በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም ስለተቀሰቀሰው ግጭት እስካሁን የምናውቀው

ታንክ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

የትግራይ የእርስ በርስ ጦርነት በፕሪቶርያ ስምምነት ከተገታ ወዲህ ከረቡዕ መስከረም 13 አንስቶ ግጭት በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግመኛ ተቀስቅሷል።

ረቡዕ ዕለት ግጭቱ ስለ መጀመሩ ይፋዊ መረጃ ቢወጣም ማክሰኞ ዕለት በትግራይ አላማጣ ከተማ ተከታታይ የድሮን እና የአውሮፕላን ጥቃቶች መፈጸማቸው ተዘግቧል።

ከዚህ አስቀድሞ ደግሞ መስከረም 10/2019 ዓ.ም. አመሻሽ ላይ ሰባት ታጣቂ ቡድኖችን "ትብብር ለኅልውና" የተሰኘ ጥምረት መመሥረታቸውን ይፋ አድርገዋል።

የጥምረቱ መመሥረት ይፋ ከመደረጉ በፊትም የህወሓት መሪዎች የፌደራል መንግሥቱን "የመጣል ዓላማ" እንዳላቸው ሲገልጹ የነበሩ ሲሆን፤ ባለፉት ወራትም የፌደራል መንግሥቱ የትግራይ ኃይሎችን ዒላማ ያደረጉ ተደጋጋሚ የድሮን ጥቃቶችን ሲፈጽም ቆይቷል።

እየተባባሰ የመጣው ውጥረት ረቡዕ ወደለየለት ግጭት ተሻግሮ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ውጊያዎች መካሄዳቸው ተዘግቧል።

ባለፉት ቀናት የተፈጠሩ ዋና ዋና ክስተቶች የሚከተሉት ናቸው።

የጥምረቱ መመሥረት

መስከረም 10/2019 ዓ.ም. አመሻሽ ላይ የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን) ሊቀ መንበር ዘመነ ካሴ "ትብብር ለኅልውና" የተሰኘ ጥምረት መመሥረቱን በትግራይ መገናኛ ብዙኃን ላይ ባነበቡት መግለጫ አስታውቀዋል።

ህወሓት፣ የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን) እና የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊትን (ኦነሠ) ጨምሮ ሰባት ታጣቂ ቡድኖች የተጣመሩበት ቡድን፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን አስተዳደር ጥሎ "የሽግግር መንግሥት" የመመሥረት ዓላማ እንዳለው ይፋ አድርጓል።

ትብብር ለኅልውናን በሰብሳቢነት የሚመሩት ዘመነ "አዲስ የሽግግር ምዕራፍ" ሲል የጠቀሰው ይህ ሒደት፤ የሁሉንም ኢትዮጵያውያን ሰብዓዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች "ሳይሸራረፉ እንዲረጋግጡ የሚያስችል" እንደሆነ አስታውቀዋል።

ይህ "አዲስ ምዕራፍ" የሚከፈተው፤ አሁን በሥልጣን ላይ ያለውን እና በገዢው ብልጽግና ፓርቲ የሚመራውን ሥርዓት "በማስወገድ" መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የጥምረቱን ይፋ መሆን ተከትሎ የተለያዩ ወገኖች ድጋፍ እና ተቃውሞ ሲያሰሙ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ቃል አቀባይ ቢለኔ ስዩም ቡድኖቹ ከኤርትራ ድጋፍ የሚያገኙ መሆናቸውን እና ይፋ መሆኑ የኢትዮጵያ መንግሥት ሲል የነበረውን የሚያረጋግጥ ነው ሲሉ ለሮይተርስ ገልጸዋል።

ድሮን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአላማጣ የድሮን ጥቃት

ባለፉት ወራት የትግራይ ኃይሎችን ዒላማ ያደረጉ የድሮን ጥቃቶች በፌደራል መንግሥቱ ሲፈጸሙ ቆይተዋል። በእርግጥ ከክልሉ አስተዳደር የቀረቡ ክሶችን በተመለከተ ከፌደራል መንግሥቱ የተባለ ነገር የለም።

የፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ አመራሮች መካረራቸው ሲባባስ ከተፈጸሙ የድሮን ጥቃቶች መካከል ነሐሴ 14/2018 ዓ. ም. በመቀለ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች የደረሰው ጥቃት ይጠቀሳል።

የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ በተፈጸመው ድሮን ጥቃት ከ13 ሰዎች በላይ ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጾ፣ ለጥቃቱ የፌደራል መንግሥቱን ተጠያቂ አድርጓል።

ሌላው የድሮን ጥቃት ነሐሴ 4/2018 ዓ. ም. በትግራይ ክልል ራያ አላማጣ ወረዳ "መረዋ" የተባለ ቀበሌ ላይ የተፈጸመ ሲሆን፤ የሰዎች ሕይወት ማለፉን የአካባቢው ባለሥልጣን እና የትግራይ ኃይሎች ምንጮች ገልጸዋል።

በያዝነው ሳምንት ደግሞ ማክሰኞ መስከረም 12/2019 ዓ. ም. በትግራይ አላማጣ ከተማ አካባቢ በተፈጸሙ ተከታታይ የድሮን እና የአውሮፕላን ጥቃቶች ቢያንስ 14 ሰዎች መገደላቸውን እና ሌሎች በርካቶች መቁሰላቸውን የከተማዋ ከንቲባ አቶ ሞገስ ሽፈራው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከንቲባው አቶ ሞገስ በጥቃቱ "የተገደሉት በሙሉ ሰላማዊ ሰዎች" መሆናቸውን እንዲሁም በታጣቂም ሆነ በጦር መሣሪያ ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ቢቢሲ ትግርኛ ያነጋገራቸው ሦስት የአካባቢው ነዋሪዎች ከተጎጂዎች መካከል በርካታ ታጣቂዎች መመልከታቸው አስረድተዋል።

አሉላ አባ ነጋ አውሮፕላን ማረፊያ

የፎቶው ባለመብት, Geez media

አውሮፕላን ማረፊያ መቆጣጠር

የትግራይ ኃይሎች በክልሉ ዋና ከተማ መቀለ የሚገኘውን አሉላ አባ ነጋ አውሮፕላን ማረፊያን መቆጣጠራቸው የተሰማው ረቡዕ ማለዳ ነው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድም በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ በትግራይ ክልል የሚያደርገውን በረራ "ለጊዜው መቋረጡን" አስታውቋል።

አየር መንገዱ በረራውን ያቋረጠው በክልሉ "ባለው ወቅታዊ ሁኔታ" ምክንያት ከመግለጽ ውጪ በረራውን ለማቋረጥ ያስገደዱትን ምክንያቶች በመግለጫው ላይ አልጠቀሰም።

የቢቢሲ ምንጮችም ወደ መቀለ፣ አክሱም እና ሽሬ ከተሞች የሚደረጉ በረራዎች በሙሉ መሰረዛቸውን ተናግረዋል።

አየር መንገዱም በመግለጫው ላይ በእነዚህ ሦስት ከተሞች የሚደረጉ በረራዎችን መሰረዛቸውን ሲያስታውቅ፣ በረራዎቹ መቼ መልሰው እንደሚጀመሩ ግን አልገለጸም።

የትግራይ ኃይሎች የአውሮፕላን ማረፊያዎቹን የተቆጣጠሩት ተቋማቱን የሚጠብቁ የፌደራል መንግሥቱ ኃይሎችን በቁጥጥራቸው ስር አስገብተው መሆኑ ተዘግቧል።

ውጊያ የተካሄደባቸው አካባቢዎች

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ እና እና የቀድሞው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ፤ የህወሓት ኃይሎች በአፋር እና በአማራ ክልሎች በሚገኙ ቦታዎች በኩል "ሙሉ ጥቃት መክፈታቸውን" ገልጸዋል።

የህወሓት መሪዎች በበኩላቸው የመንግሥት ኃይሎች ቀደም ብለው ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ ኃይሎቻቸው "ወደ መከላከል ውጊያ" መግባታቸውን አስታውቀዋል።

የአፋር ክልል ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ረቡዕ በፌስቡክ ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ ህወሓት "ከዛሬ [ማከስኞ] ሌሊት ጀምሮ በአፋር ክልል ኪልበቲ ረሱ ዞን በአብአላ፣ በመጋሌ፣ በወሰማና በሌሎች አካባቢዎች" ላይ ጦርነት "መክፈቱን" ገልጿል።

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ኃይሎች ትብብር ለሕልውና የተባለው ጥምረት በበኩሉ አባል ድርጅቶቹ "በተለይ በሰሜን ወሎ፣ በዋግ ህምራ፣ በአፋር ክልል ሰሜናዊ ቀጠናዎች" ላይ "ፀረ ማጥቃት" እያደረጉ እንደሆነ ባወጣው መግለጫው አስታውቋል።

በትግራይ እና በፌደራል መንግሥቱ በኩል ምን ተባለ?

በፌደራል መንግሥቱ በኩል በይፋ ስለ ግጭቱ የተባለ ነገር ባይኖርም የፌደራል መንግሥቱ ከፍተኛ ባለሥልጣን አቶ ጌታቸው፤ አክለውም የህወሓት ኃይሎች በአፋር እና በአማራ ክልሎች በሚገኙ ቦታዎች በኩል ሙሉ ጥቃት መክፈታቸውን በመግለጽ ጦርነት መቀስቀሱ "እጅግ የሚያሳዝን" ክስተት ነው ብለዋል።

አቶ ጌታቸው "የህወሓት የፖለቲካ እና የወታደራዊ አመራር ኃላፊነት የጎደለው አካሄድ ወደ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገሩን" ሲሉም አክለዋል።

በኒው ዮርክ በተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ንግግር ያደረጉት ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ፤ ኢትዮጵያ "የውጭ ጣልቃ ገብነቶች" ቢኖሩም እንኳን "በከፍተኛ ሁኔታ ተቆጥባ" እንደቆየች እና ከጎረቤት አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት "እንዳሻሻለች" ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ቀጣናዊ ትስስሯን በማጠናከር እና በሱዳን ሰላም እንዲሰፍን የሚደረጉ ጥረቶችን ብትደግፍም "የውጭ ኃይሎች ጣልቃ እየገቡ" እንደሆነ ጠቁመዋል።

"ለአጥፊ እና አውዳሚ ኃይሎች የምናስተላልፈው መልዕክት ግልጽ ነው። በአፍሪካ ቀንድ ሰዎች በሰላም እና በብልጽግና የመኖር መብታቸውን እንዲያከብሩ እናሳስባለን" ሲሉም አክለዋል።

ትግራይን የሚያስተዳድሩት የህወሓት መሪዎች በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት "ተከፈተብን" ያሉትን ጥቃት ለመከላከል ኃይሎቻቸው "እርምጃ እንዲወስዱ መታዘዛቸውን" ገልጸዋል።

ከህወሓት ጋር የተጣመሩት ሰባት ታጣቂ ቡድኖች ባወጡት መግለጫ "በአየር እና በምድር መጠነ ሰፊ ጥቃቶች" እንደተከፈቱ ብለዋል።

"የብልጽግና አገዛዝ" ከፍቶታል ካለው ጥቃት በተጨማሪ "በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ የሕዝብ አገልግሎቶችንም ጭምር አቋርጧል" ሲልም ጥምረቱ ከስሷል።

አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ

የፎቶው ባለመብት, US EMBASSY AA/FB

የምስሉ መግለጫ, በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ

አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት ምን አሉ?

Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ማሕሙድ አሊ ዩሱፍ በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው ውጥረት እና ወታደራዊ መካረር "እጅግ እንዳሳሰባቸው" ገልጸው፤ ግጭቱ "በአፋጣኝ እንዲቆምም" አሳስበዋል።

ትናንት ማምሻውን ባወጡት መግለጫ፤ የመቀለ፣ የአክሱም እና ሽረ አውሮፕላን ማረፊያዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው፣ ህወሓት የፌደራል መንግሥት ሠራተኞችን መያዙ እና የሕዝብ አገልግሎት መስጫዎች መቋረጣቸው እንዳሰጋቸው አስታውቀዋል።

ሊቀ መንበሩ በደቡብ ትግራይ እና በአፋር ክልል ግጭት እየተባባሰ መምጣቱ እንዳሳሰባቸው ጠቅሰው፤ አያይዘውም በቅርቡ በታጣቂ ኃይሎች የተፈጠረው ጥምረት "አለመረጋጋቱን እንደሚያባብስ" ገልጸዋል።

በፕሪቶርያ ስምምነት መሠረት "ሳይዘገይ ወደ ቀጥተኛ ንግግር" መመለስ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ አጎራባች አገራት ግጭቱን ከሚያባብሱ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ አሳስበው፤ "ግጭቱ እንዲቆም እና ንግግር እንዲደረግ" ሚናቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ በበኩላቸው የህወሓት አመራሮችን "መጠነ ሰፊ ጥቃት በመክፈት" ከስሰዋል።

የህወሓት አመራሮች በአፍሪካ ኅብረት ልዑክ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ አማካኝነት የሚካሄደው ንግግር ውድቅ አድርገው "በማያሸንፉት ጦርነት ውስጥ መግባት ለሕዝቡ ምንም የሚፈይደው ነገር የለም" በማለትም ወቅሰዋል።

አምባሳደሩ ትናንት ማምሻውን በወጣው መግለጫቸው "ሌሎች ታጣቂ ቡድኖች በዚህ ጦርነት ውስጥ ባለመግባት ብልህ እንዲሆኑ" አሳስበዋል።

አሜሪካ ኢትዮጵያን ወደተሳሳተ መንገድ ለመምራት የሚሞክሩ ተጨማሪ አመራሮች ላይ ማዕቀብ ለመጣል አማራጩ እንዳላት አመልክተዋል።

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ማሕሙድ አሊ ዩሱፍ እና በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ መግለጫ ማውጣታቸውን ተከትሎ፤ የህወሓት ከፍተኛ አመራር እና የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አማኑኤል አሰፋ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ በሰጡት ምላሽ በመግለጫዎቹ "ማዘናቸውን" ገልጸዋል።

አቶ አማኑኤል፤ የአሜሪካ አምባሳደር እንዲሁም የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽነር በትግራይ ውስጥ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት ያደረሱ የአየር ጥቃቶች ሲፈጸሙ በዝምታ ቆይተው አሁን የሰነዘሩት ወቀሳ "ፍትሐዊ አይደለም" ብለዋል።

የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ውጥረት መባባሱ "እጅግ እንዳሳሰበው" ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ሁሉም ወገኖች "ግጭቱን እንዲያቆሙ እንዲሁም ውጥረቱን ከሚያባብሱ፣ የንጹኃንን ሕይወት ለአደጋ ከሚያጋልጡ እና የሰላም ጥረትን ከሚያሰናክሉ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ" ጠይቋል።

የፕሪቶሪያ ስምምነት "ችግሮችን ለመፍታት እንዲውል" እና በስምምነቱ የተቀመጡት ግዴታዎች "ሙሉ በሙሉ እንዲከበሩ" ኢጋድ በመግለጫው አሳስቧል።

የአውሮፓ ኅብረትም ዛሬ ባወጣው መግለጫ በሰሜን ኢትዮጵያ በፍጥነት እየተባባሰ ያለው ሁኔታ እና ይህ ሁኔታ በሕዝቡ ላይ እያሳደረ ያለው ተጽዕኖ በጥልቅ እንደሚያሳስበው አስታውቋል።

"ውጥረቱን በአስቸኳይ ማርገብ ያስፈልጋል" ያለው የአውሮፓ ኅብረት፣ ሁለቱም አካላት ግጭትን በዘላቂነት ለማቆም ለተደረሰው ስምምነት ዳግም ቁርጠኝነታቸውን እንዲያሳዩ ጠይቋል። ለዚህም "ጊዜው አልረፈደም" ብሏል።

ልዩነቶች ሊፈቱ የሚችሉት በውይይት ብቻ እንጂ በወታደራዊ እርምጃ እንዳልሆነም ገልጿል።