የኬንያው ሚኒስትር በአሜሪካ የኢቦላ ማዕከል ግንባታ የተነሳ ፍርድ ቤት በመድፈር ጥፋተኛ ተባሉ

የኬንያ የጤና ሚኒስትር ኤደን ዱአሌ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የኬንያ የጤና ሚኒስትር ኤደን ዱአሌ ከአወዛጋቢው የአሜሪካ የኢቦላ ለይቶ ማቆያ ማዕከል ግንባታ ጋር በተያያዘ ፍርድ ቤትን በመድፈር ጥፋተኛ ተባሉ።

ባለፈው ወር የኬንያ ፍርድ ቤት በኛኙዩኪ ከተማ በሚገኝ ወታደራዊ ሰፈር የሚካሄደው 50 አልጋዎች ያሉት የለይቶ ማቆያ ማዕከል ግንባታ እንዲቆም ውሳኔ አሳልፏል።

ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን መመልከት የጀመረው የመብት ተሟጋች ቡድኖች ባቀረቡትን አቤቱታ የተነሳ ነው።

ይሁን እንጂ የጤና ሚኒስትሩ የፍርድ ቤቱን ብይን ወደ ጎን በማለት ግንባታው እንዲቀጥል መፍቀዳቸውን ሠኞ ዕለት ዳኛው ተናግረዋል። ለዚህ ድርጊታቸው ጥፋተኛ የተባሉት የጤና ሚኒስትሩ ማክሰኞ የቅጣይ ብይን ይተላለፍባቸዋል።

የለይቶ ማቆያ ማዕከሉ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በተቀሰቀሰው የኢቦላ ቫይረስ የተጠረጠሩ አሜሪካዊያን እንዲታከሙበት የታሰበ ነው።

እቅዱ ከዋና ከተማዋ ናይሮቢ 140 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በኛኙዩኪ ቁጣ እና ተቃውሞ የቀሰቀሰ ሲሆን፤ ፖሊስ ተቃዋሚዎችን ለመበተን ሲሞክር ሦስት ሰዎች ተገድለዋል።

ከሟቾቹ መካከል የ17 ዓመቱ ቄስ ለመሆን ህልም ያለው ተማሪ ስልቬስተር ሙጊ ናደንጉ አንዱ ነው። የዓይን እማኞች ስልቬስተር ግንባሩን በጥይት ተመትቶ ሕይወቱ እንዳለፈ ሲናገሩ፤ ፖሊስ የሞቱን ምክንያት ለማወቅ የአስከሬን ምርመራ ውጤት እየጠበቀ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግሯል።

መጋቢት ላይ ግንባታው እንዲቆም ለፍርድ ቤት አቤቱታ ያቀረበው 'ዘ ካቲባ ኢንስቲትዩት' ስምምነቱ "ከባድ እና የማይቀሩ አደጋዎችን" ለኅብረተሰቡ ጤና መደቀኑን አስጠንቅቋል።

በኋላ ላይ የጤና ሚኒስቴር የአሜሪካ እና ኬንያ የግንባታ ሥራ እንዲቆም የተወሰነው የፍርድ ቤት ውሳኔ ተዘዋውሯል ሲል አጥብቆ ተናግሯል። ለዚህም ምክንያት ሲያቀርብ በኬንያ መንግሥት የቀጠለው ግንባታ ኬንያዊያንን ከኢቦላ ለመጠበቅ ሲባል ለብሔራዊ ጥቅም የሚገነባ ነው ብሏል።

ይሁን እንጂ ሠኞ ዕለት ዳኛዋ መንግሥት "ሥም በመቀየር አሊያም ዓላማውን በማዘዋወር ለፍርድ ቤት ተገዢ ላለመሆን ግንባታውን መቀጠል" አይችልም ብለዋል። የፍርድ ቤት ትዕዛዝ "ለፈጠራ ግብዣ አይደለም። ሊከበር የሚገባ ትዕዛዝ ነው" ሲሉ አክለዋል።

ዳኛ ፐትሪሺያ ናዩንዲ የጤና ሚኒስትር ዱአሉ በናንዩኪ የሚደረገው ግንባታ በሙሉ እንዲቆም እንዳወቁ እና እንደተረዱ ተናግረው፤ ነገር ግን ግንባታው እንዲቀጥል ፈቅደዋል ብለዋል።

በቅርብ ሳምንታት የኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ የአሜሪካን የኢቦላ የለይቶ ማቆያ ማዕከል እቅድ ደግፈው ተከራክረዋል። ፕሬዝዳንቱ ከአሜሪካ ማዕከሉን ለማቋቋም ፈቃድ እንደተጠየቁ እና ፈቃደኛ አለመሆን "ኢ-ሰብዓዊነት" ነው ብለዋል።

ኬንያዊያን እንደ ኢቦላ አይነት "አሳሳቢ" የሆነውን ጉዳይ ፖለቲካዊ እንዳያደርጉት ጥሪ ያቀረቡት ፕሬዝዳንቱ፤ ፖለቲከኞችን ደግሞ "ግዴለሽ" ከሆኑ ንግግሮች እንዲታቀቡ ጠይቀዋል።

የምሥራቅ አፍሪካ ባለ ግዙፍ ምጣኔ ሀብት ባለቤት በሆነችው ኬንያ እስከ አሁን ድረስ የኢቦላ ኬዞች አልተመዘገበም።

1,000 በበሽታው የተያዙ ሰዎች የተገኙባት ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና 20 የተረጋገጡ ሰዎች ያሳወቀችው ኡጋንዳ ተጠቂ የኢቦላ አገራት ናቸው። በኡጋንዳ በቫይረሱ ተይዘው የተገኙ ሰዎች አብዛኞቹ ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የመጡ ናቸው።