በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ ሰባት ታጣቂ ቡድኖች ፀረ መንግሥት ጥምረት መመስረታቸውን አስታወቁ

የፎቶው ባለመብት, Facebook
ሰባት ታጣቂ ቡድኖችን ያካተተ "ትብብር ለኅልውና" የተሰኘ ጥምረት መመስረቱን የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ዘመነ ካሴ በትግራይ መገናኛ ብዙኃን ቀርበው ተናገሩ።
አቶ ዘመነ ካሴ ትናንት መስከረም 10/2019 ዓ.ም. አመሻሽ ላይ በትግራይ መገናኛ ብዙኀን ላይ ባነበቡት መግለጫ መሠረት ትብብሩ ህወሓትን፣ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን እና የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄን ጨምሮ ሰባት ታጣቂ ቡድኖችን ያካተተ ነው።
አቶ ዘመነ ካሴ የትብብሩ ሰብሳቢ መሆናቸውም በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።
የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን) ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ዘመነ በትግራይ ቴሌቭዥን በሰጡት መግለጫ የብልጽግና አገዛዝ ከተወገደ በኋላ "አካታች የሽግግር መንግሥት" እንደሚመሰረት ተናግረዋል።
ይፋ በሆነው ትብብር አፋብን፣ ህወሓት፣ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ፣ የጉሙዝ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣ የቤንሻንጉል ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ፣ የኦጋዴን ሕዝብ ነፃነት ግንባርና የአፋር ብሄራዊ አንድነት ግንባር አባላት መሆናቸው ተነግሯል።
አቶ ዘመነ በመግለጫቸው ትብብሩ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን መንግሥት ለመጣል እና "በሽግግር ቻርተር የሚመራ አካታች የሽግግር መንግሥት" ለመመስረት ዓላማ እንዳለውም አስረድተዋል።
ትብብር ለኅልውናን በሰብሳቢነት የሚመሩት አቶ ዘመነ ካሴ "አዲስ የሽግግር ምዕራፍ" ሲሉ በመግለጫቸው የጠሩት ይህ ሂደት፤ የሁሉንም ኢትዮጵያውያን ሰብዓዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች "ሳይሸራረፉ እንዲረጋግጡ የሚያስችል" እንደሆነም አስታውቀዋል።
ይህ "አዲስ ምዕራፍ" የሚከፈተው፤ አሁን በሥልጣን ላይ ያለውን እና በገዢው ብልጽግና ፓርቲ የሚመራውን ስርዓት "በማስወገድ" መሆኑንም አቶ ዘመነ በመግለጫቸው ጠቅሰዋል።
ትብብር መፍጠራቸውን የገለጹት ታጣቂ ቡድኖች ሁለተኛ ዋነኛ ዓላማቸው "የሽግግር ምዕራፍ" መክፈት እንደሆነ በመግለጫው ላይ ተገልጿል።
ከብዙ ጥረት እና ውጣ ውረድ በኋላ እንደተመሰረተ የተገለጸው ይህ ትብብር "የሕዝቦችን ኅልውና እና የአገርን ደኅንነት መታደግ" ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑ በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።
ትብብሩ የብልጽግናን መንግሥት በማስወገድ ቅድሚያ ሰጥቼ እሰራቸዋለሁ ካላቸው ጉዳዮች መካከል በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እየተካሄዱ ያሉ "ሁሉንም ጦርነቶችን ማስቆም"፣ "ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ማረጋገጥ" እና "ሰላምንና ጸጥታን ማስጠበቅ" ይገኙበታል።
"ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስን ማረጋጋት፣ ከጎረቤት አገር ጋር ያለውን ግንኙነት ማሻሻል እና የአገሪቱን ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ቁመና ማስተካከል" የሚሉትም በመጀመሪያው ዋነኛ ዓላማቸው ሥር ተካትተዋል።
ትብብር ለኅልውና በሁለተኛ ዋና ዓላማነት በመግለጫው የጠቀሰው ጉዳይ፤ "ሕዝባዊ እና ሕገ መንግስታዊ ውይይት" ማድረግን ነው።
ለኢትዮጵያ "ሰላም" እና "ለሕዝቦች ቀጣይ ኅልውና" ሲባል እንደሚደረግ የተገለጸው ይህ ውይይት፤ "ሀቀኛ፣ ታማኝ፣ ሁሉንም ያካተተ እና ያሳተፈ" እንደሚሆን በመግለጫው ላይ ተመልክቷል።
የውይይቱ ዓላማም "ወሳኝ ሕዝባዊ እና አገራዊ ጥያቄዎችን በሕዝቦች ቀጥተኛ ተሳትፎ መመለስ" እንደሆነም አቶ ዘመነ በመግለጫቸው አብራርተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Screengrab
የትብብሩ መመስረት ይፋ የተደረገው የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) አመራሮች ከኤርትራ ጋር "ጽምዶ" መመስረታቸው ይፋ ከተደረገ ከወራት በኋላ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሐምሌ ወር ለፓርላማ አባላት ኢትዮጵያ "የመከላከል አቅም" ላይ እንደሚተማመኑ ተናግረው ነበር።
"ሌሎች ቢጨመሩም እንኳ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ የሚሰማን ፍርሃት የለም" ሲሉ ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም አቶ ዘመነ ካሴ የሚመሩት የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን) እንቅስቃሴው "በአማራ ክልል ብቻ የተወሰነ እንዳልሆነ" ለቢቢሲ ገልጾ ነበር።
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በበኩሉ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ዕለት በሰጠው መግለጫ የፋኖ አመራሮች በኦሮሚያ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ እና ራሳቸውን ፋኖ ብለው ከሚጠሩ አካላት እንዲያርቁ ጠይቋል።
ሠራዊቱ በመግለጫው "ከእንደዚህ ዓይነት ቡድን ጋር በመተባበር፣ ሊገኝ ከሚችለው የአጭር ጊዜ ወታደራዊ ጥቅም እጅግ የላቀ የፖለቲካ ዋጋ ሊያስከፍል የሚችል አደጋ" እንዳለው ገልጾ፣ የአማራ ኃይሎች ይህን ቡድን በተመለከተ የሚያደርጉትን "ኃላፊነት ከጎደለው የሚዲያ ንግግሮች እንዲታቀቡ እና ከዚህ ቡድን ጋር ያላቸውን ግንኙንት በግልጽ እንዲያቋርጡ" ጠይቆ ነበር።
የቀድሞ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ አቶ ጌታቸው ረዳ ደግሞ ለፐልስ አፍሪካ በሰጡት ቃለ ምልልስ እንደ ፋኖ፣ ኦነግ ሸኔ እና ህወሓት ያሉ አካላት የኤርትራን ዓላማ ለማሳካት እና የጦርነቱን ሸክም እንዲሸከሙ ተሰልፈዋል ሲሉ ከስሰዋል።
አቶ ጌታቸው ለመገናኛ ብዙኃኑ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ የኤርትራ መንግሥት ከግብፅ ጋር በመሆን የምሥራቅ አፍሪካን ሰላም ለማናጋት እና ቀጣናውን ለማተራመስ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
ህወሓት እና የኤርትራ መንግሥት አብረው መሠለፋቸው እጅግ አደገኛና የትግራይንና የአማራን ሕዝብ ለከፋ ሁኔታ የሚዳርግ መሆኑን አቶ ጌታቸው ጨምረው አስረድተዋል።
የፌደራል መንግሥቱ በትናንትናው ዕለት መመስረቱን ይፋ ያደረገውን ትብብር ለኅልውና በሚመለከት እስካሁን ያለው ነገር የለም።















