ቀይ መስቀል የአየር መንገድ ሠራተኞች እና የአፍሪካ ኅብረት ታዛቢዎችን ጨምሮ 161 ሰዎችን ከትግራይ ማስወጣቱን አስታወቀ

የዓለም አቀፉ ቀይመስቀል መኪኖች
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ግጭት ካለበት የትግራይ ክልል "161 ሰዎችን" ወደ ሌላ ሥፍራ ማዘዋወሩን አስታወቀ።

ዛሬ ሰኞ መስከረም 18፣ 2019 ዓ. ም. በማኅበራዊ ሚዲያው ባወጣው መግለጫ ላይ እንደተጠቀሰው ከትግራይ ክልል ካስወጣቸው መካከል የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አባላት እና ቤተሰቦቻቸው፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኞች እና ቤተሰቦቻቸው፣ የሲቪል አቪዬሽን ደኅንነት ሠራተኞች፣ የአፍሪካ ኅብረት ታዛቢዎች እና የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር አባላት ይገኙበታል።

ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ 161ዱን ሰዎች ከትግራይ ያዘዋወረው "ሁሉም የሚመለከታቸው ኃላፊዎች ባቀረቡት ጥያቄ እና በሰጡት ይሁንታ መሠረት፣ የገለልተኛ ሚና በመወጣት" እንደሆነ በመግለጫው አትቷል።

ባለፈው ሳምንት ረቡዕ የትግራይ ኃይሎች በክልሉ ዋና ከተማ መቀለ የሚገኘውን አሉላ አባ ነጋ አውሮፕላን ማረፊያን መቆጣጠራቸው ከተሰማ በኋላ ስለ ሠራተኞቹ ደኅንነት ጥያቄ ሲነሳ ነበር።

የትግራይ ኃይሎች በክልሉ የሚገኙ ሦስት አውሮፕላን ማረፊያዎችን መቆጣጠራቸውን ተከትሎም በረራዎች ተቋርጠዋል።

በረራው "ላልተወሰነ ጊዜ መቋረጡን" የኢትዮጵያ አየር መንገድ በይፋዊ የማኅበራዊ ድረገጹ ላይ በወቅቱ አስታውቋል።

በፌደራል መንግሥቱ እና በትግራይ ኃይሎች መካከል እንደ አዲስ ያገረሸው ጦርነት እንደቀጠለ ሲሆን፤ በአማራ እና አፋር ክልል አዋሳኝ ቦታዎች ውጊያዎች እየተካሄዱ መሆኑም ተዘግቧል።

ዛሬ ወደ ኮምቦልቻ የሚደረግ በረራ ተቋርጦ የነበረ ቢሆንም ከሰዓት 8 ሰዓት አካባቢ ዳግመኛ መጀመሩን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ሆኖም ግን ከባለፈው ሳምንት አንስቶ በላሊበላ የተቋረጠው በረራ እስከ ዛሬ ድረስ አለመጀመሩን ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ከትግራይ ክልል መዲና መቀለ ከተማ ወደ አፋር ክልል ሰመራ የተደረገው ጉዞ የቀይ መስቀል አርማ ምልክት በተደረገባቸው አውቶቡሶች እና በዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ሠራተኞች እጀባ የተካሄደ እንደሆነ ተቋሙ አስታውቋል።

አያይዞም "በግጭቱ ውስጥ ካሉ ወገኖች ጋር ውይይት ማድረጉን በመቀጠል ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች ሁኔታ አሳሳቢ በሚሆንበት ጊዜ እና ሁሉም ወገኖች ለእንደዚህ ዓይነት ሥራዎች በሚስማሙበት ጊዜ ሁሉ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ" ገልጿል።

በትግራይ የኢትዮ ቴሌኮም የስልክ እና የኢንተርኔት መስመር የተቋረጠ ሲሆን፤ ይህም በሸቀጦች ግብይት እና በገንዘብ ዝውውር ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሯል።