ቀኝ አክራሪው የእስራኤል ሚኒስትር የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ዐቃቤ ሕግ የእስር ማዘዣ እንደጠየቀባቸው ተናገሩ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ቀኝ አክራሪው የእስራኤል የፋይናንስ ሚኒስትር ባዛሌል ስሞትሪች የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ሕግ "ምሥጢራዊ" የእስር ማዘዥ እንዲወጣባቸው ጥያቄ ማቅረቡ እንደተነገራቸው ገለጹ።

እስራኤል በወረራ በያዘቻቸው የዌስት ባንክ ግዛቶች ውስጥ የሚተገበሩ ፖሊሲዎችን በተመለከተ ሰፊ ሥልጣን ያላቸው ሚኒስትሩ፤ ወጥቶብኛል ላሉት የእስር ማዘዣ ምላሽ ለመስጠት ታዋቂው የፍልስጤም መንደር 'ቤዱኢን' እንዲፈርስ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

የእስራኤሉ ሚኒስትር የቀረበባቸው ክስ ምን እንደሆነ አልገለጹም። ይሁን እንጂ እርምጃውን "የጦርነት አዋጅ" ሲሉ የገለጹት ስሞትሪች፤ የፍልስጤም ባለሥልጣንንም ተጠያቂ አድርገዋል።

የእስር ማዘዣዎችን የማውጣት ሒደት በምሥጢር የሚከናወን ሲሆን በዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ዳኞችም መጽደቅ ይኖርበታል። ፍርድ ቤቱ ስለ ጉዳዩ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም። በቅርቡ ግን በአምስት የእስራኤል ባለሥልጣናት የእስር ማዘዣ ወጥቷል መባሉን አስተባብሎ ነበር።

የፍልስጤም ባለሥልጣን የእስራኤሉ ሚኒስትር መንደር እንዲፈርስ ያስተላለፉትን ትዕዛዝ "አደገኛ መባባስ" በማለት ተቃውሞታል።

የእስራኤል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በአውሮፓውያኑ 2018 ኻን አል አህማር የተባለው መንደርን በተመለከተ የተላለፈውን የማፈናቀል ትዕዛዝ አጽንቶት ነበር።

የተባበሩት መንግሥታት፣ ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት እና ሌሎች አካላት ግን እርምጃው ዓለም አቀፍ ሕግን እንደሚጥስ በመግለጽ አስጠንቅቀዋል።

ስሞትሪች ማክሰኞ ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ "ትናንት ምሽት ሄግ የሚገኘው ፀረ ሴማዊው ፍርድ ቤት ወንጀለኛ ዐቃቤ ሕግ እኔ ላይ ምሥጢራዊ ዓለም አቀፍ የእስር ማዘዣ እንዲወጣ ጥያቄ ማቅረቡ ተነግሮኛል" ብለዋል።

"እንደ ሉዓላዊትና ነጻ አገር፤ በቋሚነት ከእስራኤል መንግሥት በተጻራሪ ከሚቆሙ ወገንተኛ አካላት የሚመጡ ግብዝ ትዕዛዞችን አንቀበልም" ሲሉም ተናግረዋል።

"በበቀል መልሼ እታገለላሁ" ሲሉ ቃል የገቡት ሚኒስትሩ፤ በእስራኤል ቁጥጥር ሥር ያልሆነውን የዌስት ባንክ ግዛት የሚያስተዳድረው የፍልስጤም አስተዳደር አመራሮች "ጦርነት ጀምረዋል፣ ጦርነትም ያገኛሉ" ሲሉ ዝተዋል።

"እዚህ መግለጫዬን እንዳጠናቀቅኩኝ ወዲያውኑ የኻን አል አህማርን መንደር [ነዋሪዎችን] ማስለቀቂያ ትዕዛዝ እፈርማለሁ" ሲሉ ተደምጠዋል።

የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት የዐቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት "ቀርቧል የተባለ ማንኛውንም የእስር ትዕዛዝ ማመልከቻ በተመለከተ አስተያየት መስጠት እንደማይችል" ገልጿል። ይህ ዓይነት ማመልከቻዎች "በፍርድ ቤቱ ዳኞች ካልተፈቀደ በስተቀር ምሥጢራዊ" በሚል ምድብ ውስጥ እንደሚካተቱም አስረድቷል።

የፍልስጤም ባለሥልጣን ሚኒስትር የሆኑት ሙያድ ሻባን በበኩላቸው ኻን አል አህማር ላይ የተላለፈው የማስለቀቂያ ትዕዛዝ "የእስራኤል የወረራ መንግሥት በፍልስጤም ሕዝብ ላይ የሚከተለው በኃይል የማፈናቀል ፖሊሲ ላይ የታየ አደገኛ መባባስ" እንደሆነ ገልጸዋል።

የአሁኑ ትዕዛዝ እስራኤል ከኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ ለማከናወን ለረዥም ጊዜ ያቀደችው ፕሮጀክት አካል እንደሆነ በማንሳትም አስጠንቅቀዋል። እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ እስራኤል በዚህ ፕሮጀክት አማካኝነት "የሰሜናዊውን ዌስት ባንክ ከደቡባዊው ክፍል በመለየት የገነባቻቸውን የሰፈራ መንደሮች መካከል ሙሉ ግዛታዊ ትስስር" እንዲኖር ትፈልጋለች።

ይህ አካሄድ "ተያያዥ እና ተጨባጭ የሆነች አገረ ፍልስጤምን የመመሥረት ዕድልን ሙሉ በሙሉ የሚያጠፋ" እንደሆነም አስጠንቅቀዋል።

እስራኤል በአውሮፓውያኑ 1967 የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ወቅት ፍልስጤማውያን ከጋዛ ጋር በአንድነት አገር ለመመሥረት የሚያስፈልጓቸው ግዛቶች የሆኑትን ዌስት ባንክ እና ምሥራቅ ኢየሩሳሌምን ተቆጣጥራለች።

ከዚያ ወዲህም 700,000 አይሁዶች የሰፈሩባቸው 160 ገደማ የሰፈራ መንደሮችን ገንብታለች። በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት እነዚህ ሠፈራዎች ሕገ ወጥ ናቸው።