የአሜሪካ የኢሚግሬሽን ፖሊስ አባላት የኤሌክትሪክ ንዝረት ጓንት ሊቀርብላቸው ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ የኢሚግሬሽን እና ጉምሩክ ሕግ አስፈጻሚ (አይስ) ፖሊስ መኮንኖች ስምሪት ላይ በሚሆኑበት ወቅት የሚያደርጉት የኤሌክትሪክ ንዝረት የሚያደርስ ጓንት ሊቀርብላቸው ነው።
የሕግ አስፈጻሚ መስሪያ ቤቱ አይስ፣ 'ጄነሬትድ ሎው አውትፑት ቮልቴጅ ኢሚተር' የተባሉትን የኤሌክትሪክ ንዝረት የሚያደርሱ ጓንቶች ለመግዛት እስከ 20 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የማድረግ እቅድ እንዳለው የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደኅንነት መስሪያ ቤት ሰነድ አመልክቷል።
ጓንቶቹ እስከ 380 ቮልት የሚደርስ ኤሌክትሪክ የማስተላለፍ አቅም ያላቸው ሲሆን፣ ይህ የኃይል መጠን አሜሪካ ውስጥ መደበኛ ሶኬቶች ካላቸው አቅም በሦስት እጥፍ ገደማ ይበልጣል።
'አሜሪካን ሲቪል ሊበሪቲስ ዩኒየን' የተባለውን ተቋም ጨምሮ የተለያዩ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች ንዝረት የሚያስከትለው ጓንት ጥቅም ላይ መዋሉ እንዳሰጋቸው ገልጸዋል።
የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ስደተኞች ላይ የሚወስዳቸውን እርምጃዎች እያስፈጸመ ያለው አይስ፣ በሕግ ማስከበር ወቅት በሚከተላቸው ታክቲኮች ምክንያት በርካታ ወቀሳዎች ይነሱበታል። የአይስ መኮንኖች በወሰዷቸው እርምጃዎች ሰዎች በጥይት መገደላቸው ይታወሳል።
የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደኅንነት መስሪያ ቤት ለቢቢሲ በላከው መግለጫ "መኮንኖቻችን ወንጀለኛ ሕገ-ወጥ መጤዎችን ደኅንነቱ በተጠበቀ መንገድ በቁጥጥር ሥር እንዲያውሉ እና ከአገራችን እንዲያስወጡ የሚያስፈልጓቸው መሳሪያዎች እና ቁሳቁሶች ማሟላታቸውን ለማረጋገጥ አይስ በቋሚነት ግምገማ ያደርጋል" ብሏል።
ጓንቶቹን የሚያመርተው 'ኮምፕላየንት ቴክኖሎጂስ' የተባለው ኩባንያው ስለ ሽያጩ አስተያየት መስጠት እንደማይችል ለቢቢሲ ገልጿል። ጨረታ ሳይወጣ የተፈጸመው የግዢ ውል እስከ አርብ ባለው ጊዜ ውስጥ ይፋ ሊደረግ እንደሚችል የአገር ውስጥ ደህንነት መስሪያ ቤቱ አስታውቋል።
የጓንት መሣሪያው ኤሌክትሪክ ንዝረት የሚያስተላልፈው የሚገጠምለት ቁልፍ ሲነካ ነው። በአንድ ሴኮንድ እስከ 30 ንዝረቶችን ማተስላለፍ ይችላል። ጓንቶቹ የኤሌክትሪክ ንዝረቱ ጥቅም ላይ የዋለበትን ጊዜ የሚመዘግብ 'ማይክሮፕሮሰሰር' አላቸው።
ጓንቶቹ ጉዳት እንደማያደርሱ እና በርካታ ተቋማት እየተገለገሉባቸው መሆኑን አምራቹ ኮምፕላየንት ቴክኖሎጂስ ድረ ገጹ ላይ አስፍሯል።
ኩባንያው ድረ ገጽ ላይ የሰፈረው የአጠቃቀም መመሪያ አሌክትሪክ ንዝረቱ አዛውንቶች፣ ትንንሽ ልጆች፣ ነፍሰ ጡር ሴቶች እንዲሁም "ከባድ አካል ጉዳት" ያለባቸው ሰዎች ላይ መሰንዘር እንደሌለበት ያስረዳል። ጓንቱ ጥቅም ላይ በሚውልበት ወቅት ንዝረቱ የሚደረግበትን ሰው ለመቆጣጠር ሌላ መኮንን ስፍራው ላይ መኖር እንዳለበትም ተጠቅሷል።
ብዙውን ጊዜ በፖሊስ አባላት ጥቅም ላይ የሚውለው 'ቲዘር' የተባለው መሣሪያ ተወርውረው ቆዳ ውስጥ በሚገቡ ስለታማ ነገሮች አማካኝነት እስከ 50,000 ቮልት ንዝረት ያደርሳል። የአሁኑ ጓንት ከዚህ መሣሪያ በተለየ መልኩ የኤሌክትሪክ ንረዝቱ ሰውነት ውስጥ ኡደቱን እንዲጨርስ አያደርግም።

የፎቶው ባለመብት, Compliant Technologies
ጓንቱ "ሕመም" በመፍጠር ግለሰቡ እንቅስቃሴውን እንዲገታ በሚያደርግ መልኩ ስል ንዝረት እንደሚያደርስ በቴነሲ ግዛት የሚገኘው የሆኪንስ ካውንቲ ማረሚያ ቤት አስተዳዳሪ ሌትናንት ባች ጋሊዮን ተናግረዋል።
ንዝረቱ የሚፈጠረው ጓንቱ ቆዳን ሲነካ ብቻ ነው። በዚህም የተነሳ መኮንኖች ከግለሰቡ ጋር ትግል ውስጥ ከገቡ መጀመሪያ የግለሰቡን ልብስ፣ ቀጥሎም ቆዳውን መንካት ይኖርባቸዋል። ብዙውን ጊዜ የእጅ አንጓ ወይም ክንድ ላይ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል።
የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደኅንነት መስሪያ ቤት እንደሚገልጸው፣ መኮንኖች የኤሌክትሪን ንዝረት ጓንቱን የሚጠቀሙት ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ድርጅቶችን የሚመረምረው የአገር ውስጥ የደኅነንት ምርመራ ክፍል በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ላይ ነው።
የኢሚግሬሽን ሕጎችን የሚጥሱ ሰዎችን በቁጥጥር ሥር የማዋል፣ የማሰር እና የማባረር ኃላፊነት ያለበት የሕግ ማስከበር እና ማባረር ስራዎች ክፍልም በሚሰማራበት ወቅት ጓንቱ ጥቅም ላይ እንደሚውል ተገልጿል።














