ሩሲያ በዩክሬን የድሮን ዐውደ ርዕይ ላይ በፈጸመችው ጥቃት 10 ሰዎች ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, Ukrainian President Zelensky
በዩክሬን መዲና ኪቭ ውስጥ በፈጸመቻቸው ጥቃቶች 15 ሰዎች ተገደሉ። ከእነዚህ ውስጥ 10 ያህሉ የተገደሉት በዋና ከተማዋ አቅራቢያ እየተካሄደ በነበረ የድሮን ዐውደ ርዕይ ላይ በደረሰ የባለስቲክ ሚሳዔል ጥቃት ነው።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ እንደተናገሩት፤ ዐውደ ርዕዩ ላይ በደረሰው ጥቃት ወደ 100 የሚጠጉ ሰዎች ተጎድተዋል።
ዐውደ ርዕዩ ላይ ከፍተኛ የመከላከያ ባለሥልጣናት ተገኝተዋል።
በዩክሬን ምሥራቃዊ ከተማ ሶሎቪናስክ በደረሰ የሩሲያ የቦምብ ጥቃት አምስት ሰዎች ተገድለዋል።
በሰሜናዊ ከተማ ሱሚ ሁለት ወንዶች መገደላቸውንም ወታደራዊ አመራሮች አረጋግጠዋል።
ዜሌንስኪ፤ ሩሲያ "በቀጣይ 48 ሰዓታት ውስጥ" ሌላ መጠነ ሰፊ የሚሳዔል ጥቃት እንደምታደርስ የሚጠቁም የደኅንነት መረጃ ትናንት አርብ ምሽት እንደደረሳቸው ተናግረዋል።
ትናንት ዩክሬን በሩሲያዋ ኪሮቭ ከተማ ባደረሰችው ጥቃት ስድስት ሰዎች ሲገደሉ 26 ሰዎች ተጎድተዋል።
ጥቃቱ የደረሰበት ሥፍራ ከውጊያ አውድማው 1,000 ኪሎሜትር ይርቃል።
የሩሲያ ግዙፍ የበይነ መረብ መደብር የሆነው ዋይልድቤሪስ መጋዘን ላይም ዩክሬን ጥቃት ፈጽማለች።
በኪቭ አቅራቢያ ጥቃት ሲደርስ የመከላከያ ሚኒስትሩ አማካሪ ሰርሂያ ቤስክሬስቶኖቭ እና የዩክሬን ጦር የቴክኖሎጂ ባለሙያ ሉዩባ ሺፖቪች ደኅንነት ጉዳይ አስጊ ሆኖ ነበር።
ሁለቱም ባለሥልጣናት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ደኅና መሆናቸውን አረጋግጠዋል። ቤስክሬስቶኖቭ በደኅንነት ስጋት ምክንያት በዐውደ ርዕዩ ላይ እንዳልተገኙም አስታውቀዋል።
የዩክሬን አየር ኃይል ቃል አቀባይ ዩሪ አሀንት ለአገሪቱ ቴሌቭዥን ጣቢያ እንደተናገሩት፤ ሦስት ባለስቲክ ሚሳዔሎች ተተኩሰው አንዱን ማክሸፍ ተችሏል።

የፎቶው ባለመብት, Ukrainian President Zelensky
ሩሲያ ጥቃቱን መሰንዘሯን አረጋግጣለች። የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ በከፍተኛ ርቀት ተጉዘው ዒላማ የሚመቱ የረዥም ርቀት መሣሪያዎች ጥቅም ላይ መዋላቸውን አስታውቋል።
የጥቃቱ ዒላማ የሆነው ሥፍራ በሩሲያ ሲቪሎች ስፍራዎች ላይ የሚተኮስ ድሮን ለዕይታ የቀረበበት እንደሆነ ሞስኮ ገልጻለች።
"በሩሲያ ግዛት ጥቃት ለማድረስ የሚያቅዱ እና ጥቃት የሚፈጽሙ" የድሮን አምራቾች እና የዩክሬን የድሮን ኃይል የደኅንነት ባልደረቦች በሥፍራው እንደተገኙ የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ገልጿል።
ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች ወዲህ እንዲህ ያለ ጥቃት ስትፈጽም የአሁኑ ቢያንስ ለሦስተኛ ጊዜ ነው።
መሰል ሕዝባዊ ክንውኖች ማካሄድ እና በስፋት ማስተዋወቅ አስፈላጊ አይደለም በሚል ቁጣ ተስተጋብቷል።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ጉዳዩ ላይ ምርመራ ይካሄዳል ብለዋል። የአገሪቱ ዋና ዐቃቤ ሕግ ዐውደ ርዕዩ እንዲካሄድ ማን እንደወሰነ እና ምን የደኅንነት ጥንቃቄ እንደተደረገ እንደሚመረመር አስታውቀዋል።
ዩክሬን የሩሲያ መጋዘን ላይ ጥቃት ካደረሰች በኋላ ዜሌንስኪ "ዩክሬንን ለመደብደብ የጦር አውሮፕላን እና ሚሳዔል ከሚያቀርቡ ቁልፍ ወታደራዊ ተቋማት አንዱን መትተናል" ብለዋል።
በሰዓታት ልዩነት ሩሲያ የድሮን ዐውደ ርዕዩ ላይ ጥቃት ፈጽማለች።
ባለፈው ሳምንት በሴንት ፒተርስበርግ ቢያንስ ሁለት የዋይልድቤሪስ መጋዘኖች ላይ ጥቃት ደርሷል።
ጥቃቱ የሩሲያ አነስተኛ እና መካከለኛ ነጋዴዎች ሸቀጥ ላይ ጉዳት አስከትሏል።
በዋይልድቤሪስ ድረ ገጽ ላይ ሰውነትን ከአደጋ የሚከላከል ትጥቅ (body armour) ለሽያጭ ቀርቧል።
ኪቭ በነዳጅ ማከማቻ እና ማብላያዎች ላይ ለወራት ጥቃት ስትሰነዝር ቆይታለች። አሁን ላይ እንደ ዋይልድቤሪስ ያሉ የሎጅስቲክስ ተቋማትን ዒላማ ማድረግ መጀመሯን አስታውቃለች።
እነዚህ ተቋማት መሣሪያ ለመግዛት ስለሚውሉ የጥቃት ዒላማ በማድረግ የሩሲያን ጦር እንደምታዳክም ገልጻለች።
ዜሌንስኪ በቀጣይ ሳምንት በዋይት ሀውስ ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር እንደሚወያዩ ይጠበቃል።
ዋሽንግተን የዩክሬን እና ሩሲያ የሰላም ውይይትን በድጋሚ የማስጀመር ዕቅድ አላትም ተብሏል።
የትራምፕ ዋነኛ ደጋፊ ላውራ ሉመር ትናንት አርብ በኪቭ ለዜሌንስኪ ቃለ ምልልስ አድርጋለች።
ፕሬዝዳንቱ የአሜሪካው ሴናተር ሊንዚ ግርሀም የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።















