በትግራይ ክልል የኢትዮ ቴሌኮም የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋረጠ

ስልኩን የሚመለከት ሰው ምስል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በትግራይ ክልል ከትናንት ሌሊት ጀምሮ የኢትዮ ቴሌኮም የኢንተርኔትና የስልክ አገልግሎት መቋረጡ ተገለጸ።

በኢንተርኔት ነፃነት ላይ የሚሰራው ኔት ብሎክስ የተሰኘው ድርጅትም ከትናንት ሐሙስ ሌሊት ጀምሮ በትግራይ የኢንተርኔት አገልግሎት በከፍተኛ ደረጃ መስተጓጎሉን አስታውቋል።

ቢቢሲም ወደ መቀለ እና ሽሬ በኢትዮ ቴሌኮም መስመር ያደረጋቸው የስልክ ጥሪ ሙከራዎች አልተሳኩም። የሳፋሪኮም የስልክ አገልግሎት ግን እንደሚሰራ አረጋግጧል።

የፈረንሳይ የዜና ወኪል፣ ኤኤፍፒ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡን ዘግቧል።

ቢቢሲ ከኢትዮ ቴሌኮም ኮሚኒኬሽን ኃላፊ አገልግሎቱ ስለመቋረጡ ለመጠየቅ በተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ እና በጽሑፍ መልዕክት ያደረገው ሙከራ ለጊዜው ምላሽ አላገኘም።

ቢቢሲ የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎቱ የተቋረጠው በኢትዮ ቴሌኮም ወይም በሌላ ወገን ስለመሆኑ ማረጋገጥ አልቻለም።

በትናንትናው ዕለት የክልሉ ነዋሪዎች የስልክ አገልግሎቱ መቋረጥ በገንዘብ ዝውውር እና ሸቀጦች ግብይት ላይ ከፍተኛ ጫና ይፈጥራል በሚል ስጋታቸውን ገልጸው ነበር።

ቢቢሲ ዛሬ ማለዳ ያነጋገራቸው ነዋሪ አብዛኛው የክልሉ ሕዝብ የኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎት ተጠቃሚ መሆኑን አስረድተው፣ በቀጣይ ሰዓታት ግንኙነቱ መልሶ ሥራ ካልጀመረ በርካታ ነዋሪዎች ከግንኙነት እና ከአገልግሎት ውጪ ሊሆኑ እንደሚችሉ ገልጸዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በክልሉ የኢትዮ ቴሌኮም ስልክ እና ኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡ የተሰማው የህወሓት ታጣቂዎች፣ ረቡዕ ዕለት በክልሉ የሚገኙ ሦስት አውሮፕላን ማረፊያዎችን ተቆጣጥረው "ተከፈተብን" ያሉትን ጥቃት ለመከላከል ኃይሎቻቸው "እርምጃ እንዲወስዱ ማዘዛቸውን" ከገለፁ በኋላ ነው።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትም ለመጀመርያ ጊዜ የህወሓት ታጣቂዎች ማክሰኞ መስከረም 12/2019 ዓ.ም. በሰሜን ወሎ በይዞታ ቀጣናው ላይ የከፈቱበትን ጥቃት መመከቱን ሐሙስ ዕለት ገልጿል።

ሠራዊቱ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ ባጋራው መረጃ ማክሰኞ ለረቡዕ አጥቢያ ከሌሊቱ 9 ሰዓት ጀምሮ የህወሓት ታጣቂዎች በሰሜን ምሥራቅ ዕዝ የግዳጅ ቀጣና ጥቃት መፈጸማቸውን ገልጿል።

የህወሓት ታጣቂዎች በክልሉ የሚገኙ ሦሰት አውሮፕላን ማረፊያዎችን መቆጣጠራቸው ከተሰማ በኋላ ወደ ክልሉ የሚደረጉ አውሮፕላን በረራዎች ከረቡዕ ማለዳ ጀምሮ ተቋርጠዋል።

ሐሙስ ዕለትም ወደ ላሊበላ የሚደረጉ በረራዎች መቋረጣቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

በአማራ እና አፋር አካባቢዎች የሚካሄዱት ውጊያዎች መቀጠላቸው እየተዘገበ ባለበት ወቅት ከሐሙስ ምሽት 4፡30 ጀምሮ በትግራይ የኢንተርኔት እና የስልክ አገልግሎት መቋረጡ ተሰምቷል።

የኔት ብሎክስ በክልሉ የኢንተርኔት ግንኙነት መቋረጡን በሚመለከት ባወጣው መረጃ ላይ ". . . በሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢ የኢንተርኔት መስተጓጎል ተከስቷል። ይህ ክስተት በትግራይ ኃይሎች እና በአገሪቱ ጦር መካከል ግጭቱ እየተባባሰ ባለበት ወቅት የተከሰተ ነው" ብሏል።

የፌደራል መንግሥቱ እስካሁን ድረስ በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ስላለው ጦርነት በይፋ የሰጠው መግለጫ የለም።

ሮይተርስ የዜና ወኪል ያነጋገራቸው ሰባት የታሪካዊቷ ላሊበላ ከተማ ነዋሪዎች በአካባቢው ውጊያ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ በሰሜን ወሎ የተከፈተበትን ጥቃት በመመከት ከ500 በላይ ተዋጊዎችን መማረኩን እና በርካቶችን መግደሉን አስታውቋል።

የተባበሩት መንግሥታት እና የአውሮፓ ኅብረት ሁሉም ተፋላሚ ወገኖች ውጊያ አቁመው ወደ ፕሪቶሪያው ስምምነት እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል።

የፌደራል መንግሥቱ የህወሓት ታጣቂዎች ጥቃት መክፈታቸውን በመግለጽ ወንጅሏቸዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ ኒው ዮርክ የሚገኙት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ጌታቸው ረዳ "በትግራይ ሌላ ዙር ጦርነት እንዳይቀሰቀስ ብዙዎች ጥረት ቢያደርጉም፣ ዛሬ ጠዋት [ረቡዕ] የህወሓት አመራር" ጦርነት መክፈቱን አመልክተዋል።

አክለውም የህወሓት ኃይሎች በአፋር እና በአማራ ክልሎች በሚገኙ ቦታዎች በኩል ሙሉ ጥቃት መክፈታቸውን በመግለጽ ጦርነት መቀስቀሱ "እጅግ የሚያሳዝን" ክስተት ነው ብለዋል።

የህወሓት መሪዎች በበኩላቸው ኃይሎቻቸው ወደ መከላከል ውጊያ እርምጃ መግባታቸውን ገልጸው፤ ውሳኔው የተላለፈው የመንግሥት ኃይሎች ቀደም ብለው ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ ነው ሲሉ ከስሰዋል።

ኤኤፍፒ የዜና ወኪል በአፋር ክልል የሚንቀሳቀስ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ምንጭን ጠቅሶ ሐሙስ ዕለት የትግራይ ኃይሎች በክልሉ ድንበር አቅራቢያ የምትገኘውን የያሎን ከተማ ለመቆጣጠር ከባድ የጦር መሳሪያ ጥቃቶችን መክፈታቸውን ዘግቧል።

ለዜና ወኪሉ "አሁን ሙሉ በሙሉ ጦርነት ውስጥ ነን" ሲሉ የህወሓት ምክትል ፕሬዝዳንት አማኑኤል አሰፋ ተናግረው ነበር።

በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም ጦርነት የተቀሰቀሰው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር እና የህወሓት ባለሥልጣናት ለወራት ባለመግባባት እና መካሰስ ውስጥ ከቆዩ በኋላ ነው።

ለሁለት ዓመት የተካሄደው ደም አፈሳሽ ጦርነት በፕሪቶሪያ ስምምነት ቢቋጭም ከቅርብ ወራት ወዲህ ግን የፌደራል መንግሥቱ እና ህወሓት አንዳቸው ሌላኛቸው ስምምነቱን በመጣስ ሲካሰሱ ተደምጠዋል።

እሁድ ዕለት ህወሓት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን መንግሥትን ለመጣል ከሌሎች ስድስት የታጠቁ ቡድኖች ጋር ጥምረት መመስረቱን አስታውቋል።

ቀደም ሲል ለሁለት ዓመት በተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት ወቅትም በተመሳሳይ መልኩ የስልክና ኢንተርኔት አገልግሎቶች ተቋርጠው እንደነበር ይታወሳል።