አሜሪካ ስለ 'ዩፎዎች' ታይተው የማይታወቁ አዳዲስ መረጃዎች ይፋ አደረገች

እንግዳ የሆኑ አካላት በመካከለኛው ምሥራቅ መኖሪያ ሰፈር አካባቢ ሲያንዣብቡ በቪድዮ ይታያል

የፎቶው ባለመብት, fair use

የምስሉ መግለጫ, እንግዳ የሆኑ አካላት በመካከለኛው ምሥራቅ መኖሪያ ሰፈር አካባቢ ሲያንዣብቡ በቪድዮ ይታያል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የአሜሪካ መከላከያ መስሪያ ቤት 'ፔንታገን' ምንነታቸው ያልታወቁ በራሪ አካላት (ዩፎዎች) በተመለከተ አዳዲስ መረጃዎች ይፋ አደረገ።

እነዚህ መረጃዎች ከዚህ ቀደም ያልታዩ ቪድዮዎች፣ ምሥሎች እና ሰነዶች ናቸው።

በአንድ ቪዲዮ ላይ እንግዳ የሆኑ አካላት በመካከለኛው ምሥራቅ መኖሪያ ሰፈር አካባቢ ሲያንዣብቡ ይታያል።

ሌላኛው ቪድዮ ጥቁር እና ድቡልቡል የሆነ ቁስ በፓስፊክ ውቅያኖስ ላይ አንዣቦ ሲሰወር ያሳያል።

ፔንታገን በለቀቃቸው 41 አዲስ ሰነዶች ውስጥ በርካታ የፒዲኤፍ ሰነዶችም ይገኛሉ።

ከሰነዶቹ መካከል ቀደምት የሆነው በአውሮፓውያኑ 1953 የተሰነደው ነው። የቅርብ ጊዜው ሰነድ ደግሞ አምና የተገኘ እንደሆነ ተገልጿል።

የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ያለፈው ግንቦት 8 ላይ 161 ሰነዶች ይፋ ካደረገ በኋላ ተጨማሪ መረጃ እንደሚለቀቅ አስታውቆ ነበር።

ፕሬዝዳንት ዶናድል ትራምፕ በዚህ ዓመት ሰነዶቹ ይፋ እንዲደረጉ ባስተላለፉት ትዕዛዝ መሠረት ፔንታገን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰነዶችን በአምስት ክፍል አውጥቷል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከቪድዮቹ አንደኛው በአውሮፓውያኑ 2021 በኦማን ባሕረ ሰላጤ የተቀረጸ ነው።

ጥቁር የሆነ እንግዳ አካል ባልተለመደ መንገድ ሲንቀሳቀስ ይታያል። መጀመሪያ ላይ ሲታይ እንደ ዝንብ ይመስላል። 1.2 ሜትር ስፋት አለው።

ምንነቱ ያልታወቀ ኢመደበኛ ክስተት (አንአይደንቲፋይድ አኖማሎውስ ፌኖሚና - ዩኤፒ) መሆኑ ሪፖርት ተደርጓል።

ዩኤፒ የሚለውን ስያሜ የአሜሪካ መንግሥት እና ሳይንቲስቶች ምንነታቸው በውል ያልታወቁ አካላትን ለመግለጽ ይጠቀሙበታል።እነዚህ አካላት በባሕር፣ በየብስ እና በአየር ላይ ሊገኙ ይችላሉ።

በ2025 የአሜሪካ ወታደራዊ ካሜራ ትክክለኛ ቦታው ባልታወቀ የመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ የቀረጸው ቪድዮ በአንድ መኖሪያ ሰፈር ክብ የሆነ አካል በቀጥታ መስመር ሲጓዝ ያሳያል።

ኤፍቢአይ ይፋ ያደረገው አንድ ሰነድ እንደሚያሳየው ጥቅምት 2023 ላይ በቦስተን እና ደብሊን መካከል በረራ ሲካሄድ ፓይለቱ ሰማይ ላይ ብርሃን መመልከቱን ሪፖርት አድርጓል።

ሌሎች ፓይለቶችም ከእኩለ ሌሊት በኋላ ተመሳሳይ ብርሃን አይተው ሊሆን እንደሚችልም ገልጿል።

ፓይለቱ እንደተናገረው፤ ነጩ ብርሃን መጀመሪያ ላይ እንደ ጭላንጭል ይጀምር እና ቆየት እያለ እየደመቀ ይሄዳል፤ ከዚያም ይከስማል። አንዳንዶቹ የብርሃን ፍንጣቂዎች ባሉበት ሲቆሙ፤ አንዳንዶቹ በቀጥታ መስመር፣ ሌሎቹ ደግሞ አቅጣጫ እየለዋወጡ ይጓዛሉ።

እነዚህን የብርሃን ፍንጣቂዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የተመለከተው በ2023 እንደሆነ እና ከዚያ በኋላም ቢያንስ 10 ጊዜ እንዳያቸው ይናገራል።

በ2019 በፓስፊክ ባሕር ላይ የተቀረጸው ቪድዮ ጥቁር፣ ክብ እንግዳ አካል ታይቶ ሲጠፋ ያሳያል። በድጋሚ ከታየ በኋላ ተንቀጥቅጦ በዝግታ ከግራ ወደ ቀኝ ይጓዛል።

ቪድዮው የተቀረጸው በእጅ በተያዘ ካሜራ ስለነበር ምናልባት የእንግዳ አካሉ ሲንቀጠቀጥ የሚታየው በቀረጻው ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ተጠቅሷል።

በ1953 በተዘጋጀ የፒዲኤፍ ሰነድ ላይ የአሜሪካ ባሕር ኃይል የምሥል ትንታኔ ክፍል ስለ ሁለት ቪድዮዎች የሰጠው ትንታኔ ተካትቷል።

በምዕራባዊ የአሜሪካ ክፍል፤ ዩታ እና ሞንታና በ1950 እና 1952 የተቀረጹት ቪድዮዎች እንግዳ አካላት የብርሃን መጠናቸው ሲጨምር ግዝፈታቸውም አብሮ ከፍ ሲል ያሳያሉ።

እነዚህ አካላት "በተፈጥሮ ከሚታወቁ ቁሶች" ጋር ተመሳሳይ ያልሆነ ባህሪ እንደሚያሳዩ ተገልጿል።

ፔንታገን ይፋ ያደረገው አንድ ምሥል ትልቅ፣ ሦስት መዓዘን ያለው አካል በክብ ቅርጽ በሚታይ ብርሃን ተከብቦ ያሳያል። ብርሃኑ በማዕዘኑ ሦስት ቅርጾች በኩል ይስተዋላል።

ይህንንም የተመለከቱት ሁለት የቀድሞ የአሜሪካ ወታደሮች በ2011 ነው።

በአሜሪካውያን ዘንድ ስለ ዩፎዎች የማወቅ ጉጉት በቅርብ ዓመታት ውስጥ ጨምሯል።

በ2022 የአሜሪካ ምክር ቤት ከአምስት አሥርታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ ዩፎዎች ውይይት አድርጓል።

የአገሪቱ ጦር የዩፎዎችን ጉዳይ በምሥጢር መያዝ ቀርቶ ግልጽነት እንዲሰፍን እንደሚፈልግም አስታውቋል።

የፔንታገን ቃል አቀባይ ሻን ፓርኔል እንዳሉት በቀጣይም ተጨማሪ መረጃዎች ይለቀቃሉ።