ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በግብፅ የተሰባሰቡት የኢትዮጵያ ጎረቤቶች በቀይ ባሕር እና በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ላይ የጋራ መግለጫ አወጡ
የግብፅ፣ የኤርትራ፣ የሶማሊያ እና የሱዳን መሪዎች እሁድ ዕለት በቀይ ባሕር እና አባይን ጨምሮ በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ላይ ተፈጻሚነት ያላቸውን ዓለም አቀፍ ሕጎች ማክበር አስፈላጊ መሆኑን በጋራ ባወጡት መግለጫ አመለከቱ።
አገራቱ በግብፅ ኤል አላሚን ከተማ በተካሄደው የአራትዮሽ ጉባኤ ማጠቃለያ ላይ በጋራ ባወጡት መግለጫ፣ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ከማድረስ የመቆጠብ መርኅን እንዲሁም አስቀድሞ በማሳወቅ፣ በመመካከር እና በመግባባት የመተባበርን ግዴታ ማክበር አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።
አራቱ አገራት የኤል አላሚን ስምምነት ሲሉ በገለጹት በዚህ መግለጫ ላይ ከአባይ ወንዝ አጠቃቀም አንጻር የታችኛው ተፋሰስ አገራት የሆኑትን ግብፅ እና ሱዳንን የሚጎዳ የተናጠል ድርጊትን ውድቅ አድርገዋል።
በግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አል ሲሲ አስተናጋጅነት፤ የኤርትራው ኢሳያስ አፈወርቂ፣ የሶማሊያው ሐሰን ሼኽ ሞሐሙድ እና የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበር ጄነራል አብዱል ፋታህ አል ቡርሃን የተሳተፉበት አራትዮሽ የምክክር ጉባኤ መስከረም 24/2019 ዓ.ም. በግብፅ ተካሂዶ የጋራ አቋማቸውን ይፋ አድርገዋል።
ግብፅ፣ ኢትዮጵያ እና ሱዳን ለአስራ አምስት ዓመታት በአባይ ወንዝ ጉዳይ ላይ ከስምምነት ለመድረስ ሲደራደሩ የነበረ ቢሆንም ሦስቱንም አገራት የሚያስማማ ሁሉን አቀፍ መግባባት ላይ መድረስ አልተቻለም።
ኢትዮጵያ በ2017 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ አጠናቅቃ ያስመረቀችው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ከ5000 ሜጋ ዋት በላይ የኤሌትሪክ ኃይል ያመነጫል።
ግብፅ እና የሱዳን በተደጋጋሚ በአባይ ወንዝ ላይ ኢትዮጵያ የገነባችው ታላቁ ሕዳሴ ግድብ በምሥራቅ የናይል ተፋሰስ አገራት ላይ ዘላቂ ስጋት ደቅኗል ሲሉ ይከስሳሉ።
ኢትዮጵያ በግድቡ ምክንያት በተፋሰሱ አገራት ላይ የሚደርስ ጉዳት እንደሌለ በመግለጽ በተፈጥሮ ሀብቷ በፍትሐዊነት የመጠቀም ሕጋዊ መብቷን እንደምትጠቀም በተደጋጋሚ ስትገልጽ ቆይታለች።
ግብፅ ግን በግድቡ የውሃ ይዘት እና የሚለቀቅበት ሁኔታ ላይ ኢትዮጵያ አስገዳጅ ሕጋዊ ስምምነት እንድትፈርም ትፈልጋለች።
በግብፅ አስተባባሪነት የተካሄደው የአራቱ አገራት ጉባዔ በወጣው የኤል አላሚን ስምምነት ላይ በአፍሪካ ቀንድ የሚፈጠሩ ውጥረቶች እና አለመግባባቶች ፖለቲካዊ እና ሰላማዊ መፍትሄዎች እንዲፈለጉ ጥሪ አቅርቧል።
እሁድ ዕለት በግብፅ ኤል አላሚን ከተማ በተካሄደው የአራቱ አገራት የመሪዎች ጉባኤ ማጠቃለያ ላይ በጋራ ባወጡት መግለጫ፣ የቀጣናው መረጋጋት በሉዓላዊነት፣ በግዛት አንድነት፣ በመልካም ጉርብትና ግንኙነት መርሆዎች መከበር ላይ እንዲሁም በውስጣዊ ጉዳዮች ላይ ጣልቃ አለመግባትን እንደሚያካትት ጠቅሰዋል።
ስምምነቱ ይፋ የተደረገው በትግራይ እና በአዋሳኞቹ የአማራ እና የአፋር ክልሎች ውስጥ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ያለው ውጥረት በተባባሰበት ወቅት ነው።
በኤርትራ ይደገፋሉ የሚባሉት የህወሓት ኃይሎች ከሌሎች አማጺያን ጋር ጥምረት በመፍጠር የኢትዮጵያ መንግሥትን ለመጣል የጀመሩት ጥቃት ሁለት ሳምንት ሊሞላው ጥቂት ቀናት የቀሩት ሲሆን በበርካታ ሰዎች ላይ ጉዳት ማድረሱ ተዘግቧል።
በጦርነቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ኤርትራ የህወሓት ኃይሎችን እየደገፈች መሆኑን በመግለጽ ሲከስስ የነበረ ከመሆኑ በተጨማሪ የአፋር ክልል እና የፌደራል ባለሥልጣናት የኤርትራ ወታደሮች ድንበር ተሻረግው ጥቃት መክፈታቸውን በመግለጽ ከስሰዋል።
ሁለቱ አገራት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ግንኙነታቸው ከወዳጅነት ወደ ጠላትነት ተሸጋግሮ ወደ ጦርነት ሊገቡ ይችላሉ የሚል ስጋት ተፈጥሯል።
በመጀመሪያው የትግራይ ጦርነት ወቅት በአንድ ተሰልፈው የህወሓት ኃይሎችን የወጉት የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግሥታት ግንኙነታቸው የተበላሸው ደም አፋሳሹን ጦርነት ያስቆመው የፕሪቶሪያ ስምምነት ከተፈረመ በኋላ ነው።
ከዚያም በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት ሉዓላዊ የባሕር በር የማግኘት ፍላጎቱን ይፋ ካደረገ በኋላ ሁለቱ አገራት ይፋ ወደ ወጣ ውዝግብ ውስጥ ገብተው ቆይተዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት እና መገናኛ ብዙኃን የኤርትራ መንግሥት ህወሓትን እና ታጣቂ ኃይሎችን በመደገፍ የአገሪቱን ሰላም ለማናጋት እየሠራ መሆኑን በመግለጽ ሲከስሱ ቢቆዩም ኤርትራ ግን ክሱን በተደጋጋሚ አስተባብላለች።
ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት አስር የኤርትራ ዲፕሎማቶችን ከአዲስ አበባ ሲያባርር ኤርትራ ደግሞ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አቋርጣለች።
ይህም ለ20 ዓመታት ተቋርጦ ከስምንት ዓመት በፊት መልሶ የተጀመረውን የሁለቱን አገራት ግንኙነት እንዲቋረጥ አድርጎታል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከኤርትራ በተጨማሪ የግብፅ አንድ ዲፕሎማትንም ከግዛቱ ያባረረ ሲሆን፣ ካይሮም ተመሳሳይ እርምጃ ወስደለች።
አራቱ አገራት በቀይ ባሕር ላይ የሚደረግ የመርከቦች እንቅስቃሴ ነፃነት መብትን በመግለጫቸው ላይ ጠቅሰው፣ የቀይ ባሕር አስተዳደር እና ቁጥጥር በቀይ ባሕር ዳርቻ በሚገኙ አገራት ብቸኛ ኃላፊነት ስር የሚወድቅ መሆኑን አስታውቀዋል።
ግብፅ እና ኤርትራ የቀይ ባሕር "ደኅንነት እና አስተዳደር የሚመለከተው የጠረፉን አገራት ብቻ" እንደሆነ ሲገልጹ ይህ የመጀመርያቸው አይደለም።
የጠረፉ አካል ያልሆኑ አገራት ቀይ ባሕርን "በሕገ ወጥ መንገድ ለመቆጣጠር የሚደረጉት ሙከራ ዓለም አቀፍ ሕግን የጣሰ ነው" ሲሉም ከዚህ በፊት ተናግረው ነበር።
የአራቱ አገራት መሪዎች በእሁዱ ጉባዔያቸው የሱዳንን ጉዳይ በተመለከተ፣ መሪዎቹ የአገሪቱን አንድነት፣ ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነት እና ብሔራዊ ተቋማት እንደሚደግፉ አረጋግጠው፣ ትይዩ አካላትን ማቋቋም እንዲሁም ለቅጥረኛ ወታደሮች የሚደረግን ማንኛውንም ድጋፍ ተቃውመዋል አድርገዋል።
በሱዳናውያን ባለቤትነት እና አመራር የሚካሄድ የፖለቲካ ሂደት እንዲቀጥል ጥሪ ያቀረቡት መሪዎቹ፣ የሱዳንን ብሔራዊ ተቋማት ለማጠናከር የሚደረጉ ጥረቶችንም እንደሚደግፉ አስታውቀዋል።
በሌላ በኩል ደግም የሶማሊያ የግዛት አንድነት እና ሉዓላዊነት ሙሉ በሙሉ እንደሚደግፉ የገለፁት መሪዎቹ፣ የሶማሊያን ግዛታዊ አንድነት የሚሸረሽሩ ማንኛቸውንም ጣልቃ ገብነቶች፣ በተለይም ለሶማሊላንድ የሉዓላዊ አገርነት እውቅና የመስጠት ጥረቶችን ውድቅ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።
መሪዎቹ ሶማሊያ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት የምታደርገውን ጥረት በመደገፍ ለአፍሪካ ኅብረት የማረጋጋት ተልዕኮ (ኤዩሶም) በቂ፣ ዘላቂ እና አስቀድሞ ሊታወቅ የሚችል የገንዘብ ድጋፍ እንዲያቀርቡም ለቀጣናዊ እና ዓለም አቀፍ አጋሮች ጥሪ አቅርበዋል።
መሪዎቹ በአራቱ እና በሌሎች የአፍሪካ አገራት መካከል ያለውን ምክክር እና ቅንጅት ለማጠናከር እንዲሁም የጉባኤውን ውጤቶች ለመከታተል የሚያስችል አሠራር ለመዘርጋት ተስማምተዋል።
በአራቱ አገራት መካከል ያለውን ቅንጅት ለማጎልበት ሲባል፣ ይህ የምክክር ጉባኤ በየጊዜው እና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ እንዲካሄድም ተስማምተዋል።