በትግራይ የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎት የተቋረጠው በህወሓት ትዕዛዝ መሆኑን ሮይተርስ ዘገበ

የሞባይል ስልክ ያያዘች ሴት
የምስሉ መግለጫ, ለሁለት ዓመት በተካሄደው ጦርነት ወቅት የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጦ ነበር
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የትግራይ ክልል አስተዳደርን ተቆጣጥረው ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ግጭት ውስጥ የገቡት የህወሓት አመራሮች በክልሉ ውስጥ ያለው የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲቋረጥ ማድረጋቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘገበ።

በቀድሞ የህወሓት አባላት የተቋቋመው እና በጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ የሚመራው ስምረት ፓርቲም ባወጣው መግለጫ የህወሓት መሪዎች አገልግሎቱን አቋርጠዋል በማለት ከስሷል።

በትግራይ የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎት የተቋረጠው በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መሪዎች መካከል የነበረው ውዝግብ ተባብሶ ባለፈው ረቡዕ ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ ነው።

የትግራይ ኃይሎች በክልሉ የሚገኙ ዋነኛዎቹን ሦስት አውሮፕላን ማረፊያዎች በመቆጣጠራቸው የአውሮፕላን በረራዎች ከተቋረጡ ሦስተኛ ቀናቸው ይዘዋል።

ቢቢሲ አርብ ጠዋት ያነጋገራቸው የሳፋሪኮም ተጠቃሚዎች እንደገለጹት በአገሪቱ እንዲሁም በትግራይ ክልል ሰፊ ተጠቃሚ ያለው ኢትዮቴሌኮም የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎት በክልሉ የተቋረጠው ሐሙስ ምሽት ነው።

በትግራይ ውስጥ ስለተከሰተው የአገልግሎት መቋረጥ በኢትዮጵያ ዋነኛው የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ከሆነው ኢትዮቴሌኮም ምላሽ ለማግኘት ቢቢሲ ለተቋሙ የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ እና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተደጋጋሚ ጥሪዎች እና የጽሑፍ መልዕክት ቢልክም ምላሽ አላገኘም።

ሮይተርስ አርብ ከሰዓት በኋላ አንድ የዲፕሎማሲ ምንጭን ጨምሮ፣ ጉዳዩን በቅርብ ያውቃሉ ያላቸው አራት ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው በትግራይ ውስጥ የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎቱ የተቋረጠው በህወሓት መሪዎች ውሳኔ መሆኑን አመልክቷል።

ካለፈው ዓመት ግንቦት ወር አንስቶ በፌደራል መንግሥቱ የተሾመውን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርን በማስወገድ ሥልጣን የያዙት የህወሓት ባለሥልጣናት ለመንግሥታዊው ኢትዮቴሌኮም እና የግል ኩባንያ ለሆነው ሳፋሪኮም በክልሉ ያለውን "የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎቶችን እንዲያቋርጡ ትዕዛዝ ሰጥተዋል" ብሏል ዘገባው።

Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ለወሳኝ የግንኙነት አገልግሎቶቹ መቋረጥ "የመንግሥት ኃይሎች ለጥቃት የሚያውሏቸውን ድሮኖች ለመጠቀም የሚያስችለውን የሞባይል ኔትወርክ ተደራሽነት ለማቀብ የተቀየሰ ስልት ሊሆን ይችላል" ሲሉ ከምንጮቹ አንዱ በምክንያትነት እንደነገሩት ሮይተርስ በዘገባው ጠቅሷል።

ስምረት ፓርቲ ባወጣው መግለጫም የህወሓት ቡድን "ከትናንት [ሐሙስ] ምሽት ጀምሮ በመላው ትግራይ የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲቋረጥ አድርጓል" በማለት ከስሷል።

ፓርቲው ጨምሮም ህወሓት በክልሉ ውስጥ የኢንተርኔት እና የስልክ አገልግሎትን ለማቋረጥ "ሲያሴር" እንደነበር እና መስከረም 14/2019 ዓ.ም. ምሽት አንስቶ አገልግሎቱ እንዲቋረጥ አድርጓል በማለት ወቅሷል።

ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ የህወሓት ባለሥልጣናትን አስተያየት ለማግኘት ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ ሙከራዎችን ቢያደርግም በአገልግሎት መቋረጥ ምክንያት አልተሳካለትም።

ከህወሓት ጋር ቅርብ የሆነ አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ ምንጭ ግን "ለስልክ እና ለኢንተርኔት አገልግሎቶቹ መቋረጥ ተጠያቂው ህወሓት ሳይሆን መንግሥት ነው" ሲል ከስሷል።

ምንጩ ይህን ቢሉም በመስከረም ወር መጀመሪያ ላይ ለዲፕሎማቶች የተጋራ እና ሮይተርስ የተመለከተው የስጋት ትንተና መጠቆሚያ ሰነድም ህወሓት በበርካታ የትግራይ ከተሞች ውስጥ የሚገኙ የኢትዮቴሌኮም ትራንስፎርመሮችን በመንቀል የቴሌኮም አገልግሎቶችን የማቋረጥ እርምጃ መውሰዱን አመልክቷል።

ኢትዮቴሌኮም ከአምስት ዓመት በፊት በተካሄደው ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነት በቢሊዮኖች የሚቆጠር ብር የሚያስወጡ መሠረተ ልማቶቹ እንደወደሙበት አሳውቆ ነበር። ከጦርነቱ በኋላ በክልሉ ውስጥ አገልግሎቱን ለመቀጠልም ከፍተኛ በጀት መድቦ ሲሠራ መቆየቱን ሲገልጽ እንደነበር ይታወሳል።