ማንቸስተር ሲቲ የፋይናንስ ደንቦችን በመጣስ ጥፋተኛ ተባለ

ማንቸስተር ሲቲ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ማንቸስተር ሲቲ ጥሷቸዋል በሚል በተከሰሰባቸው 115 የፋይናንስ ክሶች በአብዛኛዎቹ ጥፋተኛ ተባለ።

'ዘ አትሌቲክ' እንደዘገበው፣ እስካሁን ቡድኑ ላይ ስለሚጣለው ማዕቀብ የተወሰነ ውሳኔ ባይኖርም፣ ገለልተኛ ኮሚቴ ግን ውሳኔውን አሳልፏል።

በዚህም መሠረት ማንቸስተር ሲቲ በክለቡ ላይ ከቀረቡት 115 ክሶች መካከል ከአንዱ በስተቀር በሁሉም ጥፋተኛ ሆኖ ተገኝቷል።

ፕሪሚየር ሊጉ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል። ሲቲም ዘገባው ትክክል ስለመሆኑ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም።

ይልቁንም "ፕሪሚየር ሊጉ ጉዳዩን አሁንም እየመረመረ ነው። አንዳንድ ወሳኝ ጉዳዮች ገና አልተጠናቀቁም ስለዚህ መረጃዎቹ ምስጢራዊነታቸው የተጠበቀ መሆን ይኖርበታል"

ፕሪሚየር ሊጉ ወገንተኝነት ሳያሳይ ፍትሃዊ እና ገለልተኛ ውሳኔ ይሰጣል ብሎ በማመን እና ሕጎቹን በመከተል ለስምንት ዓመታት በትዕግስት መጠበቁን ክለቡ በመግለጫው ላይ አስታውቋል።

ቢቢሲ ስፖርት ሲቲ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ ይግባኝ እንደሚል ተነግሮታል።

ሌሎች የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ገለልተኛ ኮሚቴው ስላሳለፈው ውሳኔ እንዲያውቁት እንደተደረገ የሚገመት ሲሆን ካሳ ለመጠየቅ የሚያስቡ ከሆነ የሕግ ምክር ሊጠይቁ ይችላሉ ተብሏል።

Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2023 የካቲት ወር በቡድኑ ላይ ለአራት ዓመታት የዘለቀ ምርመራ ከተደረገ በኋላ ከ100 በላይ የፕሪሚየር ሊጉን የፋይናንስ ደንቦች ጥሶ ተገኝቷል።

ቡድኑ እአአ ከ2009 እስከ 2018 ባለው ጊዜ ውስጥ የፋይናንስ ደንቦችን ጥሷል በሚል ተወንጅሎ፣ ጉዳዩ ለገለልተኛ ኮሚሽን ተላልፎ ተሰጥቶ ነበር።

የጉዳዩን ሂደት የሚመለከተው ችሎት በመስከረም 2024 በዝግ የተካሄደ ሲሆን፣ ለአስራ ሁለት ሳምንታት ያህል ከቆየ በኋላ በዚያው ዓመት ታኅሳስ ወር ላይ ተጠናቅቋል።

ፕሪሚየር ሊጉ፣ ክለቡ "ትክክለኛ እና ፍትሃዊ የሆነ የፋይናንስ ሁኔታን የሚያሳይ እውነተኛ መረጃ" የማቅረብ ግዴታን የሚደነግጉ ሕጎችን ሲቲ ጥሷል ሲል ከስሶታል።

ሲቲ ክሶቹን በሙሉ ያስተባበለ ሲሆን፣ ክርክሩ "ማስተባበያ በሌላቸው አጠቃላይ እና አሳማኝ ማስረጃዎች" የተደገፈ መሆኑን ገልጿል።

ሲቲ ላይ ምርመራ እየተደረገ በነበረበት ዓመታት ክለቡ ስምንት ዋንጫዎችን አሸንፏል፤ እነዚህም ሦስት የፕሪሚየር ሊግ፣ ሦስት የሊግ፣ አንድ የኮሚኒቲ ሺልድ እና አንድ የኤፍ ኤ ዋንጫ ናቸው።

ጉዳዩ ሮቤርቶ ማንቺኒ እና ማኑኤል ፔሌግሪኒ አሰልጣኝ በነበሩበት ወቅት እንዲሁም ፔፕ ጋርዲዮላ በክለቡ ያሳለፋቸውን የመጀመሪያዎቹን ሁለት ዓመታት ያካትታል። ጋርዲዮላ በክለቡ ለ10 የውድድር ዘመናት ከቆየ በኋላ፣ የ2025 – 26 የውድድር ዘመን ሲጠናቀቅ ክለቡን ለቅቋል።

ባለፈው ዓመት በሲቲ እና በፕሪሚየር ሊጉ መካከል ሌላ ክርክርም ተከፍቶ ነበር።

እ.ኤ.አ. በ2024፣ ማንቸስተር ሲቲ በተወሰኑ የፕሪሚየር ሊጉ ሕጎች ላይ ተቃውሞ ካቀረበ በኋላ፣ አንድ ገለልተኛ ኮሚቴ ከእነዚህ ሕጎች መካከል ከአጋር አካላት ጋር በሚደረጉ የንግድ ልውውጦች ላይ የተደነገጉትን አንዳንድ ክፍሎች ውድቅ አድርጓል።

እአአ በየካቲት 2025፣ አንድ የዳኝነት አካል በ2021 እና በ2024 መካከል በነበሩት የስፖንሰርሺፕ ስምምነቶች ላይ ፕሪሚየር ሊጉ ያወጣቸው ደንቦች ተፈጻሚ ሊሆኑ እንደማይችሉ አስታውቋል።

በመቀጠልም፣ በመስከረም 2025 ማንቸስተር ሲቲ እና ፕሪሚየር ሊጉ ስምምነት ላይ ደርሰዋል። ሲቲ የንግድ ልውውጦች ላይ የተቀመጡት ደንቦች ትክክለኛ እንደሆኑና መከበር እንዳለባቸው የተቀበለ ሲሆን፣ ሁለቱም ወገኖች የሕግ ክርክራቸውን ለማቆም ተስማምተዋል።

ሕጎቹ በፕሪሚየር ሊጉ የወጡት ክለቦች ከባለቤቶቻቸው ጋር ግንኙነት ካላቸው ኩባንያዎች ጋር በሚያደርጉት የንግድ ስምምነት፣ ከ"ፍትሃዊ የገበያ ዋጋ" በላይ ትርፍ እንዳያገኙ ለመከላከል ነው።