የናይጄሪያ 'የሺህዎች ጋብቻ' እና አስቸጋሪ እየሆነ የመጣው ፍቅረኛሞችን ከአጭበርባሪዎች የመለየት ጣጣ

ቀይ ሒጃብ የለበሱ ሙሽሮች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የሁሉም የሠርግ አልባሳት ወጪ የተሸፈነው በካኖ ግዛት መንግሥት ነው
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

ባለፈው ሳምንት በሰሜናዊ ናይጄሪያ በምትገኘው ካኖ ከተማ የተሞሸሩት 1 ሺህ 500 የሚሆኑ ጥንዶች ድባብ ደማቅ እና በደስታ የተሞላ ነበር።

የከተማዋ ጎዳናዎች በሠርግ ዝግጅቶች ተጠምደው ነበር የሰነበቱት። የሙሽራዎቹ ቤተሰቦችም አልባሳት ሲያዘጋጁ እና ሌሎች ዝግጅቶች ላይ ሲሳተፉ ቆይተዋል።

አርብ ዕለት ቀይ ሒጃብ የለበሱ ሙሽሮች እና ቀይ ባርኔጣ እና ነጭ ካባ ከለበሱ ተጣማሪዎቻቸው ጋር ሆነው በይፋ ባል እና ሚስት የሚሆኑበትን ዋናው የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ለመታደም የከተማዋ ባህላዊ ሙስሊም መሪ ወደሆኑት ኢምር ቤተ መንግሥት አምርተዋል።

ቅዳሜ ዕለት ጠዋትም በግዛቷ አስተዳዳሪ አባ ካቢር ዩሱፍ ቡራኬ የተሰጣቸው ሲሆን የቁርስ ግብዣም ተደርጎላቸዋል።

ለዚህ 'የሺ ጋብቻ' ፕሮግራም የገንዘብ ድጋፍ ያደረገው የካኖ ግዛት መንግሥት ነው።

በትዳር መተሳሰር የሚፈልጉ ጥንዶችን ለመደገፍ ባሰናዳው ዝግጅት 1 ሚሊዮን ዶላር አውጥቷል። ለሙሽሮቹ ጥሎሽ እና የቤት ዕቃም ያበርክታል።

ፕሮግራሙ ትዳር ለመመስረት የገንዘብ ችግር የገጠማቸው ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ግለሰቦች ላይ ትኩረት የሚያደርግ ነው።

ይህ ዓመታዊ 'የጅምላ ሠርግ' የተጀመረው እአአ በ2012 ሲሆን ያስጀመሩት በወቅቱ የነበሩት አስተዳዳሪ ነበሩ።

የኔ በዋናነት አጋሮቻቸውን በሞት ያጡ እንዲሁም በፍቺ ተለያይተው እንደገና ትዳር ለመመስረት ያቀዱ 100 ጥንዶች በቤተ መንግሥቱ በተደገሰላቸው ሠርግ ጋብቻቸውን ፈፅመዋል።

ገዥዎች ቢቀያየሩም የጅምላ ሠርጉ መካሄዱን ቀጥሏል። ከአንድ በላይ ሚስት የሚያገቡትን ጨምሮ የጥንዶች በጅምላ ሠርጉ የመካተት ፍላጎት በመጨመሩ ቁጥሩም እያሻቀበ መጥቷል።

በዚህ ዓመት ብቻ ከአምስት ሺህ በላይ ጥንዶች በፕሮግራሙ ተጠቃሚ ለመሆን አመልክተዋል።

ፕሮግራሙ ሂስባህ በተባሉ በከተማዋ ባሉ የእስላማዊ ፖሊሶች ኃይል ቁጥጥር የሚደረግበት ሲሆን የእነዚህ ፖሊሶች ዋነኛ ሥራ ለመጋባት የሚፈልጉትን ጥንዶች ፍላጎት ትክክለኛ መሆኑን ማረጋገጥ ነው።

ካኖ ከተማ በአብዛኛው ሕዝቧ የእስልምና እምነት ተከታይ ሲሆን ከመደበኛው ሕግ ጎን ለጎን የሸሪአ ሕጎች ተግባራዊ ይሆናሉ።

የሂስባህ ምክትል ኮማንደር የሆኑት ሙጃሂድ አሚኑዲን፣ ሥራው ቀላል እንዳልሆነ ይናገራሉ።

"የሆነ ልክ ያልሆነ ወይም አጠራጣሪ ነገር ስናገኝ ከፕሮግራሙ እንሰርዛቸዋለን" ብለዋል።

ኮማንደሩ እንደሚሉት አንዳንድ ጥንዶች ከዕድሉ ለመጠቀም ፈልገው እንደሆነ ዓይናቸው ቢያሳብቅም እውነተኛ ፍቅረኛሞች እንደሆኑ በመግለፅ ባለሥልጣናቱን ለማሳመን ብዙ ርቀት ይጓዛሉ።

እስላማዊ ፖሊስ ቢሮ ውስጥ የሚስተናገዱ ሰዎች እና ፖሊሶች

የፎቶው ባለመብት, Mahmud Bashir

የምስሉ መግለጫ, የእስላማዊ ፖሊስ ቢሮ (ሂስባህ) ዕድሉ የሚሰጣቸውን ጥንዶች ለመምረጥ ለሳምንታት በሥራ ተጠምደው ቆይተዋል
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የግዛቲቷ መንግሥት ለአንድ ጥንዶች 735 ዶላር የሚሆን ገንዘብ አውጥቷል።

እንደ ሂስባህ ከሆነ የድጋፍ ማዕቀፉ ጥንዶቹ አዲስ ለሚቀልሱት ጎጆ የሚሆኑ እንደ አልጋ፣ ፍራሽ፣ አንሶላ፣ ትራስ እና የቤት ውስጥ መገልገያ ቁሳቁሶችን ያካትታል።

ከዚህም በተጨማሪ ሴት ሙሽራዎች እያንዳንዳቸው 100 ሺህ ናይራ ጥሎሽ የሚበረከትላቸው ሲሆን ጥንዶቹ ጋብቻ ከመሰረቱ በኋላ በገቢ ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ ለአነስተኛ ንግድ መነሻ የሚሆን ተጨማሪ 100 ሺህ ናይራ ይሰጣቸዋል።

ጋብቻ ለመመስረት የተዘጋጁት ጥንዶች በፕሮግራሙ ከመካተታቸው በፊትም ኤችአይቪ፣ ሂፐታይተስ፣ የእርግዝና እና የዘረ መል ችግር አለመኖርን ጨምሮ የሕክምና ምርመራ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

አሚኒዱን እንደሚሉት የተወሰኑ ጥንዶች የምርመራ ውጤታቸውን ለማቅረብ ባለመፈለጋቸው ከፕሮግራሙ እንዲወጡ ተደርገዋል።

በአንድ ኬዝ አንዲት ሙሽራ ከፕሮግራሙ ጥቅም ለማግኘት ስትል ወንድሟን ሙሽራዋ አድርጋ ማቅረቧን ኮማንደሩ ጠቅሰዋል።

ለዓመታት ሲካሄዱ የነበሩ የጅምላ ሠርጎችን የዘገበው የአካባቢው ጋዜጠኛ ዩሱፍ አሊ አብደላህ፣ በናይጄሪያ ያለው የኢኮኖሚ ቀውስ በዚህ ዓመት የአመልካቾች ቁጥር እንዲጨምር አድርጎታል ብሏል።

" ሁላችንም እንደምናውቀው ጋብቻ መመሥረት ገንዘብ የሚጠይቅ ቢሆንም አሁን ላይ በአገሪቷ ያለው ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ተስፋ ሰጪ አይደለም" ሲል ለቢቢሲ ገልጿል።

በዚህም ምክንያት አንዳንድ ሰዎች ፕሮግራሙ ውስጥ መካተት ይፈልጋሉ።

ቀድሞውኑ ትዳር የመሠረቱ ጥንዶች ራሳቸውን በጋብቻ ለመተሳሰር የተዘጋጁ ጥንዶች አድርገው ያቀረቡ ሲሆን ጉዳዩ ከተደረሰበት በኋላ ከፕሮግራሙ እንዲወጡ ተደርገዋል።

ከዚህም ባሻገር በፕሮግራሙ ለመካተት ከሚሞክሩ ጥንዶች ጥቅም ለማግኘት የሚሞክሩ አጭባርባሪዎችም ተበራክተዋል። ጉዳዩ ከሁለት ሳምንት በፊት መነጋጋሪያ ሆኖ ነበር።

አንድ ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ የከተማዋ ነዋሪ በዝርዝሩ ውስጥ ለመግባት ጉቦ እንደተጠየቀ ተናግሯል።

"በኋላ ላይ ግን ገንዘብ የጠየቁኝ ሰዎች የሂስባህ አባላት እንዳልሆኑ ደረስኩበት" ብሏል።

እርሱ እና እጮኛው በዚህ ዓመት ለተካሄደው ሠርግ ሳይመረጡ ቀርተዋል። ሆኖም በሚቀጥለው ዓመት ፕሮግራም ላይ ለመካተት እንደሚሞክር ተናግሯል።

 የ24 ዓመቷ አሚና አልሃሳን

የፎቶው ባለመብት, Mahmud Bashir

የምስሉ መግለጫ, የ24 ዓመቷ አሚና አልሃሳን የጅምላ ሠርጉ ተጠቃሚ ባትሆን ኖሮ አሁን ላይ ትዳር ለመመስረት አቅሙ እንደማይኖራት ተናግራለች

ምክትል ኮማንደር አሚኑዲን እስላማዊው ፖሊስ እንዲህ ዓይነት ክሶችን እንደሚያውቅ ገልጸው፤ "ጥንዶች በዝርዝሩ ውስጥ እንዲካተቱ ለማድረግ ገንዘብ የሚጠይቁ አንዳንድ ሰዎች እንዳሉ ደርሰንበታል" ብለዋል።

አሚኑዲን ወደፊት በዚህ ፕሮግራም ውስጥ ተካተው ጋብቻቸውን መፈፀም የሚፈልጉ ጥንዶች የሚከፍሉት ምንም ሽራፊ ሳንቲም እንደሌለ አስረግጠዋል።

"ለካኖ ሕዝብ ሁሉም ሂደት ነፃ መሆኑን እና ከምርጫው ጀምሮ እስከ የሕክምና ምርመራው ድረስ እንዲሁም የሚደረግላቸው የቁሳቁስ ድጋፍ በመንግሥት እንደሚሸፈን ማሳወቅ እንፈልጋለን" ብለዋል።

በዚህ ወጪው በመንግሥት የሚሸፈን የሠርግ ፕሮግራም ትዳር የመሠረተው የ43 ዓመቱ የልብስ ነጋዴ ራቢዩ ዩሱፍ የጋብቻ ሥነ ሥርዓቱ በጥሩ መልኩ እንደተካሄደለት ገልጿል።

"በግሌ ማንም ምንም አልጠየቀኝም። መንግሥት ሁሉንም ወጪ እንደሚሸፍን ተነግሮኝ ነበር" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

ዩሱፍ ከባለቤቱ አይሻ ኦዋል ጋር የተዋወቁት ልብስ ለመግዛት ወደ ሱቁ በምትመላለስበት አጋጣሚ ነበር።

ከመጀመሪያ ሚስቱ አምስት ልጆች ያሉት ዩሱፍ " ደስተኛ መሆኑን እና አሁን ሙሽራው ከሆነችው ደንበኛው ጋር አዲስ ሕይወት ለመጀመር መጓጓቱን" ገልጿል።

ሌላኛዋ ተጋቢ የ24 ዓመቷ አሚና አልሃሰንም የእርሱን ሃሳብ ነው የምታስተጋባው። ከ40 ዓመቱ ኑራ አብዱላሂ ጋር ትዳር ለመመስረት ባመለከተችበት ጊዜ የገጠማት ተግዳሮት እንደሌለ ገልጻለች።

" ሁሉም ነገር ነፃ ነበር። ለዚህ ፕሮግራም የካኖን መንግሥት አመሰግናለሁ፤ ምክንያቱም በኑሮ ውድነቱ ምክንያት በርካቶች ያለዚህ ድጋፍ ትዳር መመስረት አይችሉም ነበር" ብላለች።

ከቅዳሜ ዕለቱ የሠርግ ድግስ በኋላ ለጥንዶቹ የቤት ቁሳቁሶች መቅረብ ጀምረዋል።

አዲሶቹ ተጋቢዎች ቤታቸውን ለማዘጋጀት በሥራ ስለተጠመዱ በካኖ ያለው ፌሽታና ግርግር ለመቀዝቀዝ በርካታ ቀናትን መውሰዱም አይቀሬ ነው ።