በመቀለ ለቀናት ተቋርጦ የነበረው የሞባይል እና የኢንተርኔት አገልግሎት መጀመሩን ነዋሪዎች ገለፁ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀለ እና አካባቢው ለቀናት ተቋርጦ የነበረው የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎት መጀመሩን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገለፁ።

በትግራይ ክልል የኢትዮ ቴሌኮም የኢንተርኔት እና የስልክ አገልግሎት የተቋረጠው ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ምሽት ነበር።

የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎት ዳግም የተጀመረው ቅዳሜ መስከረም 23/2019 ዓ.ም. የአገር መከላከያ ሠራዊት እና የትግራይ የሰላም ኃይል መቀለን መቆጣጠራቸውን ተከትሎ ነው።

በትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀለ የተቋረጠው የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎት ከ10 ቀናት በኋላ እሁድ ማለዳ ሲመለስ ነዋሪዎች ለወዳጅ ዘመዳቸው መደወል መቻላቸውን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ቢቢሲ ዛሬ ማለዳ ያነጋገራቸው ሁለት ነዋሪዎች በመቀለ ከረፋድ አራት ሰዓት ጀምሮ እንዲሁም በውቅሮ እና ሌሎች አካባቢዎች ደግሞ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ጀምሮ ስልክ መሥራቱን ተናግረዋል።

ለቢቢሲ አስተያየታቸውን የሰጡት እነዚህ ነዋሪዎች መቀለ ከተማን ቅዳሜ ከሰዓት የፌደራል ኃይሎች እስኪቆጣጠሩ ድረስ በመንግሥት ተቋማት ላይ ዘረፋዎች በስፋት ሲፈጸሙ እንደነበር ተናግረዋል።

ስማቸው ለደኅንነታቸው ሲባል እንዳይጠቀስ የጠየቁት የመቀለ ነዋሪ ቅዳሜ ከሰዓት እና እሁድ ጠዋት በመቀለ ከተማ የትግራይ ሰላም ኃይሎች በሚል የሚጠሩት እና ከፌደራል መንግሥቱ ጎን በመሆን የተሰለፉት ታጣቂዎች የከተማውን ነዋሪዎች ሲያረጋጉ እና ፀጥታ የማስከበር ሥራ ሲሠሩ መመልከታቸውን ጨምረው ገልጸዋል።

አክለውም ባለፉት አስር ቀናት በመቀለ የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎት በተቋረጠበት ወቅት የነበረው የገንዘብ እጥረት በጣም አሳሳቢ እንደነበር ገልጸው፣ አሁን የአገልግሎቱ መመለስ ትልቅ እፎይታ እንደሰጣቸው ተናግረዋል።

ፍጹም ብርሃን የተባሉ የመቀለ ከተማ ነዋሪ ባለፉት 24 ሰዓታት በከተማዋ የሚገኙ የመንግሥት ቢሮዎች የክልሉ ፕሬዚዳንት እና ፖሊስ ጣቢያዎችን ጨምሮ መዘረፋቸውን ተናግረዋል።

አቶ ፍፁም ባለፉት 10 ቀናት በክልሉ የነበረውን ሁኔታ ሲገልጹት ከፍተኛ የደህንነት ስጋት እንዲሁም አፈሳ ነበር ብለዋል።

በከተማው ትናንት የትግራይ የሰላም ኃይሎች መግባታቸውን ተከትሎ አሁን አንጻራዊ መረጋጋት መኖሩን የተናገሩት አቶ ፍጹም፣ የፌደራል ኃይሎች ከከተማዋ መግቢያዎች የሚገኙ ኬላዎች ላይ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በዘረፋ ወቅት ሦስት ሰዎች መሞታቸውን መስማታቸውን የገለጹት እኚህ ነዋሪ በከተማዋ ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት ተፈጥሮ እንደነበርም አክለዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የውቅሮ ከተማ ነዋሪ በበኩላቸው ባለፉት ቀናት በከተማዋ የነበረውን አለመረጋጋት ገልጸዋል።

አቶ ፍጹም በመቀለ ዛሬ ጠዋት ጀምሮ አንጻራዊ ሰላም ቢኖርም ከርቀት የተኩስ ድምጽ እንደሚሰማ ተናግረዋል።

"አሁንም ከርቀት የተኩስ ድምጽ ይሰማል፤ ሰዎች ቀጥሎ ምን ይሆናል በማለት ስጋት ውስጥ ናቸው" ብለዋል።

የኢንተርኔት አገልግሎት በከተማይቱ በድጋሚ መጀመሩ በሞባይል ስልክ የሚደረጉ የገንዘብ ዝውውሮች ዳግም እንዲጀመሩ ያደርጋል።

በትግራይ የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎት የተቋረጠው በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መሪዎች መካከል የነበረው ውዝግብ ተባብሶ መስከረም ረቡዕ 13/2019 ዓ.ም. ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ ነው።

ባለፈው ሳምንት የስልክ አገልግሎት ከተቋረጠ በኋላ ሮይተርስ የዜና ወኪል የትግራይ ክልል አስተዳደርን ተቆጣጥረው ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ግጭት ውስጥ የገቡት የህወሓት አመራሮች የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲቋረጥ ማድረጋቸውን ዘግቧል።

በቀድሞ የህወሓት አባላት የተቋቋመው እና በጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ የሚመራው ስምረት ፓርቲም በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ ባጋራው መልዕክት የህወሓት መሪዎች አገልግሎቱን አቋርጠዋል በማለት ከስሶ ነበር።

ትናንት ቅዳሜ ከሰዓት የፌደራል ኃይሎች መቀለን ከተቆጣጣሩ በኋላ አመሻሽ ላይ ህወሓት ባወጣው መግለጫ ከተማዋን "ለጊዜው" ለቅቆ መውጣቱን አስታውቋል።

በትግራይ ክልል መንግሥት ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ስም በወጣው መግለጫ አስተዳደሩ በበርካታ ግንባሮች የተጀመሩ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች በጥቂት ቀናት ውስጥ ወደ ክልሉ ዋና ከተማ መስፋፋታቸውን በመግለጽ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የአደጋ ስጋት መደቀናቸውን ገልጿል።

ህወሓት መቀለ ከተማን "በጊዜያዊነት" ለቅቆ የወጣው ውጊያ በነዋሪዎች ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ተጽዕኖ ለመቀነስ እና አስተዳደሩ ከሌላ ቦታ ሥራውን እንዲቀጥል ለማስቻል እንደሆነ ተናግሯል።