የአፍሪካ ቁጥር አንድ ባለሀብቱ አሊኮ ዳንጎቴ፣ ኢትዮጵያ እና ጂቡቲ በ660 ሚሊዮን ዶላር የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ ሊገነቡ ነው

የፎቶው ባለመብት, Bloomberg via Getty Images
ናይጄሪያዊው ቢሊየነር አሊኮ ዳንጎቴ ከኢትዮጵያ እና ጂቡቲ ጋር በመሆን ሁለቱን አገሮች የሚያገናኝ 660 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ እና ማከማቻ ፕሮጀክት ለመገንባት ከስምምነት ላይ ደረሱ።
ይህ ፕሮጀክት የጂቡቲን ዳመርጆግ ወደብ በኢትዮጵያ ደወሌ ከሚገኝ የነዳጅ ማከፋፈያ ማዕከል ጋር የሚያገናኝ 120 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የቧንቧ መስመር እንዲሁም 400 ሚሊዮን ሊትር ያህል የመያዝ አቅም ያለው ማከማቻን ያካትታል።
ይህ በመቶ ሚሊዮኖች ዶላር የሚወጣበት ፕሮጀክት በሚቀጥሉት 18 ወራት ውስጥ ሥራው እንደሚጀመር ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እንዳሉት፣ ይህ የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ ከጂቡቲ ወደብ ወደ ኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ ነዳጅ ለማጓጓዝ የሚወስደውን ጊዜ ከአምስት ቀናት ወደ አንድ ቀን ያሳጥረዋል።
የፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ የአውሮፕላን ነዳጅ፣ ናፍጣ እና ቤንዚንን ጨምሮ ዋና ዋና የፔትሮሊየም ምርቶችን ከጂቡቲ ወደ ኢትዮጵያ ያጓጉዛል።
መስከረም 14/2019 ዓ.ም. ጂቡቲ ውስጥ በተካሄደው በፕሮጀክቱ የመሠረት ድንጋይ የማኖር ሥነ ሥርዓት ላይ ቢሊየነሩ አሊኮ ዳንጎቴ እንደተናገሩት፣ ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያን የኃይል አቅርቦት ደኅንነት እንደሚያጠናክር እና የነዳጅ አቅርቦት ሥርዓቷን ይበልጥ ጠንካራ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
ወደብ የሌላት ኢትዮጵያ ነዳጅን ጨምሮ ለሚያስፈልጓት ገቢ ዕቃዎች በብዛት በጂቡቲ ወደብ ላይ ጥገኛ ናት። ግንባታው እንደሚጀመር የተገለጸው የነዳጅ ማከማቻ እና ማስተላለፊያ መሠረተ ልማት አሁን ባሉት የማጓጓዣ ሥርዓቶች ላይ ያለውን ጫና በመቀነስ ትራንስፖርት፣ አቪዬሽን፣ ግብርና እና ግንባታን ጨምሮ ለተለያዩ ዘርፎች ድጋፍ እንደሚያደርግ ይጠበቃል።
ጂቡቲም በወደብ እንቅስቃሴ መጨመር፣ የሥራ ዕድሎች መፈጠር እና የመንግሥት ገቢ ማደግ ተጠቃሚ እንደምትሆን ይጠበቃል።
ፕሮጀክቱ ዳንጎቴ በአፍሪካ ደረጃ እያስፋፋቸው ያሉ የመሠረተ ልማትና የምርት ንግዶች አካል ነው።
በኢትዮጵያም ግዙፍ የሲሚንቶ ፋብሪካ ያለው ሲሆን፣ በቅርቡም የተፈጥሮ ነዳጅ ማውጫ እና የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ጀምሯል።
ዳንጎቴ ሲሚንቶ በዓመት 55 ሚሊዮን ቶን የማምረት አቅም ሲኖረው፣ በናይጄሪያ የሚገኘው የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካው በቀን 700 ሺህ በርሜል ድፍድፍ ዘይት የማቀነባበር አቅም አለው፤ ይህንንም ወደ 1.4 ሚሊዮን በርሜል በቀን ለማሳደግ እየሠራ ነው።
ይህ የነዳጅ ዘይት ማጣሪያ ፋብሪካ በቅርቡ 4.1 ቢሊዮን አክሲዮኖችን በናይጄሪያ የአክሲዮን ገበያ በማስመዝገብ 1.63 ቢሊዮን ዶላር ለማሰባሰብ አቅዷል።
በኬንያም ኩባንያው በላሙ በቀን 700 ሺህ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ የማጣራት አቅም ያለው የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ በሚቀጥለው ሳምንት ያኖራል ተብሎ ይጠበቃል።


































