጠረው የዓለም አቀፍ በረራዎች መስተጓጎል፣ በአውሮፕላኖች ማስረከቢያ ጊዜ እና ጥብቅ በሆነ የቁጥጥር አሰራር ምክንያት ጫና ውስጥ በወደቀበት ወቅት ነው።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአቪዬሽን ባለሙያዎች፣ ተወልደ ገብረማሪያም ምናልባትም ለ'ኤር ኢንዲያ' የሚያስፈልጉት መሪ ናቸው ብለዋል። ተወልደ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚነት ዘመናቸው ያጋጠሟቸውን ሁለት ቀውሶች ማለፋቸውንም በማሳያነት ይጠቅሳሉ።

በተርታ የቆሙ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላኖች

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Airlines

የምስሉ መግለጫ, ተወልደ ገብረማሪያም በኢትዮጵያ አየር መንገድ የሥልጣን ዘመናቸው የተቋሙት የአውሮፕላኖች ብዛት በሦስት እጥፍ ገደማ አሳድገዋል

የመጀመሪያው ቀውስ በመጋቢት 2011 ዓ. ም. ከአዲስ አበባ ወደ ኬንያ መዲና ናይሮቢ ሲበርር የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንድ 737 ማክስ አውሮፕላን ላይ ያጋጠመው የመከስከስ አደጋ ነው። በዚህ አደጋ 157 ሰዎች ሕይወታቸው እንዳለፈ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተወልደ መሪነት የተጋፈጠው ሌላኛው ፈተና የኮቪድ ወረርሽኝ ነው። አየር መንገዱ በወረርሽኙ ምክንያት የሰዎች ጉዞ ገበያው ቢቀዛቀዝበትም፣ ትኩረትን ወደ ካርጎ ጭነት በማዞር ትርፋማነቱን አስጠብቁ ወረርሽኙን አሳልፏል።

'አቪያላዝ ኮንሰልታንትስ' የኤቪዬሽን አማካሪ ተቋም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሳንጃይ ላዛር፣ "ተወልደ በሁለቱም መጥፎ አጋጣሚዎች ወቅት የሠራተኞችን ተወዳጅነት ማግኘት ችለዋል፤ በተለይም ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ፓይለቶች እና ኢንጂነሮች ጎን መቆማቸው [አስወድዷቸዋል]" ሲሉ ለቢቢሲ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ተወልደ ኤር ኢንዲያ የአመራርነት ዘመናቸው ቅድሚያ ከሚሰጧቸው ጉዳዮች መካከል፣ የተቋሙን የሥራ ባሕል መልሶ መገንባት እና የሠራተኞችን ሞራል ማነቃቃት እንደሚገኙበት ባለሙያዎች ያስረዳሉ። የዘገየውን የአውሮፕላኖች ማስፋፊያ እና እድሳት ማፋጠን እንዲሁም ኪሳራን ለመቀነስ ሲባል የአየር መንገዱን የበረራ ስርዓት መቀየርም ቅድሚያ ከሚሰጧቸው ጉዳዮች መካከል ተጠቅሰዋል።

የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተወልደ አዲሱን ኃላፊነታቸውን በይፋ የሚረከቡት መቼ እንደሆነ አልተገለጸም። ዝርዝር መረጃዎች በቅርቡ ይፋ ይሆናሉ ተብሏል።