ምርጫ ቦርድ የኢሕአፓው አመራርን ራስን ከእጩነት የማግለል "ጥያቄ እንደማይቀበል" አስታወቀ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት የተባለውን ጥምረት በመወከል ለውድድር የቀረቡት ይሳቅ ወልዳይ ራሳቸውን ከእጩነት ለማግለል ያቀረቡትን "ጥያቄ እንደማይቀበል" አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) አመራር የሆኑት ይሳቅ በበኩላቸው በእጩነት መቅረብ "መብት እንጂ ግዴታ እንዳልሆነ" በመግለጽ በምርጫው ለመወዳደር እንደማይገደዱ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ይሳቅ ኢሕአፓ አባል የሆነበትን ትብብር በመወከል በእጩነት የቀረቡት በአዲስ አበባ ከተማ አራዳ ክፍለ ከተማ ምርጫ ክልል 1/9 ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውድድር ነበር።

ይሁን እንጂ ሰኞ ዕለት ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በጻፉት ደብዳቤ ሊካሄድ ከሁለት ሳምንት ያነሰ ጊዜ ከቀረው "ጠቅላላው የምርጫ ሒደትም ሆነ ከእጩነት" ራሳቸውን ማግለላቸውን አስታውቀዋል።

ይሳቅ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት "ኢሕአፓም ሆነ ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ምርጫው ተዓማኒ እና ፍትሐዊ እንዲሆን የምርጫ አስቻይ ሁኔታዎችን በተመለከተ ያስቀመጧቸው ቅድመ ሁኔታዎች ባለመሟላታቸው" እንደሆነ ገልጸዋል።

ምርጫ ቦርድ ትናንት ማክሰኞ ግንቦት 11/2018 ዓ.ም. ለዚህ ውሳኔ መልስ መስጠቱን ደብዳቤው የተጻፈላቸው ይሳቅ እና በግልባጭ የተጠቀሰው ኢሕአፓ ፕሬዝዳንት የሆኑት አብርሃም ሃይማኖት ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ቢቢሲ በተመለከተው ደብዳቤ መሠረት ምርጫ ቦርድ የይሳቅን ውሳኔ ውድቅ አድርጓል። የቦርዱ ደብዳቤ ሁለት ጉዳዮችን በምክንያትነት ጠቅሷል።

የመጀመሪያው ምክንያት ከጊዜ ሰሌዳ ጋር የተያያዘ ነው። ምርጫ ቦርድ "ከእጩነት የመልቀቅ ወይም መሰረዝ ጥያቄን በሕጉ መሠረት ተቀብሎ ሲያስተናግድ የቆየው እስከ ሚያዝያ 23 ቀን 2018 ዓ. ም." እንደነበር ገልጿል።

በመሆኑም "ይህ ጊዜ ካለፈ በኋላ" ይህንን ዓይነት ጥያቄ እንደማያስተናግድ አስረድቷል።

በተጨማሪም ቦርዱ የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ታትመው ወደ አገር ውስጥ መግባታቸውን በምክንያትነት አንስቷል። "ለምርጫ 12 ቀን ሲቀረው የቀረበ ጥያቄ የሕግ መሠረት የሌለው በመሆኑ ቦርዱ ጥያቄውን ያልተቀበለ መሆኑን ያስታውቃል" ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

የአሕአፓው ይሳቅ ግን የምርጫ ቦርድን ውሳኔ እንደማይቀበሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል። "ከእጩነት ራሴን ስለማግለሌ ለምርጫ ቦርድ አሳወቅኩኝ እንጂ ጥያቄ አይደለም ያቀረብኩት" ያሉት ይሳቅ፤ "እጩ ሆነህ መቅረብ መብት እንጂ ግዴታ አይደለም። በማንኛውም ጊዜ ሁለት ቀንም፣ ሦስት ቀንም ሲቀር መውጣት ይቻላል" ሲሉ ተከራክረዋል።

በምርጫ ቦርድ ደብዳቤ ላይ የተጠቀሰው የጊዜ ገደብ "ፓርቲው አንድ እጩውን ሰርዞ ሌላኛው እጩውን ለመተካት" በሚጠይቅበት ጊዜ የሚተገበር እንደሆነም ገልጸዋል።

ቢቢሲ የይሳቅን ቅሬታ በተመለከተ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስተያየትን ለማካተት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

በ2012 ዓ. ም. የወጣው የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ስለ "የእጩዎች ከውድድር መውጣት እና መተካት" ባሰፈረበት ክፍሉ፤ "አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ወይም የግል እጩ ከውድድር ራሱን ሊያገል" እንደሚችል ደንግጓል።

ራሱን ያገለለው እጩ ውሳኔውን "ለወከለው ፖለቲካ ፓርቲ በጽሑፍ ማሳወቅ" እንዳለበትም ይገልጻል። አዋጁ ራስን ከእጩነት ማግለል ስለሚቻልበት የጊዜ ሰሌዳ ባያስቀምጥም፤ ፓርቲዎች ግን እጩውን መተካት የሚችሉት "ከድምጽ መስጫው ቀን ከአንድ ወር በፊት ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ" እንደሆነ አስፍሯል።

ይህንን የሚያነሱት ይሳቅ "ግለሰቦች [ድምጽ መስጫ ወረቀት] ታተመም አልታተመም በማንኛውም ጊዜ መውጣት ይችላሉ […] 'አልሳተፍም' ካለ ድምጹ የማይጸና እና ተፈጻሚነት የሌለው (null and void) እንደተደረገ ነው መታሰብ የሚችለው እንጂ [ድምጽ መስጫ ወረቀት] ስለታተመ 'ግዴታ ግባ' የሚል የሕግ ማዕቀፍ የለም" ብለዋል።

ምርጫ ቦርድ ከእጩነት ራስን የማግለል ውሳኔውን እንደማይቀበለው ቢያሳውቅም ይሳቅ ግን "በእጩነትም በተወዳዳሪነትም" እንደማይቀጥሉ ተናግረዋል። "እጩ ሆኜ አልቀጥልም፤ ምክንያቱም እንድቀጥል የሚያስገድደኝ ሕግ የለም[…] በእኔ እጩ መሆን እና አለመሆን ማንም አይወስንልኝም" ሲሉ አቋማቸውን አስረድተዋል።