ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን ነጋዴዎችን ጨምሮ በርካቶችን ያሰጋው የኬንያ ፕሬዝዳንት ትዕዛዝ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

ንዲኬች አሊ በኬንያ መዲና ናይሮቢ የባጃጅ ሹፌር ነው። ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ዋነኛ ችግር የሆነበት የናይሮቢ የትራፊክ መጨናነቅ ነው። መጤ ጠልነት ይገጥመኛል ብሎ ግን አላሰበም።

ቡሩንዲያዊው ንዲኬች ኬንያውያን እንግዳ ተቀባይ እንደሆኑ ይናገራል፤ በቀላሉ ጓደኛ ለማድረግም ይመቻሉ ይላል። ባለፈው ሳምንት ግን ሁሉም ነገር ተለወጠ።

ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ ከውጭ አገራት ወደ ኬንያ የገቡ ጥቃቅን እና አነስተኛ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ትዕዛዝ ሰጡ።

"አሁን ተነስተውብናል" ይላል ንዲኬች። ወደ አገራቸው ለመመለስ የሚያስፈልጋቸውን ሰነድ ከሚጠባበቁ አንዱ ነው።

ባለፈው ሳምንት በርካታ የቡሩንዲ ዜጎች በረዥሙ ተሰልፈው ይሄንን ሰነድ ለማግኘት ሞክረዋል።

"ማስፈራሪያው ብዙ ነው። ሕጻናት እንኳን አልቀሩም። ውሻ ተፈትቶ የተለቀቀብን ያህል ነው የተሰማን። ተደብድበናል።"

የውጭ አገር ዜጎችን ከጥቃቅን እና አነስተኛ ንግድ የሚያግድ እንዲሁም አንዳንድ ንግዶችን ለኬንያውያን የሚሰጥ ሕግ በምክር ቤት ይቀርባል። ፕሬዝዳንቱ ይሄንን ረቂቅ በቤተ መንግሥታቸው ሲያስተዋውቁ ነው በወጭ አገር ነጋዴዎች ላይ ስለሚወሰደው እርምጃ ይፋ ያደረጉት።

ፕሬዝዳንቱ ለውጭ አገር ነጋዴዎች ቀነ ገደብ አስቀምጠው፣ ሱቃቸውን እንዲዘጉ አስጠንቅቀዋል። ጥቃቅን እና አነስተኛ ንግድ የኬንያውያን መሆን አለበት ብለዋል።

ንዲኬች እና ሌሎችም በፕሬዝዳንቱ ትዕዛዝ ደንግጠዋል። ኬንያውያን የፕሬዝዳንቱን መልዕክት ከሰሙ በኋላ የውጭ ዜጎች በአገራቸው ተቀባይነት እንደሌላቸው ይሰማቸዋል በሚልም ፈርተዋል።

"ጥቃት እየደረሰብን ነው፤ መሥራት አልቻልንም። መሥራት ካልቻልን ምግብ መግዛት እና ቤት ኪራይ መክፈል አንችልም። ሥራችን ሲነጠቅ ያለው ብቸኛ አማራጭ አገራችን መግባት ነው።"

ቡሩንዲያውያን እና ከሌላ አገር ወደ ኬንያ የገቡ ዜጎችም በድንጋጤ አገሪቱን ጥለው ለመሸሽ ወደ ድንበር አቅራቢያ ሄደዋል።

አብዛኞቹ ከድንበር ማለፍ አልቻሉም።

ጥንዶች ለመለያየት እንገደዳለን ብለው ፈርተዋል። የተለያዩ የቤተሰብ አባላትም አሉ።

ከኬንያዊት ልጅ የወለደው ፕሮስፐር የተባለ ቡሩንዲያዊ "ከ2019 ጀምሮ እዚህ ኖሬያለሁ" ይላል።

"ትዕዛዙን ስሰማ በጣም ነው ያሳዘነኝ። ቤተሰቤን ጥዬ ለመሄድ ልገደድ ነው ማለት ነው። ቤተሰቤን እወዳቸዋለሁ።"

አነስተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች በሚኖሩበት የናይሮቢ ማጄንጎ መንደር የምትኖረው ግሬስ ዋማታ እንደምትለው የፕሬዝዳንቱ ትዕዛዝ በተሰማ በማግስቱ ቡሩንዲያዊ ባለቤቷ ከአገር ወጥቷል።

አምስት ልጆቻቸውን ማሳደግ ስላልቻለች ልብስ በማጠብ ተጨማሪ ሥራ ጀምራለች።

"እሱ ሄዷል። የትምህርት ቤት ክፍያ ማን ያግዘኛል? ምን ማድረግ እንዳለብኝ አላወቅም። እንዲመለሱ ይፈቀድላቸው።"

በናይሮቢ እና በሌሎች የኬንያ ከተሞች የውጭ አገር ዜጎች በፀጉር ቤት፣ በግንባታ፣ ሞተርሳይክል በመንዳት፣ በጎዳና ላይ ንግድ፣ ልብስ እና ምግብ በመሸጥ እንዲሁም የቤት ውስጥ መገልገያዎችን በመነገድ ይተዳደራሉ።

አንዳንዶች በአገራቸው ያለውን የምጣኔ ሃብት ጫና በመሸሽ ወደ ኬንያ ተሰድደዋል። የተቀሩት ደግሞ የተሻለ አማራጭ በመፈለግ ኬንያ ገብተዋል።

የስምት አገራት ቀጣናዊ ትብብር የሆነው ምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ ስብስብ ነጻ ዝውውርን ይፈቅዳል። ኬንያ እና ቡሩንዲ የስብስቡ አባላት ናቸው።

ነጻ ዝውውር ቢፈቀድም የሥራ እና የኑሮ ፈቃድ ለማግኘት ማመልከት ያስፈልጋል።

የኬንያ ሕግ ስደተኞች በአገሪቱ የመሥራት መብት እንዳላቸው ይደነግጋል። ነገር ግን ተገቢውን ሕጋዊ ሰነድ ማውጣት አለባቸው።

በናይሮቢ የኤርትራውያን ማኅበረሰብ አስተባባሪ ፊሊሞን ኢዮብ እንደሚለው፤ የፕሬዝዳንቱ ትዕዛዝ የውጭ ዜጎች ላይ ጥቃት ለማድረስ እንደ ሽፋን ሊውል ይችላል።

አብዛኞቹ ኬንያውያን የውጭ አገር ዜጎችን ቢቀበሉ እና ቢደግፉም እንኳን አንዳንድ ኤርትራውያን እና ኢትዮጵያውያን ለቅድመ ጥንቃቄ በሚል ንግዳቸውን ዘግተው ቤት ለመቀመጥ መገደዳቸውን ለቢቢሲ ተናግሯል።

የሩቶ ንግግር ከቡሩንዲ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት አስከትሏል። የቡሩንዲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር "ቡሩንዲ ላይ የተቃጣ የጥላች ንግግር" ብሎታል።

ከኬንያ ውጭ በሚኖሩ ኬንያውያን ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር መሆኑንም ገልጿል።

የኬንያ ባለሥልጣናት ትርክቱን ለመቆጣጠር እየታገሉ ነው። የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኮሪር ሲንኦይ ወደ ቡሩንዲ ኤምባሲ አቅንተው ዜጎቹን ይቅርታ ጠይቀዋል። መንግሥት ከጥቃት እንደሚከላከላቸውም ማረጋገጫ ሰጥተዋል።

ተቺዎች እንደሚሉት የሩቶ ንግግር ዕውቅናን ከማትረፍ ያለፈ የመጤ ጥላቻን የሚያነሳሳ ነው። የኬንያ መንግሥት ይሄንን አስተባብሏል።

የፕሬዝዳንቱን ትዕዛዝ የሚያብራሩ መግለጫዎችም እየወጡ ነው።

መንግሥት ሰነድ አልባ የሆኑ በጥቃቅን እና አነስተኛ ንግድ የተሰማሩ የውጭ አገር ዜጎች እንዲመዘገቡ 90 ቀናት ሰጥቷል።

የተመዘጉ የውጭ አገር ዜጎች ኬንያ ውስጥ በሕጋዊ መንገድ እንደሚኖሩ ዕውቅና ይሰጣቸዋል።

ተንታኞች ግን በዚህ መንገድ መከናወን አልነበረበትም ሲሉ ይከራከራሉ።

ተመራማሪው ሄስቦን ኦዊላ ለቢቢሲ እንደገለጹት የፕሬዝዳንቱ አስተያየት፣ በተለይም ሰነድ አልባ በሆኑ ሰዎች ላይ በተሳሳተ መንገድ የሚተረጎምበት ዕድል ሰፊ ነው።

የቀረበው ምክረ ሐሳብ ለኬንያ መልካም ቢሆንም ከዓለም አቀፍ የስደተኞች ድንጋጌ ጋር የሚጣጣም መሆን ይገባዋል ይላሉ።

መረጃው የተላለፈበት መንገድ ዲፕሎማሲያዊ መሆን እንደነበረበት ይገልጻሉ።

ፕሬዝዳንቱ ንግግር ባደረጉበት ቦታ ያልተገኙ ሰዎች ትዕዛዙን የተረጎሙት "እነዚህ ሰዎች እናባርራቸዋለን" በሚል እንደሆነ ያስረዳሉ።

ሩቶ በጥቃቅን እና አነስተኛ ነጋዴዎች ብቻ አላቆሙም። የሕንዱ ታታ ኬሚካልስ አገሪቱን ጥሎ እንዲወጣ አዝዘዋል። ኩባንያው በካጂያዶ ግዛት ለማሳይ ማኅበረሰብ በቂ ጥቅም አለመስጠቱን ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።

ኩባንያው ከማጋዲ ሐይቅ ለዓመታት ሶዳ አሽ የተባለውን ንጥረ ነገር ሲያወጣ ቆይቷል።

የማዕድን ቁፋሮው የተጀመረው ኬንያ በብሪታኒያ ቅኝ ግዛት ስር በነበረችበት በአውሮፓውያኑ 1911 ነበር።

ከመሬት ይዞታ እና ከግብዓት ጋር በተያያዘ ለዓመታት ውዝግብ ቢኖርም ኩባንያው ሥራውን ቀጥሏል። በሚነሱ ውዝግቦች ምክንያት ማኅበረሰቡ ከመንግሥት ጋር በተደጋጋሚ ተጋጭቷል።

የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ኦዲሂምቦ ራሞጊ እንደሚናገሩት የውጭ አገር ዜጎችን ከንግድ ማገድ መጠነ ሰፊ ውሳኔ ነው። መከናወን ያለበትም ብልሀት በተሞላው መንገድ ነው ይላሉ።

ኬንያ በዋነኛነት ከምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና በመቶ ሺህዎች ለሚቆጠሩ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች መኖሪያ እንዲሁም ሌሎችም ዓለም አቀፍ ባለ ሃብቶች መኖሪያ መሆኗን ይጠቅሳሉ።

የሩቶ ዓላማ "ኬንያውያን ሥራ እንዲያገኙ ከማረጋገጥ የዘለለ" መሆኑን ይናገራሉ።

የፕሬዝዳንቱ ውሳኔ ከሲቪል ማኅበራትን እና ከኬንያውያንም ተቃውሞ ገጥሞታል። ለውጭ አገራት ዜጎች ያላቸውን ድጋፍም አሳይተዋል።

በዚህ ዓመት ነሐሴ ላይ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የሚጠብቃቸው ሩቶ ትዕዛዛቸውን ለመከላከል ሞክረዋል።

በቃል አቀባያቸው በኩል የወጣ መግለጫ "ኬንያ ክፍት፣ ተቀባይ እና ደኅንነቷ የተጠበቀ አገር መሆኗ ይቀጥላል። የዜጎችን ዕድል የምትጠብቅ እና በግዛቱ ውስጥ ያሉ ሁሉም ሰዎች በሕጋዊ መንገድ የሚሠሩባትም ናት" ይላል።

ኬንያ ለምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ ስብስብ እና ለአፍሪካም "ታማኝ" ሆና እንደምትቀጥልም አክለዋል።

የምጣኔ ሃብት ባለሙያው በበኩላቸው ኬንያ የጎረቤት አገራትን ዜጎች ዒላማ በማድረግ እንደምትጎዳ ይናገራሉ።

ባለፈው ዓመት ኬንያ ከቡሩንዲ ጋር በተደረገ የውጭ ንግድ 56 ሚሊዮን ዶላር ማግኘቷን ጠቅሰዋል። አገሪቱ ከውድድር ተጠቃሚ እንደምትሆንም ተናግረዋል።

አያይዘውም "የውጭ አገር ዜጎችን ማስወጣት ማለት በውድድር የሚያድግ ምጣኔ ሃብት በፍጥነት እንዲመነደግ አለመፈለግ ነው" ይላሉ።

ከአንድ አገር የሚገኘው የምጣኔ ሃብት ጥቅም አስከ 56 ሚሊዮን ዶላር ከሆነ "በወር 200 ዶላር ለሚያገኘው ለምን ትጨነቃላችሁ?" ሲሉም በንጽጽር አስቀምጠዋል።

ባለሙያው "ፕሬዝዳንቱ ያደረጉት ምንም ትርጉም አይሰጥም" ብለዋል።

የናይሮቢ ነዋሪዋ ሊማ ካቡራ ባለቤቷ ታንዛኒያዊ ነው። የፕሬዝዳንቱ ንግግር አላስደሰታትም።

ሩቶ መጀመሪያ ላይ በአገሪቱ ውስጥ በሕገ ወጥ መንገድ የሚኖሩትን ማቋቋም እንዳለባቸው ትናገራለች።

"የሚባረሩ ከሆነ ሥራ አይኖረኝም፤ ንግድ አይኖረኝም፤ ባልም አይኖረኝም" ትላለች።