በጦርነቱ ተጎድተው በኮረም፣ አላማጣ እና ሽረ ሆስፒታሎች የታከሙ ሰዎች ቁጥር 720 እንደሚደርስ ኤምኤስኤፍ ገለጸ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግመኛ ጦርነት በመቀስቀሱ ምክንያት ከመስከረም 12 እስከ መስከረም 15፣ 2019 ዓ. ም. ድረስ በኮረም እና አላማጣ ሆስፒታሎች የገቡ ታካሚዎች ቁጥር በ48 ሰዓታት ውስጥ ከ180 ወደ 420 ከፍ ማለቱን ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ) አስታወቀ።
በተቋሙ ድጋፍ መስከረም 15፣ በሰሜን ምዕራብ ትግራይ፣ ሽረ ወደሚገኘው ስኹል ሆስፒታል የገቡ በጦርነት የተጎዱ ታካሚዎች ከ300 በላይ እንደሚሆኑ ገልጿል።
ኤምኤስኤፍ ሰኞ መስከረም 18/2019 ዓ. ም. ባወጣው መግለጫ፤ በጦርነት ተጎድተው ወደ ሆስፒታል የሄዱ ታካሚዎችን ቁጥር ይፋ አድርጓል።
ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ እየተጎዱ ላሉ ታካሚዎች ድጋፍ ለመስጠት ከመስከረም 12 ጀምሮ የኤምኤስኤፍ አባላት እንቅስቃሴያቸውን እንዳሰፉም ጠቁሟል።
ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን አሁን ላይ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ "በጣም አስጊ ነው" ብሏል።
"ኤምኤስኤፍ በሽረ፣ ሽራሮ እና ኮረም በሆስፒታሎች የሚሰጠውን የሕክምና አገልግሎት መደገፍ ይቀጥላል" ሲል በመግለጫው አትቷል።
ይህም የእናቶች እና ሕጻናት ጤና ጥበቃን እንደሚያካትት ተመልክቷል።
"አሁን ባለው ሁኔታ ምክንያት በአላማጣ ሆስፒታል ያለው እንቅስቃሴ ተቋርጧል" ሲልም ኤምኤስኤፍ አስታውቋል።
በፀጥታ ሁኔታ ምክንያት "ነዋሪዎችን የመድረስ ሥራዎች (Outreach activities) መቋረጣቸውን" ገልጿል።
ሆኖም ግን "በጦርነት የተጎዱ ሰዎች በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመሩባቸው ባሉ አካባቢዎች" የተቋሙ ባለሙያዎች እንዲሰማሩ መደረጉን አብራርቷል።
ነዋሪዎች ከግጭት እየሸሹ በመሆኑ የተፈናቃዮችን ሁኔታ እየተከታተለ እንደሆነ ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን ጠቁሟል።
በትግራይ፣ በአማራ እና አፋር ክልሎች "የተፈናቃዮችን ፍላጎት ለማሟላት" ዝግጅት እያደረገ እንደሆነም ተገልጿል።
ግጭቱ እየተባባሰ ከመምጣቱ አንጻር የንጹኃን ዜጎች ደኅንነት እና የጤና አገልግሎት ተደራሽነት "እንዳሰጋው" ጠቅሷል።
በሌላ በኩል ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ግጭት ካለበት የትግራይ ክልል "161 ሰዎችን" ወደ አፋር ማዘዋወሩን መግለጹ አይዘነጋም።
ሰኞ ዕለት በማኅበራዊ ሚዲያው ባወጣው መግለጫ ላይ እንደተጠቀሰው፤ ከትግራይ ክልል ካስወጣቸው መካከል የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አባላት እና ቤተሰቦቻቸው፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኞች እና ቤተሰቦቻቸው፣ የሲቪል አቪዬሽን ደኅንነት ሠራተኞች፣ የአፍሪካ ኅብረት ታዛቢዎች እና የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር አባላት ይገኙበታል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ተቀስቅሶ የነበረው ደም አፋሳሹ ጦርነት ከአራት ዓመት በፊት በአፍሪካ ኅብረት አሸማጋነይት ከቆመ በኋላ በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት ኃይሎች መካከል ያለው ቁርሾ እየተካረረ መጥቶ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ዕለት በይፋ ዳግም ግጭት ውስጥ ገብተዋል።
በፌደራል መንግሥቱ እና በትግራይ ኃይሎች መካከል እንደ አዲስ ያገረሸው ጦርነት እንደቀጠለ ሲሆን፤ በአማራ እና አፋር ክልል አዋሳኝ ቦታዎች ውጊያዎች እየተካሄዱ መሆኑም ተዘግቧል።
ህወሓት "ከፌዴራል ኃይሎች ተፈፀመብኝ" ያለውን ጥቃት ለመከላከል ግጭት ውስጥ መግባቱን የጠቀሰ ሲሆን የፌደራል መንግሥቱም ከህወሓት ለተከፈተበት ጥቃት የመከላከያ እርምጃ መውሰዱን ገልጿል።
የአሁኑ ግጭት በይፋ የተጀመረው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት)፣ የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን) እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን ጨምሮ ሰባት ታጣቂ ቡድኖች " የፌደራል መንግሥቱን ከሥልጣን ለማውረድ" ጥምረት መፍጠራቸውን ባስታወቁ ማግስት ነው።
በትግራይ የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎት ሲቋረጥ፣ በአማራ ክልል ታሪካዊ ቅርስ መገኛ በሆነችው ላሊበላም በረራ መቆሙን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ እና ዩኤኢ ህወሓት በአጎራባች ክልሎች እና በደቡብ ትግራይ ፈፀመ ያሉትን ጥቃት እና በትግራይ ክልል ያሉ አየር ማረፊያዎችን መቆጣጠሩን አውግዘው የግጭቱ መባባስ እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።
የሂውማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ ዳይሬክተር ላቲሽያ ባደር በሲቪሎች ላይ ተጨማሪ ጉዳቶች እንዳይደርስ ለመከላከል የኢትዮጵያ ጦር የጦርነት ሕጎችን እንዲያከብር እና ጥቃት ከመፈፀሙ በፊት ሁሉንም ተጨባጭ የጥንቃቄ እርምጃዎችን ሊወስድ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በትግራይ ለሁለት ዓመት በተካሄደው እና በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተፈረመው የሰላም ስምምነት በተቋጨው ጦርነት ከ600,000 በላይ ሰዎች መሞታቸው ይገመታል።
































